በአዲስ አበባ ከተማ ለመንገድ ግንባታ ተብሎ የተቆፈሩ ቦታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ሕብረተሰቡ ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
መንገዶች ለግንባታ ተቆፍረው በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ባለመጀመራቸው ምክንያት ሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ እንደሚገኝ ቢሮው ገልጿል። ለመንገድ ግንባታ ሥራ የተቆፈሩ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ከፍሎች ምሽት ላይ ለግንባታ ተብለው በተቆፈሩ ጉርጓዶች ውስጥ እየገቡ ለተለያዩ አደጋዎች እየተጋለጡ መሆኑን ቢሮው ጠቁሟል።
የእግረኛ መንገዶች ለግንባታ ተብለው በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሚቆፈሩ ሲሆን፣ ግንባታቸውን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የማያልቁበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ ተናግረዋል። ይህም ሁኔታ በሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት የኑሮ እቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ በመጥቀስ፣ በይበልጥም አካል ጉዳተኞች ለመኪና አደጋና ለተለያዩ ጉዳቶች ተጋላጭ እንደሚሆኑ ኃላፊው አስታውሰዋል።
የመንገድ ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቃቸው በትራንስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በከተማዋ የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዳይኖር ከሚያደርጉ መንስኤዎች መካከል የመንገድ መቆፋፈር በዋነኛነት እንደሚጠቀስም አንስተዋል።
በተጨማሪም፣ በመንገድ መቆፋፈር ምክንያት ተሳፋሪዎች ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ አንስተው፣ጊዜው የክረምት ወቅት ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ዝናብ ሲጥል የመንገዶቹ መቆፋፈር ለከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ፍሳሾች በተገቢው መንገድ በውኃ ማስተላለፊያ መስሮች ስለማይሄዱ አስፋልት ላይ ጎርፉ ስለሚተኛ አሽከርካሪዎችም አመቺ በሆነ መልኩ የትራፊክ ፍሰቱን ጠብቀው እንዳያሽከረክሩ ተግዳሮት እንደፈጠረ ጠቁመዋል። እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ፣ በተለይም ይህንን የክረምት ወቅት ተከትሎ በከተማዋ ለሚስተዋሉ የትራፊክ አደጋ መበራከት እንደ መንስኤ የመንገዶቹ መቆፋፈር ይቆጠራል ሲሉ አንስተዋል።
በክረምት ወቅት በነዋሪዎች ላይ የሚከሰቱ ቀላልና ከባድ አደጋዎች ቁጥር እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ለመሰረተ ልማት ተብለው ተጀምረው በወቅቱ ያላለቁ ግንባታዎች ዋና መንስኤ መሆናቸውን ነው። ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አደረጃጀት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለትራንስፖርት ቢሮ እንደነበር ጠቁመው፣ አሁን ላይ የመንገዶች ባለሥልጣን ራሱን የቻለ ተቋም ከሆነ ወዲህ ያለመናበብ ችግሮች እየገጠሙ ነው ብለዋል።
በዚህም የመንገድ ግንባታዎች ከመጓተታቸው አልፎ ለሕብረተሰቡ ችግር ሆነዋል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንና ትራንስፖር ቢሮ በቅንጅት ተናበው የመሥራት ሁኔታ እንደነበር ጠቅሰው ፣በግንባታዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በጋራ ይፈቱም እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም ግን ከሐምሌ 1/ 2011 ጀምሮ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ወደ ከተማ ማዘጋጃ እንደዞረ ገልጸዋል።
በመንገድ ትራንስፖርት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት መንገዶች ባለሥልጣን እንደ አንድ ተቋም ሆኖ ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር ለመሥራት ጥረት እያደረገ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በፊት ከነበረው አንጻር የቅንጅት ሥራው ክፍተት ያለበት መሆኑን ዳይሬክተሩ አምነዋል።
በቀጣይ መንገድና ትራንስፖርት የተገናኙ በመሆናቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ወደ ትራንስፖርት ቢሮ የመመለስ ሒደቱ እንደተጀመረ ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013


