የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሐዋሳ ከተማ የሚገኙ 12ዐ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው፤ ውሎ አዳራቸውን በጐዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ድጋፍ ወደ ሚያገኙበት ማዕከል የማስገባት ስነ-ስርዓት ማከናወኑ ተገለፀ፡፡
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በእለቱ የሜሪ ጆይ የወጣቶችና ህጻናት ማእከልን በመጎብኝት ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያንን ለማቋቋም በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ የግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የድጋፍ ስራው ስኬታማ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት አያደረገ እንደሚገኝም ዶ/ር ኤርጎጌ ገልፀዋል፡፡
የማእከሉ መስራችና የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ዋና ሃላፊ የሆኑት ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከ1994 ጀምሮ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካማ አረጋዊያንንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን የተለያዩ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው በእለቱም የተከናወነው 120 ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውና ውሎ አዳራቸውን በጐዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ለድጋፍና እንክብካቤ ወደ ማዕከል የማስገባት ሥነስርዓት የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በሬሶ እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ደጋፊ የሌላቸውና ውሎ አዳራቸውን በጐዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ለመደገፍ በድርጅቱ በኩል ለተከናወኑ የበጎ አድራጎት ስራዎች ምስጋናቸውን በማቅረብ መልእክታቸውን ማስተላለፋቸውን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡



