በቤንሻንጉል ክልል በደረሰ ጥቃት 25 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለፀ

0
750

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ዞን ቡሊጊ ሊጉ ወረዳ ዎንቂ፣ ቦቃ፣ ውርሲቱ በተባሉ 3 ቀበሌዎች ላይ ታጣቂ ኃይል ባደረሰው ጥቃት 25 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች መፈናቀላቸውን የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ኃይል በወረዳው ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ንጹን ዜጎች ለህልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን፣ እንዲሁም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች መኖራቸውንም የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል። በታጣቂ ኃይሉ ጉዳት የደረሰባቸውና የጥቃት ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ለመሸሽ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ሠላም በማስከበር ላይ የነበረው የመካላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከለትሎ፣ ጥቃት የተሰነዘረባቸው እና የጥቃት ስጋት ውስጥ የሚከቱ ምልክቶች እያስተዋሉ ያሉ ነዋሪዎች ወደተለያዩ አጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎች እንደተፈናቀሉ ለማወቅ ተችሏል።

በክልሉ ከአራት ወራት በፊት በካማሺ ዞን በጸዳል ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመድረሱ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለንብረት መውደም መከሰት ምክንያት እደነበር ተፈናቃዩቹ አስታውሰዋል። በካማሺ ዞን በቡሊጊ ሊጉ ወረዳ ታጥቆ በሚንቀሳቀስ ኃይል ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ተፈናቅለዋል። በዚህም ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ በአጎራባች ወደሚገኙ ቦታዎች፣ ማለትም ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን መንዲ ወረዳ፣ ዳለቲ፣ ባምበቲ እንዲሁም ወደ አሶሳ መሸሻቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውሰዋል።

በነዋሪዎቹ ላይ በደረሰ ጥቃት ምክንያት የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ሠላም ለማስከበር ወደ ቦታው ገብቶ አንጻራዊ መረጋጋት መፈጠሩን የሚያስታውሱት ነዋሪዎቹ፣ አሁን ላይ መከላከያ አካባቢውን ለቆ በመውጣቱ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እየፈጸሙ አከባቢውን የስጋት ቀጠና አድርገውታል ብለዋል። ጥቃት የደረሰባቸውና ስጋት የገባቸው ነዋሪዎቹ መከላከያ ወደ አካባቢው እንዲገባ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርበው የክልሉ ልዩ ኃይል ቢላክም፣ ችግሩን መቅረፍ ግን እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በቤንሻንጉል ክልል ዎንቂ፣ ቦንቃ፣ ውርሲቱ ቀበሌዎች በደረሰው ጥቃት የተፈናቀሉ የአከባቢው ነዋሪዎች፣ የመኖሪያ ቤታቸው እና ኃብት ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደመባቸው፣ ነፍሳቸውንም ለማተረፍ በአቅራቢያቸው ውደሚገኙ አካባቢዎች መሸሻቸውን አስታውቀዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎች፣ በጊዜያዊነት በሸሹባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የአካባቢው ነዋሪ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ጎዳናዎች ላይ ተጠልለዉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ተፈናቃዮቹ በተጠለሉባቸው አከባቢዎች ከማኅበረስቡ ከሚደረግላቸው ድጋፍ ውጪ በመንግሥት በኩል ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላገኙ ጠቁመዋል። ተፈናቃዮቹ ምንም አይነት የምግብ፣ መጠለያና አልባሳት እንዲሁም በመሠረታዊነት የሚያስፈልጉ ነገሮች እርዳታ እያገኙ ባለመሆናቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።

ከተፈናቃዮች መካከል ሕፃናት፣ ሴቶች እና አቅመ ደካሞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በታጣቂ ኃይሉ ጥቃትና የጥቃት ስጋት ለተፈናቀሉ 25 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች መንግሥት አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ የተፈናቀሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙና አሁን ተጠልለው በሚገኙበት አካባቢ አንጻራዊ መረጋጋት ቢኖርም ከስጋት ነጻ እዳልሆኑ ጠቁመዋል። በመሆኑም የሚመለከው አካል ሁሉ በፍጥነት እንዲደርስላቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here