በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች ከግመል ጋር ግንኙነት ያለው ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገለፀ

0
500

በኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች ከግመል ጋር ግንኙነት አለው የተባለና ለጊዜው ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገልጿል። ወረርሽኙ በግመሎች ላይ መከሰቱን እና ከወርሽኙ ጋር በተያያዘ በሰዎች ላይም ምልክቶች መከሰታቸውን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጹን አል ዐይን አማርኛ ዘግቧል፡፡ ወረርሽኙ የታወቀው መንስኤው ባልታወቀ የግመሎች ሞት ሲሆን፣ የበሽታ ምልክት የታየባቸው ሰዎችም መኖራቸው ተገልጿል፡፡ የበሽታውን መንስኤ ለመለየት ከግብርና ሚኒስቴር እና በእንስሳት ጤና ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ስፍራው የባለሙያዎች ቡድን መሰማራቱ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የግመሎቹ ናሙና ተወስዶ ‘ናህሊክ’ ወደተባለ የእንስሳት ህክምና ላቦራቶሪ ተልኮ መንስኤው እየተጣራ መሆንኑም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ከሰዎች ላይ ናሙና በመውሰድ መንስኤው ምንድነው የሚለውን ለመለየት ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ አስታውቋል። በሰዎች ላይ ከኢንፉሎንዛ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ምልክት መታየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በሽታውም ሳዑዲ አረቢያ አካባቢ በብዛት የሚገኘው “ሜርሲኮቭ” የተባለ በሽታ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳለም ተነግሯል፡፡ “ምልክቶቹ በሰዎች ላይ ተስተውለዋል” ያለው ኢንስቲትዩት፣ ስንት ሰዎች ላይ ተከስቷል የሚለው ላይ “የላቦራቶሪ ምርመራ ካደረኩ በኋላ ነው ይፋ የማደርገው” ብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች ከግመል ጋር ግንኙነት ያለው ወረርሽኝ መከሰቱን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል። እስከ ሰኔ 5/2013 በደረሰው ሪፖርትም በኦሮሚያ ክልል 158 ሰዎች፣ በሶማሌ ክልል 40 ሰዎች ላይ በድምሩ 198 ሰዎች ላይ ወረርሽኙ መከሰቱን አስታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ 40 ሰዎች ለህክምና ሆስፒታል ገብተው የህክምና ክትትል ማድረጋቸውን እና 35 ሰዎች ደግሞ ድነው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ፣ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዝ እስካሁን የተመዘገበ ሞት የለም ብሏል። ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት፣ ተቅማጥ እና ማስመለስ የበሽታው ምልክቶች ናቸው ያለው ድርጅቱ፣ የበሽታውን መንስኤ ለመለየት የላቦራቶሪ ምርመራዎች እየተካሄዱ ነው ብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here