የአዲስ አበባን ምርጫ ውጤት ያልተቀበለው ባልደራስ

0
868

የኢትዮጵያን ስድስተኛን አገራዊ ምርጫ በዋና አሳላፊነት የመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ከወቀሳ እስከ ፍርድ ቤት የሚደርስ ተቃውሞዎችን እያስተናገደ ይገኛል። ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚነሱ ወቀሳዎችን በመስማት የሚችለውን ማስተካከሉን ሲገልጽ ቆይቷል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበለትን ጥያቄና ወቀሳ ሳያስተካክል ሲቀርም ፓርቲዎች ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ያሸነፉበት ሁኔታ እንደነበረም የሚዘነጋ አይደለም።

ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ላይ በቅድመ ምርጫ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ሲገልጹ እንደነበረው ኹሉ፣ በድህረ ምርጫም የገጠማቸውን ችግር በማንሳት ቦርዱን እየወቀሱ ይገኛሉ። ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ላይ የሚያቀርቡት ወቀሳ የምርጫ ውጤት ውድቅ እስከማድረግ የሚደርሱ ናቸው።

ስደስተኛ አገራዊ ምርጫ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በመላው አገሪቱ ባይሆንም ባሳለፍነው ሰኔ 14/2013 ተካሂዷል። ሰኔ 14 በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ያልተካተቱ እና በከፊል ምርጫ የተካሄደባቸው ክልሎች አሉ። ሙሉ በሙሉ ምርጫ ያልተደረገባቸው ሱማሌ፣ ትግራይና ሐረሪ ክልል ሲሆኑ፣ በከፊል ምርጫ ከተካሄደባቸው ክልሎች መካከል አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ደቡብ ክልል ይገኙበታል። በአንጻሩ ሙሉ በሙሉ ምርጫ ከተደረገባቸው ውስጥ አዲስ አበባ አንዷ ነች።

ሰኔ 14/2013 የተካሄደውን የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ ውጤት ከግማሽ ወር በኋላ ባሳለፍነው ሐምሌ 3/2013 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሆኗል። ቦርዱ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት 547 መቀመጫዎች ካሉት ኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 465 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ተካተዋል።

የመጀመሪያ ዙር ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከ436 የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ ገዥው ብልጽግና 410 ወንበሮችን ማሸነፉን አስታውቋል። ቦርዱ በገለጸው ውጤት መሰረት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 26 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲና በግል ተወዳዳሪዎች እንደተያዙ ያሳያል።

ሙሉ በሙሉ ምርጫ በተደረገባት በአዲስ አበባ ከተማ በምርጫው ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ያገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤት፣ ብልጽግና ፓርቲ 22 መቀመጫዎችን ያገኘ ሲሆን፣ አንድ መቀመጫ አንድ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ አግኝተዋል። ቦርዱ እንዳስታወቀው ሰኔ 14 በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ፣ በአዲስ አበባ ለመምረጥ ከተመዘገቡት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን መራጮች 99 በመቶ ያክሉ መርጠዋል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ምርጫ ውጤት ከተማዋ ላይ አነጣጥሮ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን (ባልደራስ) ያስቆጣ ሆኗል። ባልደራስ በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ሰኔ 14/2013 የተካሄደውን ምርጫ እንደማይቀበለው ገልጿል። “ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በ2013 የተከናወነው 6ኛው ዙር አገር ዐቀፍ ምርጫ እርባና ቢስ እና ለአገራችን የዲሞክራሲ መሠረት ለመጣል ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ያሰናከለ እና የገዥውን ፓርቲ አምባገነናዊ ሥርዓት ያጠናከረ ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም በምርጫ ቦርድ የተገለጸውን ውጤት በሙሉ በሙሉ የማንቀበለው መሆኑን እንገልጻለን” በማለት ምርጫውን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።

ባልደራስ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበል በገለጸበት የምርጫ ሒደትና ውጤትን በተመለከተ ባወጣው ጽሑፍ “ትክክለኛ ባልሆነ እና በርካታ ሕገ ውጥ ተግባራት በተፈጸሙበት ምርጫ፣ ኲሉም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት መቀመጫዎች 100 ፐርሰንት በአንድ ፓርቲ ብቻ መሞላታቸው ምርጫውን ነጻና ፍትሐዊ አያደርገውም” ብሏል።

