በሥነምግባር የታነጸ ትውልድን የማፍራት ጉዞ

ልጆች ለእርሻ እንደተዘጋጀ ለም መሬት ናቸው። ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ አገርና ትውልድ ደግሞ መልካም ዘርን እንዲዘሩ የሚጠበቁ ገበሬዎች። የአገር ተረካቢ ትውልድ የማንነት ግንባታ የሚጀምረው በሕጻንነት ዘመን ባለው ለም መሬት ላይ መልካም ዘርን በመዝራት ነው። በአገራችን ይህን እውነት ምን ያህል ልብ ብለነው ይሆን? ‹ተያይዘን ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት› ይህን ጉዳይ ልብ ከማለት አልፎ ሥራዬ ብሎ ይዞታል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ‹አዲሱ ትውልድ ያለውን እና የሚችለውን ለወገኑ እና ለአገሩ ያለምንም ምክንያት እና ልዩነት በመልካምነት እና በፍቃደኝነት መስጠት ይማር።›› የሚል መሪ ሐሳብ ይዟል።

ልጆች ለጋስና ሰጪ በመሆን ውስጥ ያሉ በጎ እሴቶችን እንዲያውቁ በማድረግ ግለኝነትን፣ ራስ ወዳድነትን እንዲሁም ጥቅመኝነትን እንዲያስወግዱ ማድረግ፣ በተቃራኒው ሰብአዊነትን፣ ርህራሄን እንዲሁም አገር ወዳድነትን እንዲያዳብሩ ማስቻል ግቡ ናቸው። ይህንንም ለማድረግም እድሜያቸው ከ6 – 15 የሚሆን አዳጊ ልጆች በሚገኙባቸው ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን ለጋስ ወይም ሰጪ የመሆንን ጥቅም በተለያየ መንገድ ማስተማርና ማስረዳትን አዋጪ መንገድ አድርጎ መርጧል።

ይህ መንገድ ባሳለፍነው 2013 በአዳማ ከተማ በሚገኝ ኔሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሙከራ ትግበራ ተደርጎበት ጥሩ ውጤት የተገኘበት እንደሆነ ማስረጃዎች ያመላክታሉ። ይህን ተከትሎ ነው እንቅስቃሴው በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዳጊ ሕጻናት ልጆችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲችል በንቅናቄ መልክ ሊተገበር መሆኑ ይፋ የተደረገው።

ኅዳር 16/ 2014 ድርጅቱ ‹የሚሰጥ ዘር 2014› በሚል መግቢያ ፕሮጀክት ንቅናቄ ማስጀመሪያ ፕሮግራምና ጋዜጣዊ መግለጫና የመክፈቻ መርሃ ግብር አካሂዷል። በዚህ መድረክ ላይ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በተጨማሪም ታዋቂ ግለሰቦች የዓላማው ደጋፊ ሆነው በዝግጅቱ ታድመዋል።

በዚህ ዝግጅት ላይ የሐሳቡ አመንጪና ባለቤት የሆኑት ምስጋናው ታደሰ ባደረጉት ንግግር፣ ፕሮጀክቱን ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውን ሁኔታዎች በሰፊው አብራርተዋል። በማብራሪያቸው እንዳነሱት እንቅስቃሴውን ለማስጀመርና ለመግፋት ምክንያት ከሆናቸው መካከል አንዱ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ይገኝበታል። እርሳቸው እንዳሉት ነባራዊ የኢትዮጵያ ችግሮች ከአእምሯዊ ልማት ይልቅ ቁሳዊ ብልጽግና ላይ ብቻ ትኩረት በመደረጉ ምክንያት የመጡ ናቸው።

