ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ቴሌብር ›› የተሰኘ ለማሕበረሰቡ ምቹና ሁሉን አካታች የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ ዘዴ የሆነውን የሞባይል ገንዘብ (mobile money service) አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡
“ቴሌ ብር” የተሰኘው የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ ዘዴ፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ደንበኞች ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ ገንዘብ እንዲልኩ፣ እንዲቀበሉና ግዢ እንዲፈፅሙ የሚስችል ሲሆን፣ የክፍያ ስርዓቱ ደንበኞች ካሽ ወይም ቼክ ሳያስፈልጋቸው ዘርፈ ብዙ ክፍያዎችን እንዲፈፅሙ ያደርጋል። በአገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የትስስር መንገዶች ላይ ገንዘብ መላላክን፣ ለዕቃና አገልግሎቶች ግዢ የሚደረጉ ክፍያዎችን መፈጸም ያስችላል።
የትምህርት ቤት፣ የውሃ እና ኤሌክትሪክ እንዲሁም ሌሎች መሰል ክፍያዎችን በስልክ መክፈልና በኢትዮ ቴሌኮም ለሚቀርቡ እንደ አየር ሰዓት ግዢ ላሉ አገልግሎቶች ክፍያን ለመፈፀም እንደሚያስችል ተገልጿል። ከአገር ውጪ ካለው ዲያስፖራ ገንዘብ ለመቀበል፣ ገንዘብ ለመቆጠብ፣ ብድር ለማግኘት እና የባንክ አካውንት ከቴሌብር ጋራ እንዲተሳሰር የሚፈቅድ ነው።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ለ “ቴሌ ብር” ለመመዝገብ የኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርድ ያለበት ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን እና ማንነታቸውን የሚገልፅ መታወቂያ ይዘው ወደ ቴሌብር ወኪሎች አልያም ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከላት በማምራት መመዝገብ እንደሚቻል ተመላክቷል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013