ባልደራስ ይህን ያለው በድህረ ምርጫ ወቅት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑን እንደ ዋና ምክንያት በማንሳት ነው። ባልደራስ ምርጫ ቦርድን “ገለልተኛ አይደለም” ብሎ የከሰሰው ፓርቲያችን፣ የቅድመ ምርጫ ሒደቱን በተመለከተ ያቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ የምርጫ ቀን ክንውንና የድህረ ምርጫ የቅሬታ አቀራረብን አስመልክቶ ለምርጫ ቦርድ ላቀረበው ቅሬታ በጎ ምላሽ አለመስጠቱን በመጥቀስ ነው። “በዚህም ምርጫ ቦርዱ ለገዢው ፓርቲ የወገነና ነጻ እና ገለልተኛ አካል አለመሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ተገንዝቤያለሁ” ብሏል።

በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የአዲስ አበባ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ሒደትን በተመለከተ ባልደራስ ባወጣው የግምገማ ውጤት መግለጫ፣ በምርጫው ቀን የገጠሙ ችግሮችን በጥናት ለይቻለሁ ብሏል።
ፓርቲው በጥናት ከለያቸው ችግሮች መካከል፣ የድምጽ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት የአደረጃጀትና አመራር ችግር የታየበት ነው ብሏል። በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያልተሰጣቸው የገዥው ፓርቲ አመራሮች ዋና አስተናባሪዎች እንደነበሩ ባልደራስ በጥናቱ ማረጋገጡን ጠቅሷል። እንደ ማስረጃነት ያቀረበውም “ኲለት የብልጽግና የክልል ምክር ቤት ዕጩዎች ከምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር አብረው ቆጠራ ሲያደርጉ አድረዋል(ምርጫ ክልል 26/27 ወረዳ 12 ምርጫ ጣቢያ 12)” የሚለውን ነው።
ባልደራስ አክሎም በምርጫ ቦርድ ፈቃድ ያልተሰጣቸውና ከታዛቢነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው የብልጽግና ፓርቲ የወጣት ሊግ፣ የሴቶች ሊግ፣ የወጣቶች ማኅበር እና የሴቶች ሊግ አደረጃጀቶች ተሳትፎ መኖር ምርጫውን ፍትሐዊነት አሳጥቶታል ብሏል። ለዚህም ችግር በምርጫ ክልል 24፣ በወረዳ 3 ምርጫ ጣቢያ 6፣ በወረዳ 3 ምርጫ ጣቢያ 19 እንደ ማስረጃ ጠቅሷል።

ባልደራስ ምርጫውን እንዳልቀበል አድርጎኛል ብሎ ያነሳው ሌላኛው ችግር፣ የፓርቲው ወኪሎች በድምጽ ቆጠራው ጊዜ ተገደው ከድምጽ መስጫ አዳራሽ እንዲወጡ መደረጋቸውን ነው።
ለዚህም እንደ ማስረጃ ያስቀመጠው፣ “በባልደራስ የተመደበው ተቀማጭ ወኪል በወቅቱ ህመም ስላጋጠመው በተንቀሳቃሽ ወኪል ተተክቶ እየተከታተለ ቆይቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቆጠራ ሲካሄድ አብረው ቆጥረው ወደ ክልል ምክር ቤት ቆጠራ ተገብቶ ውድቅ በሚደረጉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ አለመግባባት ተፈጥሮ ቅሬታ ሲያስገባ እንዲያውም መወከል አትችልም ብለው አስገድደው አስወጥተውታል። በዚህ ምርጫ ጣቢያም ወኪላችን ተገዶ እስከሚወጣበት ድረስ ባልደራስ በቁጥር እየመራ ነበር” ችግሩ የገጠመው ምርጫ ክልል 19 ወረዳ 11ምርጫ ጣቢያ 14/1 መሆኑን ፓርቲው ጠቅሷል።

እንዲሁም በድምጽ ቆጠራው ጊዜ ማጭበርበሮች መከሰታቸውን ባልደራስ በጥናቴ አደረጋጫለሁ ብሏል። ለዚህም ፓርቲው እንደ ማስረጃ ያቀረበው፣ በምርጫ ክልል 23 ወረዳ 2 ምርጫ ጣቢያ 1 በቆጠራ ወቅት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለባልደራስ የተቆጠረ ድምጽ 405፣ ለብልጽግና 259 እንደነበር ገልጿል። ውጤቱ ሲገለጽ ግን ተገልብጦ ለብልጽግና 405 ተብሎ ተለጥፏል ብሏል።
“ምርጫ ጣቢያ የተገለጸው ውጤት በትክክል የተካሄደውን ምርጫ የማይወክልና ሆን ተብሎ