ታድያ እርሳቸው እንደ ግለሰብ እነዚህ ችግሮች ሰፍተው ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሳይሸጋገሩ በፊት አሁን ላይ ተገቢውን ጥረት በማድረግ ማስቀረት ለነገ የሚባል ጉዳይ አለመሆኑን መገንዘባቸውን ይጠቅሳሉ። በዚህ የተነሳ የአዳጊዎች ሥነምግባር ላይ መሥራት የሚያስችል ፕሮጀክት አዘጋጅተው ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮምያ ክልል አዳማ ከተማ ተግባራዊ ሆኗል። አሁንም ላይ በመላ አገሪቱ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ በዋነኛነት ከሥነምግባር መገለጫዎች አንዱ በሆነው ‹መስጠት› ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይኸውም ሕጻናት ልጆች ከታች ጀምረው እርስ በእርሳቸው እንዲዋደዱ ለማድረግ ስጦታን እንደ አንድ መንገድ ለመጠቀም ያሰበ አካሄድ ነው። ይህ በጎ ሐሳብና አካሄድ ታድያ ጥቂት የማይባል ድጋፍን አግኝቷል። ዝነኛና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችም የእንቅስቃሴው አካል ለመሆን ተስማምተው ተቀላቅለውታል።

ሰባት የቦርድ አባላት ያሉት ተያይዘን ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ የበላይ ጠባቂዎቹ አትሌት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ እና አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ ናቸው። እነዚህ ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ፕሮጀክቱን በገንዘብና በማስተባበር ከመደገፋቸው በተጨማሪ ልጆቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች በየትምህርት ቤቶቹ በመዘዋወር የሥነምግባር እና የግንዛቤ መስጫ መንገዶችን እንዲሁም ተሞክሯቸውን ለታዳጊዎች በማካፈል በጎ መንገዶችን እንዲጠቁሙ እና እንዲያበረታቱ ያደርጋል።

ከእነዚህ አንጋፎችና ተጽእኖ ፈጣሪዎች በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት አካላትም ተሳትፎ ያደርጋሉ። በቀድሞ አጠራሩ የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር (የአሁኑ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር)፣ ሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ከጅምሩ አንስተው ደጋፊዎቻቸው እንደሆኑም በመድረኩ ተነግሯል።

ባለፈው ኅዳር 16/2014 ተዘጋጅቶ በነበረው መድረክ ላይ እነዚህ የዓላማው ደጋፊ የሆኑ ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተው የተለያዩ ገንቢ የሚባሉ ተሞክሮዎቻቸውን አካፍለዋል። ከእነዚህም መካከል ተዋናይ እንግዳሰው ሀብቴ (ቴዲ) የሙያ አጋሮቹን ወክሎ ስለ ፕሮጀክቱ አስፈላጊነት አስረድቷል።

እንግዳሰው ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲሆን ከሦስት ዓመት በላይ ያለመሰልቸት የሠሩትን ምስጋናውን አመስግኗል። አክሎም ‹‹አዳጊ ሕጻናትና ልጆች ከመሠረታዊና መደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ የሥነምግባር ትምህርቶችን በቋሚነት በተለያዩ መንገዶች አብሮ እንዲሰጣቸው ካልተደረገ በቀር ውጤቱ ገንብቶ ማፍረስ ነው። በመሆኑም በተለያዩ በጎ ያልሆኑ ተጽእኖ ውስጥ ያሉ ሕጻናትና ወጣቶች እምቅ ኃይላቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ እና ነገ ያሰቡት ቦታ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ተግባር እንዲያከናውኑ ማገዝ ተገቢ ነው።›› ብሏል።
አክሎም ‹መስጠት› ሲባል ገንዘብ ብቻ እንዳልሆነ አመላክቷል። አንጋፋ የሆኑና ብዙዎች ዘንድ እውቅና ያላቸው ሰዎች፣ እውቅናቸውን በመጠቀም ለልጆች መጻሕፍትን በማንበብ፣ ልምድን በማካፈልና በጎ ነገርን በማስተማር ማገልገል እንደሚገባ አንስቷል። ‹በእውቅናችን ካገለገልንና ጊዜያችንን መስጠት ከቻልን ለውጥ የማናመጣበት ምክንያት አይኖርም።›› ሲልም ተናግሯል።

