በሱማሌ እና አፋር ክልል ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ በመባባሱ ምርጫ ለማካሄድ ፈታኝ መሆኑ ተገለጸ። በሱማሌ እና አፋር ክልል ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም የዜጎች አለመረጋጋትና መፈናቀል በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን የሱማሌ ክልል አስተዳደር ጽኅፈት ቤት ምክትል ኃላፊ መሐመድ ሮብሌ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በአፋር ክልል የሚገኙ ሚሊሻዎች የፈጠሩት የዜጎችን ሰላም የማወክ እና ማፈናቀል ተግባር ቀጥሏል ያሉት መሐመድ፣ የሱማሌ ክልል ተወላጆች የሚገኙባትን አዳይቱ የምትባለውን ቦታ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ማደረጋቸውን ገልጸዋል። አፋር ክልል የሚገኙ ሚሊሻዎች ከተማዋን በማቃጠል በአካባቢው የሚገኘው ማሕበረሰብ እንዲሰደድ እና እንዲፈናቀል አድርገዋል ሲሉ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የሱማሌ ተወላጆች የሚኖሩባት ይህች አዳይቱ የተባለችው ስፍራ በኹለቱ ክልሎች ድንበር ያለች በመሆኗ በአፋር ክልል ሚሊሻዎች ተይዛ ነዋሪዎቹ ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ነው መሐመድ የገለጹት። በአሁኑ ሰዓት የአፋር ሚሊሻዎች ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ያደረጓት በመሆኑ፣ የነዋሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በጣም ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
‹‹በጣም አስቸጋሪ እና ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ችግሩን ለማስቆም ተቸግረናል›› ሲሉ መሐመድ ገልጸዋል። ሰላም የሚፈልግ ማሕበረሰብ ቢኖርም በኹለቱም ክልሎች ተመሳሳይ ሰላም የሚፈልግ ማሕበረሰብ ባለመኖሩ፣ አንዱ ሰላም አፍራሽ አንዱ ሰላም ፈላጊ እየሆነ መምጣቱ ለችግሩ መባባስ ዋና ምክንያት ነው ብለዋል። የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ደርሶ ሰላም እንዲያሰፍን በተደጋጋሚ ጥሪ ብናቀርብም፣ በሦስት ቀን ውስጥ እንደርሳለን ብለውን የነበረ ቢሆንም፣ ዘግይተው መጥተው አልቻልንም የሚል ምላሽ ሰጥተውናል ብለዋል።
መሐመድ እንደሚሉት ከሆነ ‹‹በኛ በኩል በጣም ከብዶናል፤ መከላከያ ሠራዊትም ቢሆን ሚሊሻዎቹን ማስወጣት አልቻልንም ብሎናል›› ሲሉ ተናግረዋል።
መጀመሪያ በአፋር ሚሊሻዎች ከተማዋ ስትወረር መከላከያ ሠራዊት የነበረ ቢሆንም፣ ምንም ማድረግ ሳይችሉ ሚሊሻዎቹ ሙሉ በሙሉ አካባቢውን በመውረር ቤቶች እና ከተማዋን አቃጥለዋል ሲሉ ገልጸዋል። የመከላከያ ሠራዊት መፍትሔ እናመጣለን ብሎን ነበር፣ ግን ምንም አይነት እርዳታ እያደረገ ስላልሆነ ነዋሪዎች በጣም ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ነው ብለዋል። እንደ መሐመድ ገለጻ ከሆነ ሱማሌ ክልል ምርጫ የሚደረገው ጷጉሜ 1 ቢሆንም፣ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ በመሆኑ ምርጫ ለማካሄድ ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የምርጫ ቅስቀሳ የተጀመረ ሰሞን በበርካታ አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ግን በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተደረገው ምርጫ ጉዳይ የአብዛኛውን ትኩረት በመሳቡ ምክንያት ቅስቀሳ እየተደረገ አለመሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ምርጫው እስከሚደርስ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ምንም አይነት ክልከላ አለመደረጉን የገለጹት መሐመድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን ጊዜአቸውን እየተጠቀሙበት አይደለም ሲሉ አንሰተዋል።
ሌሎች አካባቢዎች የተደረገው ምርጫ ፍትሃዊነትን የታየበት በመሆኑ ሕዝቡ ለመምረጥ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየበት ነበር። ነገር ግን ሰላም በሌለባቸው አካባቢዎች እየደረሰ ያለው መፈናቀል፣ ግጭትና አለመረጋጋት ለመምረጥ የተነቃቃውን ሕዝብ እያዳከመው ይገኛል ሲሉ መሐመድ ተናግረዋል። እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር በምርጫው ጥሩ የሆነ ፉክክር ይኖራል ተብሎ ይታሰባል። ሕዝቡም ለመምረጥ ተዘጋጅቶ በቂ መረጃ ማግኘቱንና አንድ ፓርቲ ብቻ የገዢነት ቦታውን እንደማይወስድ ሕዝቡ ግንዛቤ እንዳለው መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ነገር ግን ይላሉ መሐመድ፣ አዳይቱ የተባለው አካባቢው ምርጫ ከማይካሄድባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ በሱማሌ አካባቢ ሊመርጥ የተዘጋጀው ሕዝብ እህትና ወንድሞቹ እየተፈናቀሉ ምርጫ ለማካሄድ የሥነ ልቦና ዝግጅቱ እንዳይቀንስ ስጋት እንዳላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሱማሌ አካባቢ ማሕበረሰብ እና በአካባቢው የሚገኙ ተቋማት ለተፈናቃዮች እርዳታ እያደረጉ ይገኛሉ። ክልሉ በአቅሙ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አንስተዋል። በተጨማሪም በኹለቱ ክልሎች መካከል የተደረጉ ድርድሮች ምንም መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም ብለዋል። ከተማዋ ውስጥ ያሉ የሱማሌ ክልል ተወላጆችን አፈናቅሎ የከፋ ሁኔታ ውስጥ በመክተት ሌላ ኃይል ከተማዋን ሲቆጣጠር እንደአገር ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነን ሲሉ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በጉዳዩ ላይ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ያለውን አስተያየት ለማካተት አዲስ ማለዳ ጥረት ብታደርግም ጋዜጣው ለኅትመት እስከተላከበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013



