ከቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የሚዘልቀው 20.6 ኪሎ ሜትር መንገድ ከአንድ ዓመት በፊት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ በተያዘለት ጊዜ ግንባታው ባለመጠናቀቁ ለእንግልት መዳረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ አስተዳደር ዘመን በ2010 የተጀመረው ይህ መንገድ፣ በሦሰት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚያልቅ ታሳቢ ተደርጎ፣ የሸገር ፓርክን ጨምሮ የሰመራ ኢንዱሰትሪ ፓርክን ለገነባው የቻይና ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ የተሰጠ ሲሆን፣ ኩባንያው ከቃሊቲ ቂሊንጦ እና ከቱሉ ዲምቱ ቃሊቲ የሚገነቡ ኹለት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ወደ 102 ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ገንዘብ ነበር ለመሥራት ውል ያሰረው።
ሒሩት ማስረሻ ከቂሊንጦ ወደ ቃሊቲ በሚወስድ መንገድ በተለምዶ ቃሊቲ ዓለም ባንክ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በክረምት ጭቃው በበጋ ደግሞ አቧራው እንዳስቸገራቸው እና ልጆች በተደጋጋሚ በአቧራ ምክንያት እንደሚታመሙባቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም በመንገዱ አስቸጋሪነት “የሥራ መግቢያ ሰዓትን ጠብቆ ሥራ ቦታ መድረስ የማይታሰብ ነው” ሲሉም የአካባቢው ነዋሪ ጠቁመዋል።
ከወራት በፊት መንገዱን የሚሠራው ተቋራጭ የውኃ ትቦዎች ተተክተው ስላላለቀ ሥራውን መሥራት እንዳተቸገረ መናገሩን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። ሀብታሙ ዘገየ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ በመንገዱ አለመጠናቀቅ ምክንያት “የአካባቢውን ማኅበረሰብ ማገልገል አልቻልንም፤ ከቱሉ ዲምቱ ቃሊቲ ቶታል ለመድረስ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ይፈጅብናል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ውኃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን የመሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ስዩም ቶላ ለተወሰኑ ወራት በውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት አዲስ የውኃ ትቦዎችን ለመግጠም ተቸግረው እንደነበር ጠቁመው፣ አሁን ላይ ችግሩ ተፈትቶ ሥራው እየተፋጠነ እንደሆነ ይናገራሉ። ከከተማ አስተዳደሩ በተገኘ 60 ሚሊዮን ብር 28 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገድ ሥራ በዐስር ተቋራጮች በኩል እየተከናወነ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቅሰው፣ በአሁኑ ሰዓት ሥራው ከ60 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
“ማረሚያ ቤት አካባቢ ብቻ ያሉ አንዳንድ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እና ኃይል አስተላላፊ ተሸካሚዎች ለሥራችን መሰናክል ሆነዋል፣ እነዚህ በሚመለከተው አካል ከተነሱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የመተካቱ ሥራ ይጠናቀቃል” ሲሉ ስዩም ገልጸዋል።
በተያያዘ የኮንስትራክሽን ሥራውን ሲያከናውን የነበው ሲሲሲ የውሉን ግማሽ በመቶ በውጪ ምንዛሬ፣ ቀሪውን ደግሞ በብር እንዲከፍለው ይጠብቅ የነበር ሲሆን፣ ነገር ግን ክፍያዎች በአግባቡ ሊከፈሉት ባለመቻሉ ሥራውን እንዳቆመ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኩባንያው ከፍተኛ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከቻይና ኤግዚም ባንክ ለማግኘት አቅዶት የነበረውን 50 በመቶ የሚሆነውን የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሉ ሥራው ለመቋረጡ አንድ ምክንይት እንደሆነ ኃላፊው ለአዲስ ማለደ ገልጸዋል ።
ነገር ግን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ውላቸው እንዳልተቋረጠ፣ እንዲያውም ለቀጣይ ዓመትም መራዘሙን ገልጾ፣ ከኹለት ወራት በፊት የአምስት ሚሊዮን ብር ክፍያ ለኩባንያው እንደፈጸመ ይገልጻል።
የ‹የኛ ትራንስፖርት ማኅበር› ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ደጀኔ ሉሄ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ “መንገዱ የገቢና ወጪ ንግድ መንገድ ከመሆኑ አንጻር ኮንቴይነር ጫኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መንገዱ መኪኖቻቸው እየጎዳባቸው እና ለተጨማሪ የመለዋወጫ ወጪ እየዳረጋቸው በመሆኑ የማኅበሩ አባላት የጋርመንትን መንገድ እንደአማራጭ እየተጠቀሙ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን እና በውኃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን መካከል ባለ አለመግባባት የአካባቢውን ነዋሪዎች እና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ባለንብረቶች ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014



