በጋዜጠኝነት ሙያ ለበርካታ አመታት አገራቸውን ያገለገሉት ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ በታሪክ ተመራማሪነታቸውም ይታወቃሉ። መጻሕፍትን ለአንባቢያን ከማቅረብ ጀምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየቀረቡ ያለፍርሀት ሐሳባቸውን በመግለፅ የብዙዎችን ትኩረት ስበዋል። በቅርቡ ታስረው የነበሩት እኚህ አንጋፋ ምሁር ጋር አዲስ ማለዳ ቆይታ አድርጋለች።
በቅድሚያ ስለ እስር ቤት ቆይታዎና ስታሰሩበት ምክንያት ትንሽ ቢነግሩን?
አንድ ወር ሙሉ ታሰሬ ነው የተፈታሁት። እስር ቤቱ ስገባ እስረኞች በጣም በአክብሮት ነው የተቀበሉኝ። እስክወጣ ድረስ በእንክብካቤ ይዘው ነው የበኩላቸውን ያደረጉልኝ። አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች በክፉ አይን ያዩኝ ነበር እንጂ ምንም አይነት ድብደባ አልደረሰብኝም። ከቤተሰቦቼ መጀመሪያ አንድ ሰው ተፈቅዶለት ይጠይቀኝ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይ እንደሌላው ሦስት ሰው ተፈቅዶ በየተራ ያገኙኝ ነበር። በዚህ ሁኔታ ቆይቼ በ4 ሺሕ ብር ዋስ ወጣሁ።
የቀረበብኝ ክስ ሆኖ ባይሰጠኝም በጥቅሉ ከሌሎች ጋር የቀረበው ዝርዝሩ ሰፊ ነው። “በሕቡዕ ተደራጅተሃል፤ የአማራ ደም ደሜ ነው ብለሃል፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ ዝም አንልም ብለሃል፤ ከሌሎች ጋር ተራጅተህ ሕገ-መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሞክረሃል፤ ወረቀት ለመበተን ተዘጋጅተሃል።” የሚሉትን ክሶች ችሎት ላይ ፖሊስ አቅርቦ አሳይቷል። ለወደፊት የታዲዮስ ታንቱ ተሳታፊነት ብለው በግል ክስ ካቀረቡብኝ ዝርዝሩ የሚታወቅ ይሆናል።
ወደ ምርጫው ጉዳይ እንግባና የምርጫ ሂደቱን እንዴት ይገመግሙታል?
ምርጫውን እኔ ከመነሻውም አልደገፍኩትም። ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የሽግግር መንግሥት መቋቋም ነበረበት የሚል የራሴ አቋም ነበረኝ። ሕገ-መንግሥት ታጥፎና ታግዶ ሌላ እንዲቀረፅ፣ ተግባራዊ ሳይደረጉ የቆዩት ከዓለም አቀፉ የሠብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የተወሰዱት ውስጡ ያሉ ጠቃሚ የሆኑ አንቀፆች ቀርተው የክፍሌ ወዳጆ ሕገ-መንግሥት እንዲሰረዝ ማድረግ ያስፈልጋል ብዬ ነበር። ሕዝቡ የሚቀበለው አዲስ ሕገ-መንግሥት ተቀርፆ ወደፊት ኢትዮጵያ የምትመራበት ሥርዐት የጎሳ ሥርአትን ያስወገደ መሆን አለበት።
ሕዝብ በፈለገበት መኖር መቻሉን የሚያረጋግጥ፣ ፌደራላዊም ይሁን አሃዳዊ፣ ሕዝብ የፈለገው መሆን አለበት። ይህ ከሆነ በኋላ ነበር ምርጫ መካሄድ የነበረበት። ለዚህ ነው ከመነሻው ምርጫውን ያልደገፍኩት። እንዴት በዚህ ጊዜ ምርጫ ይደረጋል? ሰው በአደባባይ በሚገደልበት ሰዓት፣ በተለይ የአማራ ልጆች በየተገኙበት እየታደኑ በሚገደሉበት በዚህ ወቅት ምርጫ ማድረግ አንገብጋቢ ሆኖ ነው? የሽግግር መንግስት ለማድረግ ሁሉም የፈራው ለምንድን ነው? በተለይ ተቃዋሚ ነን ብለው አዲስ ሥርዓት እንዲመጣ እንታገላለን የሚሉት ምን አይነት አስተሳሰብ ኖሯቸው ነው ምርጫ ውስጥ አሁን የሚገቡት። ግድ ማድረግ ካስፈለገ ሥልጣን ላይ ያለው ብቻዬን ተመርጫለሁ ብሎ መቆየት ይችላል። ተሰባስበው ያለውን መታገል ሲኖርባቸው እሱ ባዘጋጀው መንገድ ገብተው ለውድድር መቅረብ ምን ማለት ነው። አላማቸው በአጭሩ የእንጀራ ፓርላማ ለማቋቋም ነው። ሥራ አጦች ተወዳድረው ገንዘብ ለማግኘት ነው። የሙስና መንግሥትና የእንጀራ ፓርላማ አቋቁመው የነበረውን ሥርዓት ለማስቀጠልና ሕጋዊ ሥርዓት ለማስያዝ ታስቦ ነው። በዚህ ምርጫ ውስጥ የገቡት ሁሉም የታሪክ ተወቃሾች ናቸው። አገር ወዳዶች