ለማጭበርበር በታቀደ ሁኔታ ቃለ ጉባኤውን ውጤት ሳይገለጽ በመፈራረም የተጭበረበረ ውጤት ነው” ብሎታል። በድምጽ ቆጠራ ላይ ባልደራስ የደረሰበት ድምዳሜ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ድምጽ አልባ ወረቀቶች ለብልጽግና ፓርቲ እንዲቆጠሩ ስለመደረጋቸው፣ የባልደራስ ወኪሎች በቆጠራ ወቅት ተገደው እንዲወጡ መደረጋቸው፣ ወኪሎችን ለመቀየር ክልከላ መፈተሙ፣ በቆጠራ ወቅት ከፍተኛ የነበረውን የባልደራስ ድምጽ ውጤት በሚለጠፍበት ወቅት ለብልጽግና እና ዝቅተኛ የነበረው የብልጽግና ድምጽ ደግሞ ለባልደራስ ተቀያይሮ መሰጠቱ ማጭበርበር ስለመፈጸሙ በጥናቱ ያረጋገጣቸው እንደሆኑ ጠቁሟል።

ባልደራስ ደርሰውብኛል ካላቸው ችግሮች ውስጥ የዕጩዎች ስምና ፎቶ ተሳስቶ መቅረብ አንዱ ነው። በዚህ ችግር ላይ ፓርቲው አጋጥመውኛል ያላቸውን ቦታዎች ዘርዝሯል። በምርጫ ክልል 26/27 ለተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ያደረጋቸው ቀለብ ስዩም ሆነው ሳሉ፣ ዓለማየሁ ጎዳና(ዶ/ር) የተባሉ ግለሰብን ምርጫ ቦርድ ዕጩ እንደሆኑ አድርጎ በምርጫ ወረቀቱ ላይ ስማቸውንና ፎቷቸውን አትሞ ምርጫ እንዲካሄድ የማድረግና መራጮችን የማደናገር ሕገ ወጥ ተግባር ፈጽሟል ብሏል።

እንዲሁም በምርጫ ክልል 23 የክልል ምክር ቤት ባልደራስ ያቀረባቸው ዕጩ ስንታየሁ ቸኮል ሁነው ሳለ፣ የቀረቡት ዕጩ ደምሌ በሚል ስም እና ፎቶ ተለጥፎ የተሳሳተ ምርጫ እንዲካሄድ ተደርጓል ብሏል። በምርጫ ክልል 24 ተወዳዳሪ የሆኑት አስካለ ደምሌ በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ ፎቷቸው እንዳይወጣ መደረጉንም ፓርቲው ጠቁሟል።

ሰኔ 14 የተካሄደውን የአዲስ አበባ ምርጫ ውጤት እንደማይቀበል የገለጸው ባልደራስ ፣ ለደጋፊዎችና ለአባላቱ ለሰላማዊ ትግል እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል። ፓርቲው በምርጫ ላይ የገጠሙትን ችግሮች ወደ ፍርድ ቤት በማምራት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱን አሳውቋል።

በምርጫው የገጠሙትን ችግሮች በተለይም ምርጫ በተካሄደበት ዕለት የገጠሙትን ቅሬታዎች በሰነድ አደራጅተን 135 ሰዎች በምስክርነት አቅርበን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሰማቱን ጠቁሟል። ባልደራስ ያለውን ቅሬታ አሰባስቦ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ በሒደት ላይ እንደሚገኝና ውጤቱን ወደፊት እንደሚያሳውቅ ጠቁሟል።

ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገውን የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ውጤት አብዛኛዎቹ በምርጫው የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተቃወሙት ሲሆን፣ ምርጫው ቀድሞ ከተጠበቀው የተለየ እንደሆነም ብዙዎች ሲገልጹ ይደመጣሉ። ይሁን እንጅ የምርጫ መሪ ምርጫ ቦርድ የቻለውን ያክል ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ እንዲሆን ጥረት ማደረጉንና ነጻ ምርጫ ማካሄድን ገልጿል።

ቦርዱ ያካሄደው ምርጫ ነጻ እና ፍትሐዊ ቢሆንም በርካታ ተግዳሮቶችና ክፍተቶች እንደነበሩበት አልሸሸገም። የመጀሪያው ዙር ምርጫ በተለይ በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ችግሮች እንደነበሩም ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here