የመጠለያና የምግብ ዕጥረት የገጠማቸው ተፈናቃዮች

0
1337

በአገራችን የተከሰተው ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ከአንድ ወር አስቆጥሯል። ይህን ተከትሎም ጥቃቱ የፈተናቸው በጦርነቱ ቀጠና የሚገኙ ዜጎች፣ ቤታቸውን ለቀው ሠላም ወደ ሠፈነባቸው የአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች መፈናቀላቸው ይታወቃል።

ጦርነቱ በፍጥነት ዕልባት ባለማገኘቱ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ችግር እየተስፋፋ መጥቷል። በዚህም በርካታ ዜጎች እስከ አራት ጊዜ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ።
ከራያ ቆቦ ከተማ ጀምረው አካባቢያቸውን በመልቀቅ እስከ ደብረ ብርሃን ያቀኑ ዜጎች “በተደጋጋሚ ተፈናቅለናል” ከሚሉት መካከል በቀዳሚነት ተጠቃሾች ናቸው። ታዲያ የመፈናቀል ክፋቱ በድርብርብ ችግሮች የተሞላ መሆኑ እንጂ፣ ቤትን ለቆ መንከራተቱ ብቻ አይደለም የሚሉት በርካቶች ናቸው። ከእነዚህም ድርብርብ ችግሮች መካከል በግንባር ቀደም የሚያነሱት የመጠለያና የምግብ ዕጥረትን ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ታጣቂ ቡድን ወደ አማራና አፋር ክልል ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ፣ ካሳለፍነው ሐምሌ 2013 ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ወልድያ፣ መርሳ፣ ውርጌሳ፣ ደሴ፣ እንዲሁም ኮምቦልቻ በማቅናት በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የህወሓት ቡድን ወደ ደሴ ከተማ በመጠጋት ጥቃት መሠንዘሩን ተከትሎ በርካቶች ወደ ደብረ ብርሃንና ባህር ዳር ከተማ ማቅናታቸውን የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲዘግቡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ከሰሜኑ የአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለማቅናት የፈለጉ ሰዎች “የህወሓት ቡድን ሠላዮች ተፈናቃይ በመመሳሰል ተቀላቅለው ሠርገው እየገቡ ነው” በሚል፣ ማንኛውም ተፈናቃይ ከደብረ ብርሃን ወዲህ መምጣት እንዳይችል መንገድ መዘጋቱን አዲስ ማለዳ ስትዘግብ ቆይታለች።

መንገድ ተዘጋብን በሚል ለቀረበው የተፈናቃዮች ቅሬታም ምላሽ ለመስጠት የተሞከረ ሲሆን፣ ስደተኞች ‹‹ባሉበት አካባቢ መቆየታቸው ተመሳስለው የሚገቡ ሰላዮችን ለመለየት ዋነኛ መንገድ መሆኑ›› በሚመለከታቸው አካላት ሲነገር ነበር።

ይህንኑ ሐሳብ ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ባለንበት ተቀምጠናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እያሳሰቡ መቆየታቸውን አንስተዋል። ይሁን እንጅ ባሉበት ሁነው ተገቢውን ድጋፍ አለማግኘታቸውን የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ አሁን ላይ የአልባሳትና የምግብ ዕጥረት እንዳጋጠማቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“ከአምስት ቤተሰቦቼ ጋር በደብረ ብርሃን ከተማ ቤት ተከራይቼ ነው ያለሁት” የሚሉት አበበ ኃይሉ፣ ከወልደያ ከተማ ጀምሮ ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን እንደመጡ ይናገራሉ። እስካሁን ለምግብ ፍጆታ የሚጠቀሙትም በደሴ መጠለያ በነበሩበት ወቅት የተደረገላቸውን የእርዳታ ድጋፍ እንደሁነ ይገልጻሉ።

አበበ አያይዘውም፣ ወደ ደብረ ብርሃን ካቀኑ ጀምሮ ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ያመላከቱ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ከቤተሰባቸው ጋር ችግር ላይ በመሆናቸው ወደ መጠለያ እንኳን እንዲቀላቀሉ የሚመለከተው አካል እንዲተባበራቸው ጠይቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ከመጠለያ ጣቢያዎች ውጭ በዘመድ ቤት ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮቹ ከመጠለያ ውጭ በመሆናቸው ምክንያት፣ ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ ሊሰጥ ከሚችለው የድጋፍ ዕርዳታ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰሜን ሸዋ ዞን የአደጋ ሥጋት እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አበባው መለሰ፣ ከ25 እስከ 40 የሚደርሱ ተፈናቃዮች በግለሰቦች ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ሮቤል ሞላ የተባሉት ግለሰብ የመጠለያ ቦታ (ካምፕ) ባለማግኘታቸው ከዘመድ ቤት ተጠግተው እንደሚገኙ ጠቁመው፣ ድጋፍ በሚደረግበት ወቅት ለማግኘት እንደተቸገሩ አብራርተዋል።