ናቸው ለማለት አያስችልም። የግል ፍላጎታቸውን እንጂ አገራዊ ጥቅምን የማያስቀድሙ ናቸው። የሁሉንም ፓርቲዎች ተወካዮች ካየን ዶክተር ኢንጂነር እየተባሉ ይጠቀሳሉ እንጂ እውቀት አላቸው ማለት አይቻልም። እውቀት ቢኖራቸው በዚህ ጊዜ ምረጡን አይሉም ነበር። ከቀን ወደ ቀን እየወደቀችና እየሞተች ባለች አገር ላይ ራስን ምረጡኝ ብሎ ማዘጋጀት ከእንጀራ ፍለጋ ውጭ ሊሆን አይችልም። ስለምርጫው ያለኝ አቋሜ አይቀየርም። ያለው ሥርዓት አካሄዱን እንዲያስተካክል መቃወም እንጂ፣ ባለው መረብ ውስጥ ገብቼ ሎሌ ሆኜ መመሪያውን እየተቀበልኩ ሥርኣቱን ዲሞክራሲያዊ ለማስመሰል መተባበር የለብኝም ብዬ ተሳተፍ ተብሎ ለቀረቡልኝ ጥያቄ እምቢ ብዬ ቀርቻለሁ። አሁን ያለው ስርዓት በይዘት ስላልተለወጠ ትንሽ ለውጥ ብቻ ነው ያሳየው ብዬ ነው ከመነሻውም አልደግፈውም የምለው። በኔ አመለካከት የምርጫው አካሄድ ትክክል አይደለም። ሰው እየተገደለ ምርጫ መባሉ ለሟቾች የተስካር ድግስ መሆኑ ነው? መጀመሪያ የአገር ፀጥታና ድንበር ተከብሮ ሁሉም ሲረጋጋ ነው እንጂ አሁን መደረግ አልነበረበትም። አካሄዱ ወንጀል ስለሆነ ተሳታፊዎቹ በታሪክ ተጠያቂ ይሆናሉ።
ምርጫው መደረጉ ስለማይቀር ምን ይሁን ይላሉ?
ምርጫው ተካሄደም አልተካሄደም ብዙ ገንዘብ ማፍሰሱ ወንጀል ነው። ሂደቱ በወንጀል ላይ ወንጀልን የሚያጠናክር ስለሆነ ሊኮነኑ ይገባል። ገዢው ፓርቲ ሥልጣን ላይ ስላለ የበለጠ የሚወቀሱት ተፎካካሪዎቹ ናቸው። ሲያጅቡ ቆይተው በስተመጨረሻ አንዳንድ አካሄዶች ተበላሽተዋል ይላሉ። ቢሳካላቸውና ቢመረጡ ዛሬ ነው ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ያየችው ብለው ፓርላማ ገብተው እንጀራ ሊበሉ ነው። ከከሸፈባቸውና ካልተመረጡ ደግሞ ለመኮነን ነው። አያያዙ ያላማራቸው ትንንሽ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ተበደልን ማለት ጀምረዋል። መጀመሪያ ውሎ ለመግባት ዋስትና በሌለበት ወቅት መጀመሪያውን ለምን ገቡ። ምርጫ ውስጥ የሚገባው ሰላም ሲኖር ነው።
አሁን ያለው የሰላም ሁኔታ ከምርጫው በኋላ የሚሻሻል ወይስ የሚብስበት ይመስሎታል?
ከምርጫ በኋላ የሚብስበት ይመስለኛል። ዋና ዋናዎቹ ፓርቲዎች ሕዝቡ ሕይወቱ ተለውጦ ማየት ፍላጎታቸው ስላልሆነ ፍርፋሪ ከተጣለላቸው ሊረጋጋ ይችል ይሆናል። ሁሉም በዜሮ ከወጡ ግን ሰላም አይኖርም።
የመሸናነፍ ባህላችንን እንዴት ይገመግሙታል?
የመሸነፍ ባህላችን ገና አልዳበረም። የመሸነፍ ፍላጎት ጭራሽ የለንም። ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ የለም። አብዛኞቹ ፖለቲካን የገንዘብ ምንጭ አድርገው ነው የሚያዩት። ተቃዋሚዎች ገና ካሁኑ ክስ ጀምረዋል። ሁሉ ነገር የልጅ ሥራ ነው የሚመስለው። ሁሉም ለማሸነፍ ቋምጧል። እንደዘንድሮ በርካቶች አሰፍስፈው ለሥልጣን ሲስገበገቡ አይቼ አላውቅም። እንጀራ የሚበላው በፖለቲካ ብቻ ይመስል እየተረባረቡ ነው።
የዘንድሮው ምርጫ ከባለፉት አምስቱ በምን ይለያል?
የዘንድሮው ካለፉት በይዘትም በቅርጽም የተለየ አይደለም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማሸነፍና መሸነፍ የለም። በስልት በዘዴ አንዱ ሌላውን ገፍቶ በመጥለፍ ሥልጣን ላይ የሚወጣበት ታሪክ ነው ያለን። ወያኔ ካካሄዳቸው የተለየ ነው ያሁኑ የምልበት ምክንያት ባይኖረኝም፣ ሰላም በሌለበት የሚካሄድ መሆኑ ይለየዋል።
በአጠቃላይ፣ ዋጋ የሌለው ምርጫ ነው ብዬ መደምደም እችላለሁ። ኢትዮጵያ ትቅደም ብለን ሰው ማዳን ይቀድማል። የውሸት ምርጫ ተደርጎ የሙስና መንግሥት መቋቋም የለበትም። ከሁሉም ኢትዮጵያን ማዳን ይቀድማል። ለሥልጣን የሚሮጡት ሁሉ ወደ ህሊናቸው ሊመለሱ ይገባል።
ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013



