በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ጥቅምት 24/ 2013 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በሠነዘረው ጥቃት ምክንያት፣ ለስምንት ወራት መንግሥት “ሕግ የማስከበር ዕርምጃ” ሲያከናውን ቆይቷል።
በወቅቱ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይሎች፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ባደረጉት “ሕግን የማስከበር ዕርምጃ” ህወሓት “ተበትኗል፤ ዱቄት ሆኗል” ሲባል እንደነበር የሚታወስ ነው።
በዚህ ሒደትም መንግሥት ሰኔ 24/2013 ለገበሬው “የእርሻ ፋታ ለመስጠት” የተናጥል ተኩስ አቁም ስምምነት አውጆ ነበር። ሆኖም ግን “ተበትኗል” የተባለው የህወሓት ቡድን፣ የፌዴራል መንግሥትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ጥቃት ለመሠንዘር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ከሐምሌ ወር 2013 ጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልል ጥቃት መሠንዘር መጀመሩ አይዘነጋም። በሂደት በአፋርም ሆነ በአማራ ክልል በኩል ህወሓት የሚዘነዝረውን ጥቃት በተወሰነ መልኩ ለመመከት ተችሎ ነበር።
ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት በጀመረባቸው ጊዜያት በአማራ ክልል በጎንደር በኩል እና በአፋር ክልል በተለያዩ ቦታዎች በደረሰበት ተደጋጋሚ ሽንፈት መግቢያ በር ባያገኝም፣ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ በኩል ግን ቀስ በቀስ የተለያዩ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ መምጣቱን የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲዘግቡ ቆይተዋል።
በሐምሌ 2013 የመጀመሪያዎቹ ኹለት ሳምንታት ህወሓት አላማጣ ከተማን አልፎ “ጮቢ በር” ቢደርስም፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደር ባደረጉት መከላከል ጥቃቱን መከተው፣ ቡድኑን መልስው አላማጣ እንዳደረሱት በወቅቱ ሲገልጹ ነበር።
የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና የአካባቢው አርሶ አደሮች በወቅቱ እንደገለጹት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግሉ በመቀላቀል፣ “እኛ ከፊታችሁ እንሆናለን፤ እናንተ ተመለሱ” እንዳሏቸው እና በሂደትም “ሥልታዊ ማፈግፈግ” እያደረግን ነው በማለት ወደ ኋላ እየተመለሱ መምጣታቸውን ነው መረዳት የተቻለው።
ይህን ተከትሎም ከሐምሌ 16/ 2013 ጀምሮ የህወሓት ታጣቂዎች በጮቢ በር፣ በደብረ ዘመዳ፣ በተኩለሽ፣ እንዲሁም በሸዎች ማርያም አካባቢዎች ሠርገው በመግባት የቆቦና አራዶም ከተማን መቆጣጠራቸውን የአካባቢው ማኅበረሰቦች ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር።
ከዚያም በኋላ ህወሓት ቀስ በቀስ እስከ ሰሜን ሸዋ ዘልቆ ገብቶ የተለያዩ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር መብቃቱ የሚታወስ ነው።
ህወሓት ወረራ ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የየአካባቢው ነዋሪዎች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው፣ መፈናቀላቸውና የመንግሥትም ሆነ የግለሰብ ንብረቶች መዘረፋቸው፣ ብሎም መውደማቸው ይነገራል።
ህወሓት ወረራ ፈጽሞ በከፈተው ጦርነት ምክንያት በርካቶች ለሞት እንደተዳረጉ እና ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሠላም ወዳለባቸው አካባቢዎች እንደተፈናቀሉ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጽ/ቤት ሲገልጽ መቆየቱን መጥቀስ ይቻላል።
ጥቃቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ፣ ከወራት በፊት መንግሥት የክተት ዐዋጀ አውጆ፣ ጥሪው ይመለከተኛል የሚል አካል ሁሉ ወደ ግንባር ሲዘምት መቆየቱ ይታወቃል። ሆኖም ግን የህወሓት ቡድን ጥቃት ከመሰንዘር ወደ ኋላ አላለም ነበር።
