በኢትዮጵያ መንግሥትና ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው ህወሓት መካከል ጦርነት ከተከፈተ ከዓመት በላይ ሲሆነው፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ጦርነቱ እየተባባሰ መቀጠሉ ይታወቃል።
በጦርነቱ ምክንያትም በርካታ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውና ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ችግር ላይ መውደቃቸው ይነገራል።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ንብረቶች መዘረፋቸውና መውደማቸውን በተመለከተም በየወቅቱ የሚዲያ ተቋማት ሲዘግቡ መቆየታቻው የሚታወስ ነው።
ይህን ተከትሎም በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ሆነው ገፈቱን የሚቀምሱ፣ ብሎም ሠላም በሠፈነበት ቦታ ያሉ ዜጎች ችግሩ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ በየዕለቱ ሲያሳስቡ ማድመጥ እየተለመደ መጥቷል።
ለተራዘመውና እየተስፋፋ ለመጣው ጦርነትም የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት አንደኛው ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ሲያነሱ ይደመጣሉ።
በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ በመግባት ጫና የሚያሳድሩ በርካታ አገራት እንዳሉ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል ግብጽና አሜሪካ ተጠቃሽ ናቸው።
ለአብነትም ሀብታሙ ግርማ ደምሴ፣ “ኢትዮጵያን እንዴት እናሻግራት” የሚል ርዕስ በተሠጠውና ጥቅምት 2014 ይፋ ባደረጉት ጥናትና ምርምራቸው ሱዳን በአሁናዊ የኢትዮጵያ ጦርነት ድንበር ጥሳ በመግባት ጫና እንዳደረሰች አመላክተዋል።
ለዚህ እኩይ ተግባሯ መሳካትም ዋነኛው ምክንያት የአገሪቱ በፖለቲካ መዳከም እንደሆነ አመላክተዋል።
“ዘንድሮም የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ሊደፍር የበቃው፣ በውስጥ ፖለቲካ ሽኩቻ አገሪቱ ስለተዳከመች ክፍተቱን ተጠቅሞ ነው። እንደ ግብጽ ዓይነት ቋሚ የኢትዮጵያ ጠላቶች በውስጥ ጉዳያችን እንዳሻቸው እንዲገቡ እየፈቀድንላቸው ያለው አሁንም የውስጥ ፖለቲካችንን በአግባቡ ማስተዳደር እያቃተን ስለሆነ ነው” በማለት ነው ሀብታሙ በጥናታቸው ያስረዱት።።
አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለከት የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በአገራችንና በሕዝቦቿ ላይ ቀላል የማይባል አለመረጋጋት እያስከተለ መሆኑን ነው።
በታሪክ ወደኋላ ብንመለከት፣ ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ በር የሚከፍትላቸው ግንባር ቀደሙ ችግር የውስጥ ፖለቲካን መቆጣጠር አለመቻል እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ለአብነትም በ1969 ሶማሊያ ኢትዮጵያን ልትወር የቻለችው በወቅቱ የነበረው መንግሥት ፖለቲካውን መቆጣጣር ባለመቻሉ እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል።
በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ በመግባት የምትታወቀው አሜሪካ እንደሆነች የተደበቀ እውነት አይደለም።
አሜሪካ፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ክልል የደኅንነት ሁኔታንና ሰበዓዊ መብትን ሠበብ በማድረግ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እያደረገች መሆኑ የሚስተዋል ነው።
በቅርቡ እንኳ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ወደ ጦር ግንባር ያደረጉትን ዘመቻ ተከትሎ ጦረኛ መንግሥት ስትል መቃወሟ ይታወቃል።
ለምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባታቸው ሌላኛው ምክንያት የሚባለው ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ የማድረግና በዚህም አሳቦ አገሪቱን ማፈራረስ እንደሆነ ነው የቅርብ ጊዜ ጥናቶች የሚያሳዩት።
“ለመጀመሪያ ጊዜ ከምዕራባውያን የፋይናንስ ምንጮች ለኢትዮጵያ መንግሥት የቀጥታ የበጀት ድጎማ ተደርጓል፤ በዚህም በ2011 ዓ.ም. የበጀት ዓመት 1.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ መንግሥት ካዝና ገብቷል። ይህም ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ካገኘችው የውጭ ዕርዳታ እና ድጋፍ 27 በመቶው” መሆኑን የሚያመላክተን የግርማ ደምሴ ጥናት ነው።
በርካቶች ኢትዮጵያ በውጭ ጣልቃገብነት አሁን እየደረሰባት ላለው አጣብቂኝ ዘመናዊ ቅኝ ግዛት የወደቀችው በራሷ ፍቃድ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ለዚህም ምላሻቸው ኢትዮጵያ ራሷን የቻለች በቅኝ ግዛት ሥርም ያልወደቀች አገር እንደመሆኗ ወደ ምዕራባውያኑ ለልመና እጆቿን መዘርጋት አልነበረባትም ባዮች ናቸው።
