የኹለት ዓመት ጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ የተሰጣቸው ሹፈሮች ቋሚውን የመንጃ ፈቃድ ለማግኘት እንዲችሉ በኹለት ዓመት ዕድሳት የሚያደርጉበት መስፈርት ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ክትትልና ቁጥጥር፣ መንጃ ፈቃድ ለማሳደስ የጠየቀው መስፈርት፣ በተለይም ጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ ለያዙ ሹፌሮች፣ ግልጽነት የጎደለው እና አግባብነት የሌለው ነው።
የከተማ አስተዳደሩ መንጃ ፈቀድ ለማደስ ለሚመጡ ሹፌሮች ባወጣው ማስታወቂያ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች መካከል ቅሬታ ያሳደረው “የኹለት ዓመት ጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ ያላቸው አሽከርካሪዎች ለዕድሳት ወደ ተቋሙ በሚመጡበት ወቅት ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከትራፊክ ጥፋት ሪከርድ ነጻ መሆናቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል” የሚል ነው።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳሚሉት ከሆነ፣ አንድ አሽከርካሪ፣ ለዛውም ገና ጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ የያዘ፣ በኹለት ዓመት ቆይታ ውስጥ ቅጣት ሊኖርበት የማይችልበት መንገድ እንደማይኖር ነው ያመላከቱት።
ለዚህም እንደምክንያት የሚያቀርቡት በየቦታው የተመደቡ የትራፊክ ሕግ አስከባሪዎች “በቀላሉም በከባዱም ጥፋት” ስለሚቀጡና በጥፋት ሪከርድ ተመዝግቦ ስለሚያዝ፣ ቢያንስ መንጃ ፈቃዱን ለማደስ የሚጠየቀው መስፈርት ምን ዓይነት የጥፋት ሪከርድ ያለበትን የሚከለክል መሆኑን በግልጽ ሊያመላክት ይገባል ሲሉ ነው ቅሬታቸውን ያቀረቡት።
ከምንጮቻችን መካከል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ሹፌር፣ መስፈርቱ ግልጽነት የጎደለው መሆኑን አመላክቶ፣ የሚመለከተው አካል መንጃ ፈቃድ ለማደስ የሚከለክለውን መስፈርት አንድም በሪከርድ ብዛት፣ አለበለዚያም በጥፋቱ ክብደትና ቅለት ለይቶ ቢያቀርብልን የተሻለ ነው በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች አክለውም፣ የኹለት ዓመት አገልግሎት ያላቸውና በርካታ ዓመት ያገለገሉ መንጃ ፈቃድ አሳዳሽ ሹፌሮች፣ ፈቃዳቸውን ለማደስ የሚጠየቁት የብር ክፍያ መጠን ተመሳሳይ መሆን ፍትሐዊ እንዳልሆነ አንስተዋል።
መንጃ ፈቃድ ለማደስ መቅረብ ያለበትን ክፍያ በተመለከተ የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ቁጥጥር ተቋሙ ያወጣው ማስታወቂያ “የአገልግሎት ክፍያ መጠን 620 ብር መክፍል ነው” እንደሚል ተመላክቷል።
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ ብዙ አገልግሎት ላላቸውና ትንሽ አገልግሎት ላላቸው ሹፌሮች ለመንጃ ፈቃድ ማሳደሻ የሚከፈለው የክፍያ መጠን እኩል መሆን እንደሌለበት ነው።
የአዲስ ማለዳ መንጮች አክለውም፣ በተለይም ከከተማ ውጭ የሚገኙ መንገዶች የተበለሻሹ በመሆናቸው፣ አንዳድ ትራፊክ ፖሊሶች “የሹፌሩን መንጃ ፈቃድ ካዩ በኋላ፣ ዘሩን፣ ኃይማኖቱን፣ እንዲሁም ብሔሩን መሠረት በማድረግ ሆን ብለው ስለሚቀጡ”፣ እንዲሁም የኹለት ዓመት ብቻ የማሽከርከር ልምድ ያላቸው ሹፌሮች ምንም ዓይነት የቅጣት ሪከርድ ሊኖርባቸው የማይችልበት መንገድ ስለማይኖር፣ መንጃ ፈቃድ ለማደስ የተቀመጠው መስፈርት እንደገና ይታይልን ሲሉ ነው ያመላከቱት።
አዲስ ማለዳ ለቅሬታው ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ ስልክ ብትደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሽ ማግኘት ሳይሳካላት ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014