በወቅቱ፣ ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዴት ይህን ጥቃት መመከት ያቅተዋል? የሚለውን ጥያቄ በርካቶች ሲጠይቁ ነበር።
ብዙኃኑ እንደሚሉት ከሆነ፣ ለጦርነቱ መራዘም ምክንያቱ የነበረው ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሳድሩት ጣልቃ ገብነትና የመከላከያ ሠራዊት ወደ ማጥቃት መሸጋገር አለመቻሉ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ሰሞኑን ወደ ግንባር መዝመታቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ከዘመቱ ጊዜ ጀምሮ የድል ዜናዎች እየተሰሙ ነው። በዚህም ካሳጊታ፣ ጭፍራ፣ ጋሸና፣ አርቢት፣ ዳቦ፣ አቀስት፣ ወረኢሉ፣ ኢንቁፍቱ፣ መዘዞ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ሞላሌ፣ እንዲሁም ላሊበላን የመሳሰሉ፣ የአፋር፣ የደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ከተሞች ከህወሓት ታጣቂዎች ነጻ መውጣታቸውን የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ በግንባር የተሰለፉ ሁሉ አመርቂ ድል እያስመዘገቡ መሆኑን እና የህወሓት ታጣቂዎች በሠላም እጃቸውን እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሻምበል ተስፋዬ ውድማ፣ በኢትዮጵያ ላይ እየተሠነዘረ ያለው ጦርነት፣ በህወሓት ኃይል ብቻ ሳይሆን በአሜሪካም በኢኮኖሚ የታገዘ ነው ይላሉ።
ስለሆነም፣ በኢኮኖሚ በበለጸጉ አገራት የሚታገዝን ጠላት፣ በኢኮኖሚ የደቀቀች ኢትዮጵያ መቋቋሟና ለአሁናዊው የድል ዜና መድረሷ ለእኔ ተአምር ሆኖብኛል ሲሉም ነው የተናገሩት።
“ውጫዊ ኃይልን መመከት የሚቻለው በውስጣዊ አንድነት ነው” የሚሉት ሻምበል ተስፋዬ፣ ኢትዮጵያዊያን ከምንም በላይ አንድነት ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። በዘር በመከፋፈል ለዚህ የዳረጉን የውጭ ኃይሎችም ጭምር መሆናቸውን በመገንዘብ አንድነትን ከተቀዳጀን፣ የህወሓትን ቡድን ዋና ዋና መሪዎችን አከርካሪ መስበር እንደሚቻል ዕምነት አላቸው።
እንደ ሻምበል ተስፋዬ ገለጻ ከሆነ፣ የንብ ‹አጆ› በመባል የምትታወቀው ንግስቷ ከተመታች፣ ተከታዩዋ እንደሚበታተነው ሁሉ፣ ቀሪዎቹ መበተናቸው አይቀርም፤ ቢሆንም ግን ጥብቅ ፍተሻ ማድረግ የመንግሥትም የሕዝብም የቤት ሥራ ነው ሲሉ መክረዋል።
ሌላኛው የአብን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት ሲያምር ጌጤ፣ የማይቀረው የድል ዜና መኖሩን የሚያሳይ ሁኔታ እየተሠማ ነው፣ ቢሆንም ግን እየተደመሰሰ ነው የሚባለው የህውሓት ቡድን እንደገና ተቀልብሶ ጉዳት እንዳያደርስ መጠርጠሩና ከጫፍ እስከ ጫፍ የማጥራት ሥራ መሥራቱ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አያይዘውም፣ ጥቃት ለመሠንዘር ከተላላኪዎቹ ጋር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወደ ኋላ የማይለውን “ባንዳ” ለማጥፋት የተጀመረው የማጥቃት ጦርነት ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በሕዝብም በመንግሥትም በኩል በርካታ የቤት ሥራዎች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም ይላሉ።
አክለውም፣ የቡድኑን መሪዎች እንደየአመጣጣቸው በሕግም ሆነ በአልሞትባይ ተጋዳይነታቸው መመከት ተገቢ ነው ያሉ ሲሆን፣ የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከሠላማዊ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተላላኪዎችንም የመለየት ሥራ በሠፊው ሊሠራ ይገባል ሲሉ ነው የገለጹት።
በርካቶች በአሁናዊው የወገን የድል ዜና ደስታቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ እስካሁንም ቢሆን የበርካቶች ሞት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ከመድረሱ በፊት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመከላከል በዘለለ ወደ ማጥቃቱ ደረጃ መሸጋገር እንደነበረበት አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።