ይህን የሚሉትም፣ የምዕራቡ ዓለም አገራት በቀጥታ መሣሪያ ሳያስወነጭፉ፣ ሕዝቦቿን እርስበርስ በማባላት አገሪቷን የማፍረስ ግብራቸውን እያከናወኑ ያሉት “ልርዳ” በሚል መልካም ተግባር መሆኑን በማንሳት ነው።
የውጭ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በተመለከተም በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያ ከተሞች ሰሞኑን የተቃውሞ ሠልፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ለአብነትም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽ/ቤት ፊት ለፊት፣ “ኢትዮያዊነት ከዘር በላይ ነው” በሚል መፈክር ምዕራባውያኑና ሚዲያዎቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንዲያቆሙ በሠልፍ ሲጠይቁ ነበር።
የተቃውሞ ሠልፉ ከአገር ውጭ በሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵዊያን ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ በሚገኙ ዜጎችም ተከውኗል። ባሳለፍነው ኅዳር 16/2014 በአዲስ አበባ የሚገኙ ዜጎች በአሜሪካን ኤምባሲ ፊት ለፊት፣ “አሜሪካ ከኢትዮጵያ ላይ እጆቿን ታንሳ” በማለት የተቃውሞ ሠልፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ከጠላቶቿ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጫና የሚያሳድሩ አገሮች እንዳሉ ሁሉ፣ ጣልቃ ገብነቱ እንዲቆም፣ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉትን የተቃውሞ ሰልፍ የሚደገፉ አገሮችም አልጠፉም። ከእነዚህም ሩሲያ ተጠቃሽ ናት። ሩሲያ ባሳለፍነው ሳምንት የውጭ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና ስለመቃወሟ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት መዘገባቸው ይታወቃል።
ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ዜጎች ተቀባይነት የለውም የሚል ተቃውሞ ማንሳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሲሰጥም ተስተውሏል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአገሪቱ ላይ የሚያደርጉት ጫና ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም፣ የተቃውሞ ሠልፍ አገራችን ካለችበት አሁናዊ ችግር ለማላቀቅ ምን አስተዋጽዖ አለው? በቂስ ነው ወይ? በምዕራባውያኑስ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል? የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ይህን በተመለከተም አዲስ ማለዳ ከፖለቲካ ተንታኞች ጋር ቆይታ አድርጋለች።
በውጭ አገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያካሄዱት የተቃውሞ ሠልፍ፣ አሜሪካና መሠሎቿ በኢትዮጵያ ላይ ባለው ጦርነት ለሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት መቆም አስተዋጽዖ እንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ።
ተቃውሞው በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ለሚቀስሩ ምዕራባውያን አሉታዊ ተጽዕኖ አለው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና የኮሚዩኒኬሽን መምህርና የፖለቲካዊ ሳይንስ ምሩቅ የሆኑት አርካ አቦታ (ዶ/ር) ናቸው።
ሠላማዊ ሠልፉ መደረጉ በኢትዮጵያ ላይ የተነሳሱ ጫና ፈጣሪ አገራትን ለመገሰጽና ኢትዮጵያን “አይዞሽ አለንልሽ” በማለት፣ ካለችበት የሠላም አለመረጋጋት ለማውጣት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ይናገራሉ።
በውጭ አገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በምዕራባውያኑ ላይ ያደረጉት የተቃውሞ ሠልፍም፣ አሁን አገሪቱ ካለችበት ችግር ለመውጣት በቂ ነውን? የሚል ጥያቄ በበርካቶች ዘንድ ሲነሳ ተደምጧል።
በዚህ ጉዳይ ደግሞ አርቃ አቦታ (ዶ/ር)፣ በቂ የሚባል ነገር የለም፤ ይህ ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ። ለዚህም ምክንያታቸው የተቃውሞ ሠልፉ እየተካሄደ ያለው “ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” በሚመስል መልኩ ስለሆነ፣ ከዚህም በላይ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ከምንም በላይ የምዕራባውያኑን ፖለቲካ መረዳት ግድ ስለሚል ነው ብለዋል።
አንዳንዶች ሠልፍ ከማድረግ ይልቅ አገሪቷን በመሣሪያ መደገፍና እስከግንባር ድረስ ሔዶ ካለችበት ችግር ማውጣት እንጂ፣ ሠልፍ ማድረጉ የሚያመጣው መፍትሔ አመርቂ አይደለም እያሉ ይናገራሉ።
