በሕግ አግባብና በፍትሕ መንገድ ላይ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ ለመውጣት ሲጣጣሩ የነበሩ 42 ተጠርጣሪ የህወሓት አባላት ላይ በዚህ ሳምንት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ጸጋዬ አስታወቁ፡፡
ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ 42ቱ ተጠርጣሪ የህወሓት አባላት በቀዳሚ ምርመራና በዋና ምርመራቸው ወቅት ጉዳያቸውን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በተለይም ያልሆኑ ሰበባ ሰበቦችን በመቃረም የፍርድ ሂደቱ ዘገየ ለማስባል መሞከራቸውን ያመለከቱት አቶ ፈቃዱ ፣ በሕግ አግባብና በፍትህ መንገድ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ እንወጣለን በሚል ሒሳቦችን ሰርተው ከእስር ለመውጣትም ሲጣጣሩ ቆይተዋል ብለዋል ፡፡
ነገር ግን ምርመራው በጣም ከታሰበው በላይ በፍጥነት በመጠናቀቁ ይህ ስሌታቸው እንዳልሰራ አመልክተዋል ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሰሩት ልክ ሕግ ተገቢውን ፍርድ ይሰጣቸዋል ያሉት አቶ ፈቃዱ፤ በቀጣዩ ሳምንት ተጠርጣሪዎቹ ለክስ እንደሚቀርቡ አመልክተዋል ፡፡
ክሱ የወንጀል ክስ በመሆኑም ፍጥነቱ ምን ያህል ተቀናጅቶ እንደተሰራበት የሚያመላክትም ነው ብለዋል ፡፡ በብዛት በምርመራና በሰበባሰበብ እንዲሁም በምስክር ማሰማት ሂደት ችግሮች ባያጋጥሙ ኖሮ ከዚህ ባነሰ ጊዜም ክሱ ይመሰረት እንደነበር ማስታወቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡



