በአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ሥራዎች በብዛት በመቆማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቀናል ሲሉ በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ ያሉ ብዙ የግል ባለሀብቶች ሕንጻ እየገነቡ ባለመሆኑ ኑሯቸውን በቀን ሥራ ላይ መሠረት ያደረጉ በርካታ ዜጎች መቸገራቸው ነው የተገለጸው። አናጺ እና የግንባታ ሠራተኛ የሆኑት እሸቱ ኃይለ ማርያም፣ በአሁኑ ወቅት ከመሬት የሚነሳም ሆነ የተጀመረ ሕንጻ ግንባታው ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የቆመ በመሆኑ ሥራ ማጣታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ሕንጻ ሲገነባ ኮንትራት ይዤ ነው የምሰራው የሚሉት ግለሰቡ፣ የግንባታ ሥራ ለረዥም ዓመታት የሠራነው ሙያ ስለሆነ ሌላ ሥራም ሆነ የትምህርት ደረጃ ስለሌለን በዚህ ወቅት ቤት ቁጭ ብለን ያለንን ገንዘብ ለቤት ኪራይ እና ለቀለብ እየተጠቀምን ነው ብለዋል።
ከመንግሥት ግንባታዎች እና ከትልልቅ ድርጅቶች በስተቀር በአሁኑ ሰዓት የግል ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ቆሟል ማለት ይቻላል ሲሉም ነው የተናገሩት። የሲሚንቶ ዋጋ ቀንሷል፣ የብረት ዋጋም ባለበት ነው ቢባልም የግንባታ ሥራው መቋረጥ የብዙዎቻን ሕይወት ፈተና ውስጥ አስገብቷል ነው ያሉት። በእርሳቸው እምነት ይህ የሆነበትን ምክንያት በግልጽ ባያውቁም፣ በዋናነት የባንክ ቤት ብድር መገደቡ እና የመሥሪያ ቦታ መሸጥ መለወጥ ባለመቻሉ እንዲሁም ባለው አገራዊ ሁኔታ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወደቀ አጥር እንኳን ለማቃናት ደንቦች እንደሚከለክሉ አስረድተዋል።
ከአዲስ አባባ ከተማ ውጭ ባሉ ከተሞች የግንባታ ሥራዎች እንዳልተቋረጡ ጨምረው ገልጸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከግንባታ ጋር የተያያዘ ሥራ በመሥራት ቤተሰብ የሚመሩ እና ልጅ የሚያሳደጉ በርካታ ሰዎች በችግር ውስጥ መኖራቸውን ተረድቶ ምላሽ ቢሰጥ መልካም ነው ብለዋል።
ቡና ቤት ከፍታ የምትሠራዋ ወጣት ውቢት መልክህ እንዲሁ ብዙ ደንበኞቿ በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች መሆናቸውን ገልጻ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በቀን የማገኘው ገቢ በግማሽ ቀንሷል ስትል ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች። ይህም የሆነው በዋናነት በከተማዋ የግንባታ ሥራ በአብዛኛው በመቆሙ ነው ብላለች። ችግሩ አነስተኛ ምግብ ቤት ከፍተው በሚሠሩና ሌሎች በጥቃቅን ሥራ ላይ ተሰማርተው በሚኖሩ በርካታ ሰዎች ላይ ያንዣበበ መሆኑንም ጠቁማለች።
አልፎ አልፎ ግንባታዎች ቢኖሩ እንኳን የምንሠራባቸው ቀናት ውስን ናቸው የሚሉት የቀን ሠራተኞቹ፣ ብዙ አሠሪዎች ደግሞ ብር ከባንክ ማውጣት ስላልቻልን ነው በማለት የሠሩበትን ገንዘብ በጊዜ ስለማይሰጧቸው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።
በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመጠየቅ አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይን እና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ኃላፊ አያልነሽ ኃብተ ማርያም (ኢ/ር) ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በበኩሉ፣ በአዋጅ የተወረሱ የድሮ ቤቶችን በመገንባት ለኪራይ የሚያውል መሆኑን ገልጾ፣ በአሁኑ ሰዓት ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች እያሰገነባቸው ያሉ ቤቶች ግንባታቸው ሳይቋረጥ በፍጥነት እየተገነቡ መሆኑን እና ብዙ የቀን ሠራተኞችም በሥራ ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014