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት፣ ኢትዮጵያ ከገጠማት አሁናዊ ጦርነት ልትወጣ የምትችለው ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ሳይሆን፣ ከውስጥም ከውጭም ያሉት ልጆቿ በአንድ ልብ ሆነው ጥቃት የሚሰነዝርባትን አካል ፊት ለፊት ሲጋፈጡ ብቻ ነው በማለት ነው።
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ ሰልፉ “አገሬን አትንኩ” የሚል መልዕክት ስለሚያስተላልፍ፣ አገሪቱ ካለችበት ችግር እንድትወጣ ቀላል የማይባል አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳለው ይናገራሉ።
አሜሪካኖች ሠልፉን ከምንም ላይቆጥሩትና “ምን ያመጣሉ” ብለው በቀላሉ ሊያዩት ይችላሉ። ነገር ግን፣ ሠልፉ ውጮች ለሚያደረጉት ጫና መቀልበስ አንደኛው መመከቻ መንገድ በመሆን አስተዋጽዖ ያደርጋል የሚሉት የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህሩ ናቸው።
አንድን መፈክር በማንገብ ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ መልዕክት ማስተላለፍ ነው የሚሉት አርቃ ፤ “ኖ ሞር” የሚለውን የመፈክር ቃል በወቅቱ ሠልፍ ያደረጉት ዜጎች ባያስተላልፉት ኖሮ አሜሪካኖች በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ተቃዋሚ እንዳለባቸው ሊያውቁ አይችሉም ሲሉ ነው የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ያብራሩት።
አንዱ ሌላኛውን በሚያደርገው ነገር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት የሚችለው ሞግቶ በመናገር እንጅ በዝምታ አይደለም። ምዕራባውያኑ ለአብነትም አሜሪካንን ብንጠቅስ፣ “በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚደረገው ጦርነት ይቁም” ስትል መቆየቷ ይታወሳል።
ከአርቃ አቦታ ገለፃም መረዳት የተቻለው፣ አሜሪካም በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ በመግባት ጫና የምታሳድረው በመናገር ነው። ኹሉም ኢትዮጵያንም እኩይ ግብሯን እንደየአስፈላጊነቱ በየጊዘው መቃወሙ “ተሞግቻለሁ” የሚል የሥነ ልቦና ተጽዕኖ ያሳድርባታል በማለት ተናግረዋል።
አክለውም፣ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ታሪክና ክብር ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን፣ በራሷ አካሄድ ራሷ መወሰን ትችላለችና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማንም አገሩ ላይ ለሚያደርሰው ጫና “ኢትዮጵያን አትንኳት፤ በቃችሁ አገሬን አትንኩ” በማለት የዜግነት ድርሻውን በመወጣት ተጽዕኖ ማሳደር እንዳለበት ነው ያመላከቱት።
ይህ ሁነትም “ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” እንደሚባለው ዓይነት፣ ቸግሩ ሲደርስ ቱግ ቱግ በማለት ብቻ የሚደረግ ሳይሆን፣ የአገራዊ ወኔን ቅርጽ በያዘ መልኩ ተመሳሳይ ችግር በሚጋረጥበት በማንኛውም ጊዜ ሊደረግ የሚችል አስተማሪ ድርጊት ነው ሲሉ አርቃ ተናግረዋል።
ምዕራባውያኑ በአገሪቱ ላይ በሚያደርሱት ዛቻና ጫናን አስመልክቶ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተደረገው የተቃውሞ ሠልፍ የአሜሪካን ብቻ ሳይሆን የህወሓትንም ሥነ ልቦና የማዳከም ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተመላክቷል።
ህወሓት በኢትዮጵዊያ አንድነት፣ የግዛት ሉዓላዊነት፣ እንዲሁም በነበራት ሠላም ላይ በመነሳሳት ዜጎችን ከፋፍሎ እርስበርስ በማጣላት ለሚያደርገው ክፉ ሥራ፣ ሠላማዊ ሠልፉ የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚገልጽ በመሆኑ የጠላትን ዓላማ ያከሽፋል የሚሉት አርቃ አቦታ ናቸው።
በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያሳድሩት ሰንሠለቱን በጠበቀ ፖለቲካዊ አካሄድ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም መረዳት የሚቻለው ጫናቸውን ለመቀልበስ የኢትዮጵያ ዜጎች በፖለቲካ ብቁና ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው ነው።
ፖለቲካ ከሌለ ምንም ነገር የለም የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቁ አርቃ አቦታ (ዶ/ር)፣በወቅቱ ኢኮኖሚውም ባህሉም በፖለቲካ ስለሚለማ፣ ፖለቲካ ከተጣመመ ምንም ነገር ልክ አይመጣም። ምዕራባውያኑም ጫና የሚያሳድሩብን በፖለቲካዊ አካሄድ ስለሆነ፣ ወጣቱን በፖለቲካ መተርጎምና ማነጽ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
አክለውም፣ የኢትዮጵያ አብዛኛው ወጣት አእምሮው ለድፍን 27 ዓመት በዘረኝነት፣ በጎጠኝነት፣ በጠባብነት ፖለቲካ የታጨቀ ነውና፣ በመጀመሪያ ወጣቱን ኃይል በጋለው ምጣድ አብስሎ በአገር ፍቅር ፖለቲካ ለመገንባት የተቀናጀ ፖለቲካዊ ተቋም ያሻል ይላሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014