አክለውም፣ ወደ አገራቸው እንዳይሄዱ ጦርነቱ፣ ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይንቀሳቀሱ የመንገድ መዘጋት፣ እንዲሁም የዕርዳታ ድጋፍ አለማግኘታቸው በጦር ሜዳ ከሚደርሰው ችግር ያልተናነሰ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

ግለሰቡ በመጨረሻም፣ ከምንም በላይ መንግሥት ጦርነቱን በወቅቱ እልባት ሰጥቶ ወደ አካባቢያቸው እንዲመልሳቸው አሳስበዋል።

ሌላኛዋ ከቤተሰብ ተጠግቼ ነው የምገኘው ያሉት የሺወርቅ አለሙ የተባሉት እናት ሲሆኑ፣ በተጠጉበት ቤት በርካታ ተፈናቃዮች ስለሚገኙ ለመኖርም ሆነ ወጥተው ለመግባት እንደተሸማቀቁ ይናገራሉ።
የሺወርቅ ወቅታዊን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ያስጠጓቸው ሰዎች ድጋፍ ስላደረጉላቸው ደስተኞች ቢሆኑም፣ በዚህ ኑሮ ውድነት ከቤተሰብ ላይ መደረብ በጭንቀት መወጠር ነው ሲሉ ነው የገጠማቸውን ችግር አስከፊነት የተናገሩት።

አያይዘውም፣ ሠላም ሰፍኖ ወደ ቀያቸው እስከሚመለሱ የሚመለከተው አካል የመጠለያና የምግብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል፣ ለተፈናቃዮቹ ፈተና የሆነባቸው የቤት ኪራይ ወጭ እንደሆነ ነው አዲስ ማለዳ የተገነዘበችው።

ብርሃኑ ኃይሉ የተባሉት ግለሰብ የቤት ኪራይ ውድ ቢሆንም፣ በርካታ ተፈናቃዮች የመጠለያ ዕጥረት ስለገጠማቸው ተከራይተው ለመቆት መገደዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እስካሁን የዓይነትም ሆነ የገንዘብ ብሎም የመጠለያ ድጋፍ እንዳላገኙ የገለጹት ብርሃኑ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩና ለኪራይም 2ሺሕ 500 ብር እንደሚከፍሉ ነው ያመላከቱት። አክለውም ለቤት ኪራይ ብቻ የሚያወጡትን ወጭ እንኳን ለመሸፈን እንደተቸገሩ ነው የጠቆሙት።

ተፈናቃዮቹ ወደ አገራቸው ለመመለስም ሆነ ሠላም ወዳለበት አካባቢ ለመሄድ መንገዶች እንደተዘጉባቸው ገልጸው፣ መንግሥትና በጎ አድራጊ ድርጅቶች ባሉበት የቻሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው በአዲስ ማለዳ በኩል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አዲስ ማለዳ በተፈናቃዮች ቅሬታ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቆይታ አድርጋ፣ መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ እንደሚከተለው አቅርባለች።
በአገሪቱ ላይ በተከሰተው ጦርነት እስካሁን በአማራ ክልል ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ተፈናቅለዋል የሚሉት የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እያሱ መስፍን ናቸው።

የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የሚዘጋጁት መጠለያዎች በቂ አለመሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ በርካታ ተፈናቃዮች እየኖሩ ያሉት በማኅበረሱ ውስጥ ተጠግተው እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህም ሆኖ ለተፈናቃዮች ድጋፉን ለማዳረስ የሚችሉትን እያደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።

እያሱ መስፍን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ 98 በመቶ የሚሆነው ተፈናቃይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጠግቶ የሚገኝ መሆኑን ነው። አያይዘውም የመተባባር ባህሉን በማንጸባረቅ ተፈናቃዮችን በከፍተኛ ደረጃ እየረዳልን የሚገኘው ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ለመስጠት የማይሳሳው ይኸው የማኅበረሰብ ክፍል ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል፣ ቁጥራቸው ከ40ሺሕ በላይ ወይም ኹለት በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች በ32 ጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

