የሰላም ሚኒስቴር መጪውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና የተረጋጋ ለማድረግ የሚያስችል ስምምት ከቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎችና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱ በመጀመሪያ ዙር የሰላምና የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው በአራቱ ክልሎች የሚተገበር ሲሆን፣ 2ሺህ ለሚሆኑ የሚሊሻ አባላት ስልጠና በመስጠት በየአካባቢያቸው ሰላምና ጸጥታን ማስከበር እንዲችሉና በምርጫ ወቅት መደበኛውን የጸጥታ ኃይል ማገዝ እንዲችሉ አቅም ለመፍጠር ያለመ ነው።
በሰላም ሚኒስቴር የሰላምና የብሔራዊ መግባባት ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ወርቅነሽ ብሩ ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ሲሰሩ የነበሩ የሚሊሻ አባላትን አቅም በማጎልበት ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ አስምረውበታል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ኃ/ሚካኤል በበኩላቸው ፌደራል ፖሊስ በቀጣይ ዓመታት ወጥ የሆነ የሚሊሻ ኃይል ለማፍራት መመሪያ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአሸባሪ ቡድኖች እንቅስቃሴ በስፋት በሚታይባቸው አካባቢዎች፣ መደበኛ የጸጥታ ኃይሉ በቋሚነት በማይቀመጥባቸው አካባቢዎች እና ለምርጫው እንቅስቃሴ ለማድረግ አስቸጋሪ በሆነባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚሊሻ ኃይሉ በስፋት በስራ ላይ እንደሚያሰማራ ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013



