የጥንቃቄ ማነስ በጎንደር ሕይወት አስከፈለ

Views: 79

ባሳለፍነው ሳምንት የተከበረው የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ጥሩም መጥፎች ድርጊቶችን ያስተናገደ ነበር። በጥሩነት የሚወሰደው በአብዛኛው የአገሪቱ ቦታዎች በዓሉ በሰላም መከበሩ፣ የሕዝብን አንድነት የገነባ መሆኑ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር አብረው ያከበሩባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው ነው።

በመጥፎ ከሚነሱት አጋጣሚዎች መካከል ደግሞ በሐረር የታየው ረብሻ እና በጎንደር የተከሰተው አደጋ ተጠቃሽ ናቸው። የጥምቀት አከባበር በጣም ከሚደምቅባቸው የአገራችን ከተሞች በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ጎንደር ከወራት በፊት በዓሉ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ ከመቼውም በላይ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች። በመሆኑም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ታከለ ኡማ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራል መንግሥት እና የክልል ባለሥልጣኖች በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው ነበር። አከባበሩም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ ስቧል።

ቁጥራቸው በርከት ያሉ ጎብኚዎች ከተማዋን አጨናንቀዋታል። ነገሮች በደመቀ መንገድ እየሔዱ እያለ ግን ለታዳሚው መቀመጫ እንዲሆን የከተማው አስተዳደር ያሠራው የእንጨት ርብራብ እላዩ ላይ የነበሩትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይዞ ወደቀ። ባልታሰበው አደጋም በተለያዩ ሪፖርቶች 10 ሰዎች እንደሞቱ ሲዘገብ 250 ሰዎች ደግሞ ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

 የአገሪቱን እና በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ትኩረት ስቦ የቆየው የጎንደር ጥምቀት አከባበር በቀላሉ ተገቢው የጥራት ደረጃ ላይ ያለ ርብራብ መሠራቱን በማረጋገጥ የብዙዎችን ሕይወት መታደግ የሚቻልበት ነበር። የዚህ ትንሽ መሳይ ሥራ በአግባቡ ያለመከናወን ግን የዜጎችን ሕይወት ከማጥፋቱም በተጨማሪ አከባበሩ ላይም ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com