የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን መቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ መዘጋጀቱ ተገለጸ

0
1296

የጤና እና ጤና ነክ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን መቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በጤና ሚኒስቴር መዘጋጀቱን የሚኒስቴሩ የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክትር አብዱልዓዚዝ ሱዉዲ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት በመድኃኒት ክብካቤና ቁጥጥር ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ሥር ያለውን አዋጅ 661/2012 በመለየት በጤና ሚኒስቴር ሥር ሆኖ እንዲተዳደር የሚያስችል አዲስ አዋጅ ነው ተብሏል።
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የጤና ጉዳዮች ተገቢው የሕግ ማዕቀፍ ስለሌላቸው ረቂቁ እንደሚያስልግ ገልጾ፣ ማዕቀፉን ጤና እና ጤና ነክ ተቋማት ላይ በማተኮር የባለሙያዎች ድጋፍ፣ ብቃትና ምዘናን እንዲሁም የስነምግባር ጉዳዮችን ወደ ጤና ሚኒስቴር አስተላልፏል።

ጤናና ጤና ነክ ቁጥጥር ቀጥታ ከባለሥልጣኑ ወደ ጤና ሚኒስቴር የተላለፈ እንደመሆኑ መጠን፣ የፍቃድና የሥነ-ምግባር ጉዳዩ የሕግ ማዕቀፍ ስለሚያስፈልገው በአዲሱ አዋጅ በማካተት አዲስ የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ የተሰራ ነው ተብሏል።

አዋጁ የሚሻሻል ሳይሆን አዲስ የሚወጣ መሆኑን ነው አብዱልዓዚዝ የገለጹት። በአዋጅ 661 ላይ ሁሉንም አጠቃሎ ይዞ በባለሥልጣኑ ተቋቋመ የነበረው ነገር ግን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሆኖ 2011 ላይ ራሱን ችሎ ሲቋቋም፣ የተቀሩትን የቁጥጥር ስራዎች ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰጥቷል። 661 በሙሉ ተሽሮ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ፈርሶ ጤና ሚኒስቴር ይስራቸው የተባሉ ጉዳዮች አሉ። እነዚህን ጉዳዮች በመያዝ ደግሞ ጤና ሚኒስቴር አዲስ የሕግ ማዕቀፍ የማውጣት እና ረቂቅ የማዘጋጀት ሥራ ሰርቷል ሲሉ አብዱልዓዚዝ ገልጸዋል።

የጤና ቁጥጥር አዋጅ ሥር፣ ጤና ማለት የጤና ባለሙያን የሚያካትት ሲሆን፣ የጤና ነክ ተቋማት ሲባል ደግሞ በቀጥታ የጤና አገልግሎት የማይሰጡ የተለያዩ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ዩኒቨርስቲዎችንና ከጤና ጋር በተዘዋዋሪ የሚገናኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ያካትታል ሲሉ አብዱልዓዚዝ ተናግረዋል።

ለምሳሌ ዩኒቨርስቲዎችን ብንመለከት የምኝታ አገልግሎት፣ ምግብ አቅርቦት እና የመጸዳጃ ቤት ንጽህናዎች ከጤና አጠባበቅ ጋር የተያያዙ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ አገልግሎቶች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ ስምንት ክፍሎችና 36 አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ ረቂቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደሚገኝ አብዱልዓዚዝ ጠቁመዋል። በመጀመሪያ ክፍል ላይ የተቀመጠው የረቂቁን ተፈጻሚነት ወሰን፣ በአዋጁ ውስጥ ትርጉምና ርዕሶች የያዘ ነው። ሁለተኛ ክፍል ላይ፣ የአስፈጻሚውና የተቆጣጣሪው ሥልጣንና ተግባር በሚመለከት የተቀመጠ ግዴታ ነው።

በክፍል ሶስት የተቀመጠው ስለጤና አገልግሎት በተመለከተ የተቋሙ አስተዳደርና ቁጥጥርን ያትታል። በዚህ ላይ የተቋማት ኃላፊነት፣ የጤና ተቋም ምዝገባና ፍቃድ፣ የጤና ተቋምና አገልግሎት ደረጃ፣ ማስታወቂያ የማስተላለፍ ሥራዎች፣ ቅድመና ድህረምረቃ ተማሪዎችን በተመለከተ፣ የጤና አገልግሎት እንዴት እንደሚሰጥ እና የድንገተኛ ህክምና፣ ሪፈራል ተደጋጋፊና አማራጭ የህክምና አገልግሎት መስጫ ቦታዎችን የሚቆጣጠር ክፍል አለው።

የአካል ክፍሎች እና ሕብረ-ህዋሳት ልገሳና ንቅለ ተከላ በተመለከተ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችልበት ሁኔታ በዚሁ ክፍል ተካቷል።
ክፍል አራት ስር ስለጤና ባለሙያዎች አስተዳደር ቁጥጥር ያትታል። በዋናነት ደግሞ በዚህ ሥር የጤና ባለሙያዎች ቁጥጥር፣ መረጃ፣ ስለሙያ ፍቃድ አሰጣጥ፣ የተደጋጋፊና የአማራጭ ህክምና ባለሙያን በተመለከተ እና የጤና ባለሙያ ብቃት ምዘና(ፈተና) ያካትታል። ከዚህ በተጨማሪም የህክምና ስህተት መኖር እና አለመኖሩን የሚከታተል የሥነ-ምግባር ኮሚቴ ያለው ክፍል ነው።
ክፍል አምስት ጤና ነክ ተቋማት ላይ የሚደረግ የጤና አጠባበቅ ቁጥጥርና ግዴታዎችን የሚያስቀምጥ ነው።

ክፍል ስድስት በዝርዝር ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የሥራ አካባቢዎች ጤንነት እና ደህንነት የሚለይ ነው። ከእነዚህ የሥራ ቦታዎች መካከል አደገኛ ኬሚካል የሚወገድባቸው፣ የግንባታ ሥራዎች፣ የቆሻሻ አወጋገድ እና የመጸዳጃ ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመታጠቢያ ስፍራዎችና የመዋኛ ገንዳዎች ንጽህና የመቆጣጠር ተግባርን የያዘ ነው።
ክፍል ሰባት አስተዳደራዊ እርምጃ በምን መልኩ እንደሚወሰድ እና ቅጣቶችን አስቀምጧል።

ክፍል ስምንት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ናቸው። ማንኛውም ተቋም ለሚያከናውነው ተግባር ግዴታ እንዳለበት የሚያስቀምጥ እና ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የሚለውን አካቷል።
ከዚህ በፊት ይፋ የተደረገው የጤና አስተዳደር አዋጅ የጤና አገልግሎት የሚተዳደርበት ሲሆን፣ ይህ ደግሞ አገልግሎቱ የሚተዳደርበትን ሥርዓት ቁጥጥር የሚያደርግ ነው ሲሉ አብዱልአዚዝ ለአዲስ ማለዳ አስታውሰዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here