ጦርነቱ በመስፋፋቱ ዜጎች ከቆቦ ጀምሮ በተደጋጋሚ ከአራት አካባቢዎች በላይ እንደተፈናቀሉ እያሱ አመላክተው፣ ይህም ከባድ የሥነ አእምሮ ጉዳት አስከትሎባቸዋል ነው ያሉት።
ይህንን ችግር ለማቃለል ሰሞኑን በሥነ ልቦና ባለሙያዎች ትምህርት ለመስጠት በሒደት ላይ መሆኑን አመላክተው፣ ትምህርቱ ከተሰጠ በኋላ ተፈናቃዮቹ ከደረሰባቸው ጉዳት መላቀቅ ይችላሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

ከዚህም በተጨማሪ፣ በሽርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች የመድኃኒትና የምግብ ድጋፍ እያገኙ አለመሆናቸውን ጠቁመው፣ ለዚህም ምክንያቱ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የገቡትን ቃል እየተወጡ ባለመሆናቸው ነው ብለዋል። አያይዘውም፣ በገቡት ቃል መሠረት ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው ጥሪያቸውን ያቀረቡት።

ደብረ ብርሃን ለሚገኙ የምግብ ዕጥረት አለብን ለሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ድጋፍ ማድረግ ግዴታችን ነው የሚሉት እያሱ፣ በተቻለ መጠን ዕርዳታ ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ከኹለት ጊዜ በላይ ተመዝግበው ድጋፍ የሚቀበሉ ወጣቶች እንዳሉ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ወጣቶቹ ለአረጋውያን የሚሰጠውን ድጋፍ ከመሻማት ይልቅ ጥቃት በመሠንዘር ላይ ያለውን ሽብርተኛ ቡድን መጋፈጥ ይገባቸዋል ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

እያሱ በመጨረሻም፣ “አገራችን በየጊዜው ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደች ስለሆነ፣ ኹሉም ማኅበረሰብ ርብርብ በማድረግ ጥቃት የሚያደርስብንን ቡድን ለመመከት መዘጋጀት አለበት” ሲሉ ነው ጥሪያቸውን ያስተላለፉት።

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ ማለዳ የተፈናቃዮች የመጠለያ ዕጥረት በተመለከተ ከሰሜን ሸዋ ዞን የአደጋ ሥጋት እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አበባው መሰለ ቆይታ አድርጋለች።
አበባው መለሰ የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 220 ሺሕ መድረሱን አመላክተው፣ በዚህ ወቅት ዕርዳታ ማዳረስ ያልተቻለበት ምክንያትም ሰሞኑን ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ እየተመሙ ስለሆነ ነው ብለዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ 17 ሺሕ 705 ተፈናቃዮች በደብረ ብርሃን አጠቃላይ ኹለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ደብረ ኢባ፣ አንድነት፣ ብሩህ ደስታ እንዲሁም ቤተ መንግሥት በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙም አበባው አመላክተው፣ ተጨማሪ መጠለያዎች እንደሚያስፈልጋቸው እና ችግሩን ለመፍታት ድንኳኖችን የመትከል ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
አበባው አያይዘወም ከድንኳን ተከላው በተጨማሪ ለመጠለያ የሚሆኑ መጋዝኖች እና ትርፍ የሆኑ ቦታዎችን የመለየት ሥራ ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ተፈናቃዮች ከሰሜን ሸዋ ቆላማ አካባቢዎች ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ መጓዛቸውን አላቆሙም የሚሉት አበባው፣ አቅማቸው በፈቀደው መጠን ወደ መጠለያ ለማስገባት እየሞከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ የመጠለያ ችግር ከመኖሩም በጨማሪ የፍራሽና ለምግብነት ፍጆታ የሚውሉ አስቤዛዎችም በቂ እንዳልሆኑና ለተፈናቃዮች ለማዳረስ እንደተቸገሩ ነው የተናገሩት።
በመጨረሻም፣ ከመጠለያ ውጭ ያሉ ተፈናቃዮችን በመመዝገብ ሒደት ላይ እንደሆኑ ያመላከቱ ሲሆን፣ ከምዝገባ በኋላ ዕርዳታውን ለማዳረስ እንዳሰቡ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here