እስከዛሬ በነበሩት ውጊያዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመከላከል ውጭ የማጥቃት ተግባር ባለማድረጉ ህወሓት ብዙ ቦታዎችን እንዲቆጣጠር ረድቶት ነበር የሚሉት ሰሞኑን ወደ ሎጊያ ከተማ ያቀኑት የፋኖ ታጣቂ ተመስገን አሕመድ ናቸው።
ተመስገን እንደገለጹት ከሆነ፣ የህወሓት ታጣቂ ቡድን ወልድያን፣ መርሳን እንዲሁም ውጫሌን አልፎ ወደ ደሴ ከተማ ለማቅናት በዙሪያው እያሰፈሰፈ በነበረት ወቅት ተጋድሎ ቢያደርጉም፣ በቂ መሣሪያ እንዳልነበራቸው ነው የጠቆሙት።
የፋኖ ታጣቂው አክለውም፣ በዛን ወቅት መከላከያ ወደ ኋላ ባያፈገፍግ ኖሮ ተቃራኒ ቡድኑ አልፎ የተቆጣጠራቸውን ቦታዎች፣ ለሞት የዳረጋቸውን ሰዎች፣ የዘረፋቸውን በርካታ ንብረቶች ብሎም ያፈናቀላቸውን ዜጎች መታደግ እንችል ነበር ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።
ከፋኖ ቡድን አባላት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ለአምስት ወራት ያክል ከመንግሥት የተለያዩ ዕርዳታዎችን ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙና እስከ ኅዳር 21/2014 ህወሓትን በራሳቸው ብቻ እየመከቱ እንደነበር ነው።
ሰሞኑን የህወሓት ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋቸው የነበሩት የተለያዩ ቦታዎች በወገን እጅ በመግባታቸው ደስታቸውን የገለጹት ተመስገን፣ ታጣቂ ቡድኑ እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት ተከትሎ ከኅዳር 22/2014 ጀምሮ በዞብል ተራራ በሚገኙት ፋኖዎች ላይ ኃይሉን አሰባስቦ በአራት አቅጣጫ ጦርነት እንደከፈተባቸው አመላክተዋል።
ተመስገን እንደሚሉት ከሆነ፣ በዞብል ያለው የፋኖ ብዛት 400 ሲሆን፣ ከጋሸና በኩል ወደ ኋላ በማፈግፈግና ከመቀሌ በኩል በመምጣት፣ ጦርነት የከፈተባቸው የህወሓት ታጣቂ ከ4ሺሕ በላይ መሆኑን አመላክተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መዝመት በአገሪቱ ታሪክ አዲስ አይደለም። የቀደሙ የአገሪቱ መሪዎች ወደ ግንባር ዘምተው የድል ዜናን እየተቀዳጁ ሲመለሱ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።
“ተከተል አለቃህን፤ ፈጽም ዓላማህን” የሚለው መርህ ከአጼዎቹ ጀምሮ ነበር የሚሉት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ግንባር ተሰልፈው የተፋለሙት የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባል ሻለቃ አታኩራቸው ተጫኔ ናቸው።
ሻለቃ አታኩራቸው ለአብነትም አጼ ምኒልክ፣ “ተሰብሰቡና ወረኢሉ እንገናኝ” በማለት፣ የውጊያ ጥሪ አስተላልፈውና ሕዝባዊ ሠራዊት አስከትለው ድል ተቀዳጅተው እንደተመለሱ አብራርተዋል።
በመሆኑም ሰሞኑን የሚስተዋለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ታሪክን የደገመ፣ ስሜትን የሚያነሳሳና ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት ችግር ሊያወጣ የሚችል ነው የሚሉት ሻለቃ አታኩራቸው፣ የወታደሩን ወኔ ስመለከት እንባዬ ተናንቆኛል ይላሉ።
በ2013 ለስምንት ወራት በተወሰደው ዕርምጃ ጦርነቱ አብቅቷል ከተባለ በኋላ፣ ሽብርተኛ የተባለው ህወሓት ከአራት ወራት በላይ በንጹኃን ዜጎች ላይ ቀላል የማይባል ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል። በመሆኑም አሁንም ቢሆን ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደገም በርካታ ሰዎች እያሳሰቡ ይገኛሉ።
ጦርነቱ እንዳይደገም ምን ማድረግ ይሻላል?
በአሁኑ ወቅት ትግል እየተደረገ ያለው አሸባሪ ከተባለው የህወሓት ቡድን ጋር እንደመሆኑ እንደለመደው ዳግም እንዳያንሰራራ፤ ቡድኑን የማጽዳት ዘመቻው “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዳይሆን ሊሰመርበት ይገባል ሲሉ የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች በጥምረት ባደረጉት ውጊያ የተለያዩ ቦታዎችን ነጻ እንዳወጡ እየተመላከተ ነው።
የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩት ሻለቃ አታኩራቸው፣ ምንም እንኳ ሰሞኑን የሚሠማው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ድልን ያቀዳጃል የሚል ዕምነት ቢጣልበትም፤ “ድል አድርጋናል” ከተባለ በኋላ፣ በ2013 የተከሰተው ተመሳሳይ ችግር እንዳይደገም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በውጊያው ዘርፍ ልምዱ ያላቸው ሻለቃ አታኩራቸው ተጫኔ፣ የህወሓት ቡድን ዳግም እንዳያንሰራራ የወገን ኃይል በመጀመሪያ ደረጃ የተቃራኒ ቡድኑን የፕሮፖጋንዳ አካሄድ መረዳት ያስፈልገዋል ይላሉ።
“በፕሮፖጋንዳ መስመራችን ትንሽ ዘገምተኛ ነን” የሚሉት ሻለቃ አታኩራቸው፣ “ጠላቶቻችንን ቀድመን እስካወቅናቸው ድረስ የፕሮፖጋንዳ መንገዳቸውን ቀድመን ማጠር ነበረብን፤ በዚህ ደግሞ ተቀድመናል” ሲሉ ነው የተገነዘቡትን ክፍተት ያስረዱት።
አያይዘውም፣ ህወሓቶች እዚህ ደረጃ የደረሱት ብዙ ድርጅቶች ጋር በፖሮፖጋንዳ በመጣመር፣ የኢትዮጵያን ብር በመዝረፍ፣ ብሎም በየቦታው ግብረ አበሮቻቸውን በማደራጀት መሆኑን በማጤን፣ አካሄዳቸውን መፈተሽ ለዘላቂ ሠላም በር ከፋች ነው ሲሉ ነው ምክራቸውን የሰጡት።
በኹለተኛ ደረጃ፣ “በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ መፈተሽና መጽዳት ያለበት ነገር ያለ ይመስለኛል፤ እንዴት እንደሆነ ባላውቅም ኦነግ ሸኔዎች ወደ መከላከያ ሠራዊት ሠርገው ገብተዋል ተብያለሁ” ያሉት ሻለቃ አታኩራቸው፣ ይህ እውነት ከሆነ መከላከያ ሠራዊቱን የመፈተሽ ሥራ ቢሠራ መልካም ነው ብለዋል።
ይህ ችግር እየተከሰተ ያለው የድሮው የሠራዊት አባልና የአሁኑ ሠራዊት ወደ ውጊያ በሚሰለፍበት ወቅት የተለያየ በመሆኑ ነው ይላሉ። የድሮው ጦር ሠራዊት ወደ ውጊያ በሚሰለፍበት ወቅት፣ “አንድ ኢትዮጵያ፤ አንድ ሞት” በማለት ከውስጥ ምንም አይነት መከፋፈል ሳይኖር ሲሆን፣ አሁን ግን የጎጠኝነት ስሜት ስላለ፣ አንዱ ከአንዱ ጎን ለመሰለፍ እየተጠራጠረ ይመስለኛል ሲሉ ነው አያይዘው የጠቀሱት።
ሻለቃው ለዚህም ችግር ምሳሌ አቅርበዋል። “ፋኖዎችን ዕድል ገጥሞኝ ሳናግራቸው ከወገን አባል ከኋላ የመጠቃት ክስተት እንደደረሰባቸውና ይቅርታ እንደተጠየቁ ነግረውኛል”፣ ምናልባት ይህ እውነት ከሆነ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት እንቅፋት እንዳይሆን ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል ይላሉ።
በሦሰተኛ ደረጃ የህወሓት ቡድን የሚያካሂደው ጦርነት ሽምቅ እንጂ መስመር ላይ የተዘረጋ ስልትን የተከተለ አለመሆኑን መገንዘብ ድልን ለመቀዳጀት አንደኛው መንገድ ነው ይላሉ። በመሆኑም ህወሓት የተቆጣጠራቸውን ቦታዎች “ነጻ አወጣሁ” ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ጥብቅ ፍተሻ ማድረጉም ቃታ ስቦ በመዋጋት ጠላትን ድል ከማድረግ ያልተናነሰ ነው ሲሉ ነው አክለው ያብራሩት።
ይህን ማድረግ ያለበት ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን የአካቢቢው ነዋሪም ጉዳዩን የዕለትተዕለት ተግባሩ ሊያደረገው ይገባል የሚሉት ሻለቃው፣ ሙሉ ለሙሉ ውጊያው ተጠናቋል የሚባለው እያንዳንዱ ክልል አንድ በአንድ በነቂስ ተፈትሾ የህወሓት ተላላኪዎች ተመንትፈው ሲወጡ ነው ብለዋል።
በርካቶች እስከዛሬ ድረስ ለጦርነቱ መራዘም እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቅሱት፣ መከላከያ ሠራዊት የጠላትን ጥቃት በመከላከል ላይ እንጂ በማጥቃት ላይ አለማተኮሩን ነው። ይህን ተከትሎም ሰሞኑን ያለው የድል ዜና ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የማጥቃት ሥራው ግን ተራዝሟል የሚሉት በርካቶች ናቸው።
ከማጥቃት ይልቅ መከላከል በመመረጡ ጦርነቱ ተራዝሟል ከሚሉት ወገን ነኝ የሚሉት ሻለቃ አታኩራቸው ናቸው። የእኛ ሰው ብዙ ከመሆኑ አንጻር በእውነቱ ህወሓት እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብዬ አልገመትኩም ነበር የሚሉት የቀድሞ የአትዮጵያ ሠራዊት አባሉ፣ የሰሞኑ እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም፣ የህወሓት ቡድን እዚህ መድረስ አልነበረበትም ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014



