ዳሰሳ ዘ ማለዳ(ጥር 26/2012)

Views: 299

በቻይና የተከሰተውን እና እስካሁን ለ426 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ ለመግታት በዓለም አቀፍ ጉዞ እና ንግድ ላይ የተደረጉት እገዳዎች አላስፈላጊ እንደነበሩ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራልቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ገለፁ። ሁሉም አገሮች በማስረጃ ላይ የተመሠረተ እና ወጥነት ያላቸውን ውሳኔዎች እንዲተገብሩ ጥሪ እናቀርባለን ሲሉ ባለፈው ሳምንት ያስተላለፉትን መልክት ለዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ በድጋሚ አስታውሰዋል። ቫይረሱ ከቻይና ውጭ ያሳየውን መዛመት በተመለከተም ቴድሮስ ‹‹አነስተኛ እና ስርጭቱም ዘገምተኛ እንደሆነ፣ ነገር ግን ከዚህ በላይ አደገኛ ሊሆን ይችል ነበር›› ሲሉ አስታውቀዋል።በዓለም ጤና ድርጅት የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባ ላይ የተገኙት የቻይና ልዑካን በበኩላቸው ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባት የሁቤይ ግዛት ፓስፖርትን የያዙ ሰዎች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የከለከሉ ሀገራት የወሰዱት እርምጃ ትክክል አይደለም ሲሉ ማውገዛቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።(ሮይተርስ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

ዘጠኝ ዓመት የፈጀው የገናሌ ዳዋ ቁጥር 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ዛሬ ጥር 26/2012  በይፋ ተመረቀ። ግንባታው 2003 የተጀመረ ሲሆን  ፕሮጀክቱ 254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።ከተያዘለት ጊዜ ዘግይቶ የተጠናቀቀ ይህ ፕሮጀክት ነው451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል። የፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር የሀገሪቱን ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅምን ወደ 4654 ሜ.ዋ ከፍ ያደርገዋል ተብሎም ይጠበቃል።(ኢቢሲ)

 

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

በአርባምንጭ አጎራባች ወረዳዎች በጣለ ከባድ ዝናብ ሳቢያ የነዋሪዎችን ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የጋሞ ዞን አስተዳድር አስታወቀ።በትላንትናው እለት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ በአርባ ምንጭ ዙሪያ በሚገኙት የሰጎ እና ሲሌ ወንዝ በመሙላታቸው በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የዞኑ የህዝብ ግኑኝነት ገልጿል።በአደጋው  በርካታ ቤቶች በውሀ መዋጣቸውን እና የአርሻ ማሳዎች በውሃው በመጥለቅለቃቸው ነዋሪዎቹ ለችግር መጋለጣቸውን ያስታወቁ ሲሆን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ደርሶ በላይ በስፍራው በመገኘት የደረሰውን ጉዳት ተመልክተው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አስቸካይ ሰብአዊ እርዳታ ይደረግላቸዋል እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።እንዚህ ወንዞች ሞልተው በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው እንደነበርም ተገልጿል ።(የጋሞ ዞን አስተዳድር ህዝብ ግንኙነት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

የቡና ዋጋ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ይህም ባለፉት ዓመታት ከቡና ዋጋ ማሽቆልቆል ጋር በተያያዘ አርሶ አደሩ በቡና ላይ ፊቱን በማዞር ቡናውን እየነቀለ በሌላ ሰብል ይተካል በሚል ይሰጋ የነበረበትን ሁኔታ እንደሚለውጠው የቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለፀ፡፡  ባለፉት ሁለት ዓመታት ዓለም አቀፉ የቡና ዋጋ በመቀነሱ የኢትዮጵያ የቡና ዋጋም መቀነስ ግድ ሆኖበት ነበር፤ በዚህ ዓመት በተለይ ያለፉት ሁለት ወራት ግን ዋጋ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል ሲሉም የባለስልጣኑ የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኸይሩ ኑሩ ገልጸዋል።ዋጋው እንደየአካባቢው ቢለያይም እሸት ቡና ከ15 እስከ 25 በመቶ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነው የይርጋ ጨፌና የሐረር ቡናም እስከ 30 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ጠቁመዋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

በደቡብ ክልል እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህፃናት ከዛሬ ጥር 26 /2012 ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀመረ። ከክልሉ አጎራባች አካባቢ የልጅነት ልምሻ በሽታ ምልክት በመታየቱ ከወዲሁ ለመከላከል ክትባቱ ተጀምሯል ሲለም የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ቤተልሄም እምነቴ ገልጸዋል።በሽታው በዋናነት ሊከሰትባቸው ይችላሉ ተብሎ በተለዩ ሀድያ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ወላይታ፣ ሀላባ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌና ስልጤ ዞኖች እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ክትባቱን እንደሚሰጡም አስታወቀዋል።(ኢዜአ)

 

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

የካቲት 1 እና 2/2012 ለ33ኛ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ቴዎድሮሰ አድሃኖም(ዶ/ር) እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ጥር 26/2012 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታወቀ። በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ 45 አገሮች የሚሳተፉ ሲሆን 31 ፕሬዝዳንቶች ሦስት ምክትል ፕሬዝዳንት እና አራት ጠቅላይ ሚኒቴሮች እንዲሁም 14 ቀዳማይ እመቤቶች  ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል  ሲሉ የሚኒስቴሩ  የፕሮቶኮል ጉዳዮች ተጠባባቂ ዳይሬክትር ጄነራል ግስላ ሻወል  ገልጸዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ከአፍሪካ አባል አገራት በተጨማሪ ከአሃጉሩ ውጪ የሚመጡ አገራት መሪዎች የሚገኙ ሲሆን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጀሰቲን ቱድሮ አንዱ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። የህብረቱ የመሪነት ቦታ ላይ የነበረችው ግብፅ ቦታዋን ለደቡብ አፍሪካ እንደምትሰጥ ግስላ ተናግረዋል።(አዲሰ ማለዳ)

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com