የድርጅቱ ዓላማ ደጋፊ ከሆኑት መካከል ተዋናይ ይገረም ደጀኔ ይገኛል። ይገረም ስለ ፕሮጀክቱ ሲናገር በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምክንያት በጎ የሆኑ ነገሮች የመታየት እና የሰውን ቀልብ የመግዛት አዝማሜያቸው እምብዛም እንደሆነና ተደራሽ የመሆን እድላቸውም ዝቅ እያለ መምጣቱን ይናገራል። መገናኛ ብዙኀንም ቢሆኑ ቀና ለሆኑና ለውጥ ማምጣት ለሚችሉ እንቅስቃሴዎች ሳይሆን ትኩረታቸውን አፍራሽ ሊባሉ በሚችሉ መረጃዎች ላይ ማድረጋቸውን ይጠቅሳል። በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱ ትኩረት እንዳልተሰጠው አስረድቷል።
አያይዞም እንቅስቃሴው ይበል የሚያሰኝና አግባብ መሆኑን በመጥቀስ፣ ነገር ግን ደግሞ ስጋቱንም አጋርቷል። በተለይም ሥነምግባርንና የማንነት ግንባታን ‹ስጦታን በመለዋወጥና በመስጠት› ውስጥ ወይም ስጦታ መስጠትና መለዋወጥን መሠረት አድርጎ ማስተማር ትክክል ቢሆንም የአንድ ሰሞን ፋሽን ሆኖ እንዳይጠፋ አሳስቧል።

በተጨማሪም ታላቅ የሚባል ትክክለኛ ለውጥን ለማምጣት ሕጻናት ላይ ብቻ መሥራት በቂ አይደለም ባይ ነው። ለሕጻናት ከወላጆችና ከቤተሰብ የሚቀርብና ተጽእኖ መፍጠር የሚችል የለምና፣ ይልቁንም ሕጻናት ላይ መሥራቱ እንዳለ ሆኑ ቤተሰብም ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አሳስቧል።

ምስጋናው እንደሚሉት ሕጻናት ልጆችን በሥነ ምግባር አንጾ የማሳደግ ተግባር መንግሥት ላይ ብቻ የሚጣል ኃላፊነት አይደለም። የተሻለ ነገን ለልጅ ልጅ ለማስረከብ የሚሹ ዜጎች ጭምር እዚህ ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል። እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ማኅበራት፣ በጎ አድራጎት ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ የንግድ ማኅበራት፣ ባለሀብቶች፣ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን፣ ሕግ አውጪ እና ሕግ አስፈጻሚ አካላት የነገ አገር ተረካቢ ሕጻናትን የመፍጠር ሥራ ላይ በኃላፊነት ሊሠሩ የሚችሉ ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

‹የሚሰጥ ዘር – 2014› ፕሮጀክት ዋና ጉዳዩ ከተለመደው የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ልማድ በተሻገረ ልብ ተብለው ያልታዩ በጎ እሴቶችን ስለመስጠት ነው። ፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት ቆይታ የሚኖረው እንደሆነ ምስጋናው አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱም በውስጡ የተለያዩ ምዕራፎች እና ተግባራት ያሉት በዓይነቱ እና በይዘቱ ለየት ያለ የሥነ ምግባር ማስጨበጫ አገር ዐቀፍ ንቅናቄ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰውም ትኩረቱ በዋነኛነት ከሥነምግባር መገለጫዎች አንዱ በሆነው ‹መስጠት› ላይ ነው። በዚህ መሠረት ‹የመስጠት ቀን›ን ማዘጋጀት ከፕሮጀክቱ መተግበርያ መንግዶች አንዱ ተደርጎ ተይዟል።

በዚህ ቀንም ሕጻናቱ እርስ በእርስ ስጦታ እንዲሰጣጡ፣ መከባበራቸውን እና ፍቅራቸውን እንዲገላለጹ በማድረግ ይህን ባህል ለወደፊቱ እንዲያሳድጉ ጥረት ይደረጋል ተብሏል። ታዋቂ ሰዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች፣ መምህራንና በድምሩ ለልጆች አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ተደማጭ ሰዎችን በመጠቀም ‹መስጠት እና መቀበል ምንድን ነው? ለምንስ ይጠቅማል?› የሚለውን ልጆች እንዲማሩ ማድረግም የፕሮጀክቱ አካል ነው።

ተያይዘን ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሲቪል ሰርቪስ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀጽ 57(1) ሚያዝያ 01/2013 የተመሠረተ አገር በቀል ድርጅት ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here