ከ2014 በጀት ውስጥ 300 ቢሊዮን ያክሉ ለግዥ ይውላል
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ከሚቀጥለው ሐምሌ ወር ጀምሮ በተመረጡ ዘጠኝ ከፍተኛ የመንግሥት ግዥ ፈጻሚ በሆኑ ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
አዲሱ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ተግባራዊ የሚደረግባቸው ከፍተኛ የመንግሥት ግዥ የሚፈጽሙ የመንግሥት ተቋማት የተባሉት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት እንዲሁም ራሱ ኤጀንሲው ናቸው።
ኢትዮጵያ እስከ አሁን ስትጠቀም የነበረው የግዥ ስርዓት በቴክኖሎጂ ያልተደገፈና ከሰው ግንኙነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ በጨረታዎች ላይ ሙስና የመፈጸም እድሉ ሰፊ እንደነበር የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። በቀጥታ በሰዎች አማካይነት የሚሠራ የጨረታ ሥራ ለሙስና ተጋላጭ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው የሚሉት ሃጂ፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የምታደርገው የኤሌክትሮኒክ ግዥ ችግሩን ይቀርፈዋል ብለዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የተመረጡ ዘጠኝ የመንግሥት ተቋማት ከሚቀጥለው ሐምሌ 7/2013 ጀምሮ ግዣቸውን ከሰው ንክኪ ነፃ ነው በተባለው የኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ይፈጽማሉ ተብሏል። አዲሱ የግዥ ሥርዓት በዘጠኙ ተቋማት ላይ መጀመሪያ ትግበራው ከተገመገመ በኋላ በሥድስት ወራት ውስጥ 50 ተቋማት የግዥ ስርዓታቸውን ወደ ኤሌክትሮኒክ ግዥ እንዲያስገቡ እንደሚደረግ ሃጂ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
አዲሱ ኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት በዋናነት አገልግሎት የሚሰጠው በገንዘብ ለሚተመኑ የግዥ ሥራዎች እንደሆነ ሃጂ ጠቁመዋል። በተጨማሪም የግዥ ዕቅድ፣ የግዥ ዕቅድ ማስጀመር፣ የጨረታ ሂደትን ማስተዳደር፣ አሸናፊዎችን መግለጽ፣ ውል መፈራረምና የውል አስተዳደር ሥራዎችን ማከናወን ይችላል ተብሏል።
ሲስተሙን (ሥርዓቱን) የሚያለማውን አማካሪ ድርጅት ከመቅጠር ጀምሮ ሥርዓቱ እንዲለማና ለተቋማት ምቹ እንዲሆን ለማስቻል በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፣ በተለይ የሲስተም መፈተሽ ሥራው ለሙከራ ትግበራ ከተመረጡ ተቋማት ባለሙያዎች ጋር ለስድስት ወራት ተከናውኗል ነው የተባለው። በፍተሻ ሥራው የግዥ ዕቅድ፣ የግዥ ዕቅድ ማስጀመር፣ ግዥ፣ ጨረታ፣ ሃራጅ፣ ውል፣ ውል መፈራረምና የውል አስተዳደር ስርዓቶችን በተግባር መፈተሽ ተችሏል። የነበረው የሲስተም ፍተሻ ሥራው በርካታ ልምድ የተገኘበት፣ የሲስተሙ ተጠቃሚዎች በቀላሉ ሥርዓቱን መጠቀም እንዲችሉ ቀላልና ግልፅ እንዲሆን የተደረገበት ሲሆን፣ ሲስተሙ ከበርካታ ተቋማት ሲስተሞች ጋር ቅንጅት ስለሚኖረው መረጃን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበት መሆኑ ታውቋል።
ከኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ጋር ተያያዞ የሚነሱ የደህንነት ስጋቶችን ለመቀነስ የኹሉም ተቋማት ሰርቨር ማዕከላዊ በሆነ መልኩ በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የሚኖር በመሆኑ፣ የአገሪቷን ግዥ በአንድ ቋት ለመያዝ ከማስቻሉም ባሻገር አስተማማኝና ከስጋት ነጻ እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል ተብሎለታል።
ኤጀንሲው አዲስ የሚተገብረውን ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት በመመሪያ ለማስተዳደር፣ ሥርዓቱ ተግባራዊ የሚደረግበትን መመሪያ ማዘጋጀቱን ሃጂ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። መመሪያው ተዘጋጅቶ ለጠቅላይ አቃቢ ሕግ ቀርቦ እየተመረመረ እንደሆነና በቅርቡ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዓመታዊ በጀቷ 60 በመቶ የሚሆነውን የምታወጣው ለግዥ መሆኑን የጠቆሙት ሃጂ፣ እስካሁን በነበረው አሠራር ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት ሥራ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር ብለዋል። የሚንስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ካጸደቀው የ561 ነጥብ ሰባት ቢሊየኑ የ2014 በጀት ውስጥ 300 ቢሊየን ያክሉ ለግዥ የሚውል እንደሆነ ሃጂ ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013


