በሶማሌ ክልል ለህወሓት ቡድን በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ 28 ግለሰቦችና ንብረቶቻቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በሶማሌ ክልል የሚገኙ የህመሓት ቡድን ተላላኪዎች ለቡድኑ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለፁት የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ረ/ኮሚሽነር መሀመድ አሊ ሐሰን፤ 28 ግለሰቦች፣ 10 የሲኖትራክ መኪና እና ሌሎች ንብረቶቻቸው በህብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ በተደረገ ከፍተኛ ክትትል መያዛቸውን ገልፀዋል።
ግለሰቦቹ በክልሉ ብጥብጥ ለማስነሳት አቅደው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም ረ/ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
ለዚህ ተግባር እንዲያብሩ ከዚህ ቀደም የነበረው አመራር አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ የክልሉ ተወላጆችን በማስተባበር ሲሰሩ ቆይተዋልም ብለዋል።
በተለይ የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ፖሊስ ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ወደ ግዳጅ ማምራቱን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ የህወሓት ተላላኪዊች ይህንን ሀገራዊ ሀላፊነት ሌላ ቅጥያ ስም በመስጠትና በማህበራዊ ሚዲያ ለፕሮፖጋንዳነት በመጠቀም ሂደቱን ለማስተጓጎል ሲጥሩ ነበርም ብለዋል ረ/ኮሚሽነሩ።
የክልሉ ልዩ ሀይል ፖሊስ የሀገሪቷን ሉዓላዊነት እና ህገ መንግስት ለመጠበቅ የገባውን ቃለ መሀላ ለመተግበር ዛሬም ሆነ ነገ ዝግጁ ነው ያሉት ረ/ኮሚሽነር መሀመድ አሊ ህወሓት ስርዓተ ቀብሩ እስኪፈፀም ድረስም ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመሆኑም በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ እጃቸውን በማስገባት ለጁንታው ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ግለሰቦችና በማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና ንብረቶቻቸውን በመሸሸግ እየተባበሩ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ሲሉ ረ/ኮሚሽነሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከዚህ በኋላ በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ የተገኘ ግለሰብም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ረ/ኪሚሽነሩ አሳስበዋል።





