የክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ሥርዓተ-ቀብር በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በዛሬው እለት ከቀኑ ዘጠን ላይ ተፈፅሟል።
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።
አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ በመባል የሚታወቁት ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ከሀገር ባለውለታነት አልፈው ለሰው ልጆች ትልቅ ክብርን በመስጠት በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ላጡ እናትም አባትም ሆነው ሰው ከወደቀበት ቀና እንዲል ያደረጉ ታላቅ እናት ነበሩ።
አበበች ጎበና በበጎ አድራጎት ስራቸው እውቅናን ያተረፉ፣ የአፍሪካዋ “ማዘር ትሬዛ” የሚል ስያሜን ያገኙ እና በልጆቻቸውም “እዳዬ” ተብለው ታላቅ እናት ነበሩ። ላለፉት ከ41 ዓመታት በላይም ወላጅ አልባ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችን ተንከባክበውና አሳድገው ለቁም ነገር ማብቃታቸውም የሚታወቅ ነው።



