የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ፣ የኢፌዴሪ ከፍተኛ ልኡካን እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመርቆ በይፋ ሥራውን ጀመረ ፡፡ በዲፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ በሶማሊላንድ 30 በመቶ እና በኢትዮጵያ 19 በመቶ ሼር የተያዘው የበርበራ ተርሚናል ኮሪዶር፣ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት 500 ሺሕ ኮንቴይነሮችን መያዝ የሚችል ተርሚናል እንደሆነና በዓመት 1ሚሊየን ኮንቴይነሮችን ማስተናገድ ይችላል ተብሏል።
ወደቡ ዘመናዊ ክሬኖች የተገጠሙለት ሲሆን፣ ከዛሬ ጀምሮ ግዙፍ መርከቦችን በማስተናገድ ለቀጠናው በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተገልጿል። የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለፁት፣ የበርበራ ወደብ የመጀመሪያው ዙር ተርሚናል ስራ መጀመር በቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደትን ከፍ እንደሚያደርግና በተለይ በየጊዜው እያደገ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማሳለጥ የሚያስችል በመሆኑ በበርበራ ወደብ ላይ ለሚደረገው ሥራ ኢትዮጵያ ትካፈላለች ብለዋል። ኢትዮጵያ በተለይ የሱማሊ ክልል በወደቡ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ከበርበራ -ጅግጅጋ- ድሬደዋ-ኤረር- ሚኤሶ መንገድ በመገንባት ጅግጅጋንና ድሬዳዋን ከበርበራ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ የኮንቴይነር መዳራሻ ይሆናሉ ብለዋል። በመጨረሻም የበርበራ ወደብ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ኮንቴይነሮችን ከመርከብ በማራገፍ ሥራውን በይፋ ጀምሯል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013


