ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ከገባች ከአንድ ዓመት ወዲህ በርካታ ግፎች መፈጸማቸው ሪፖርት ሲደረግ ቆይቷል። ዘግናኝ ግፍ አገራችን ውስጥ መፈጸም የጀመረው አሁን ባይሆንም፣ ከ3 ዓመት ወዲህ የሚፈጸሙት ግን ለጆሮም የሚከብዱ ናቸው። እኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በዚህ ዘመን ይሆናሉ ብለን የማንጠብቃቸው ዓይነት ዘግኛኝና ሰቅጣጭ ግፎችን ከመስማት አልፈን፣ የተላመድንበት ጊዜም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ግፍ ለሰሚው የሚዘገንነውን ያህል፣ ለሠሪው አለመክበዱ ከሚያመላክታቸው ጉዳዮች አንዱ ቀድመው በተፈጸሙ ተግባሮች መነሻነት ፈጻሚዎቻቸው ላይ ድርጊታቸውን የማያስደግም አስተማሪ ዕርምጃ አለመወሰዱ በዋናነት ይጠቀሳል። ማኅበረሰብን ለቂም የሚዳርጉና ተጎጂዎችን ደመከልብ ሆኑ አስብሎ ለበቀል ከሚያነሳሱ ተግባራት መካከል እንዲህ አይነት ከማኅበረሰቡ ያፈነገጡ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግፈኞችን ለፍትሕ በአፋጣኝ ማቅረብ አለመቻሉ እንደመሠረታዊ ክፍተት ይታያል።
ወንጀልን የፈጸሙ አካላት በመደበኛውም ሆነ ልዩ በሆነ የፍትሕ ሥርዓት እንደአገሪቱ አቅም ጊዜያቸውን ጠብቀው ለፍርድ መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በአንፃሩ ከማኅረሰብ ጋር ተቀላቅሎ መኖር የማያስችላቸውን ግፍ በማንአለብኝነት የፈጸሙ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ የፈጸሙት ዘግናኝ ተግባር በማኅበረሰቡ እስከታወቀ ድረስ የሌላውን አብሮ ኗሪነት ታሳቢ ያደረገ አስተማሪ የሆነ ቅጣትን በአፋጣኝ ማግኘት እንደሚገባቸው የአዲስ ማለዳ ዕምነት ነው።
ሰውን የፊጥኝ አስረው ያረዱ፣ አስከሬንን በየጎዳናው ያንገላቱ፣ በዘግኛኝና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የሰው ልጅን አሰቃይተውም ሆነ በድንጋይ ቀጥቅጠው የገደሉ፣ የጅምላ ጭፍጨፋ የፈጸሙና ያስፈጸሙ፣ ሕፃን አዛውንት ሳይሉ መነኮሳትንም የደፈሩ፣ በትዳር አጋሮቻቸውና ቤተሰባቸው ፊት እመጫትንም ጨምሮ በቡድን የደፈሩ፣ በዘግናኝ መንገድ አቅም የሌላቸውን ያሰቃዩ፣ እንዲሁም ሕብረተሰቡ ኑሮውን መሠረት ያደረገባቸውን እንስሳትንም ሆነ ሰብሎቹን ሆን ብለው በጥላቻ ተነሳስተው ያወደሙና እነዚህ ተግባራት እንዲፈጸሙ የቀሰቀሱ፣ ጭምር ከሌላው ወንጀል በተለየ ተለይተው በአፋጣኝ ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል።
የሕብረተሰቡን አብሮ የመኖር ዕሴት ሆን ብለው ለመሸርሸር እንዲህ አይነት ለመንገርም የሚከብዱ ተግባራትን ከዚሁ ማኅበረሰብ ውስጥ ወጥተው የፈጸሙ፣ እዚሁ ማኅበረሰብ ውስጥ ተደብቀው እንዲኖሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም። እንዲህ ዓይነት ግፈኞችን የደበቀ ወገኔ የሚላቸውም ሆነ ቤተሰቤ የሚላቸው የማኅበረሰብ ክፍል፣ በእንዲህ ዓይነት ተግባር አልፈው ልምድ የሆነባቸው ነገ ለልጆቹ እንደማይመለሱ መገንዘብ ይኖርበታል። “ማን ምን ያደርጋል፣ ማንስ ምድራዊ ኃይል ይደርስልኛል” የሚለው ተስፋ አስቆራጭ ስሜት በእነሱም ላይ መሠራጨቱ ስለማይቀር፣ ከቻሉ ራሳቸው ለሕግ እንዲያቀርቧቸው፣ ካልቻሉም እንዲጠቁሙ፣ አሊያም ሊያገሏቸው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
እንዲህ ዓይነት ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ የሚጠበቅበት አካል፣ በቅድሚያ የደበቃቸው አካል ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲያበቃ፣ የሠሩትንና ሊሠሩም የሚችሉትን በማስረጃ እያስደገፈ ደጋግሞ ለማኅበረሰቡ ማሳወቅ ይኖርበታል። እንደዜጋ የእነሱ ሥራ ኹላችንንም ኢትዮጵያውያንን የሚያሳፍር ቢሆንም፣ ዝም ተብሎ እስካሁን ይደበቅላቸው እንደነበረው ከመሸፋፈን ይልቅ፣ ዓለም ለይቶ እንዲያውቃቸውና ደጋፊዎቻቸው ራሳቸው ድጋፋቸውን እንዲያጡ እስኪሰለች ደጋግሞ በመሥራት ከጎናቸው የሚቆሙትን ማመናመን ከመንግሥትም ይጠበቃል። ጉልበትን ተጠቅሞ ወደ ሕግ ለማቅረብ ከመሞከር በፊት፣ ልጃችንን ብሎ ግፈኛን ለማስጣል የሚሞክር አካል እንዳይኖር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወን ይኖርበታል። “ጦር ያልፈታውን ወሬ ይፈታዋል” እንደሚባለው፣ በመጀመሪያ በሐሳብ ማሸነፍና ዕርቃናቸውን አስቀርቶ የደበቃቸው ለራሱ ሲል እንዲያጋልጣቸው፣ አሊያም እንዳይከላከልላቸው ማድረግ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ይቀንሰዋል።
በሌላ በኩል፣ ወቅቱ የጦርነት እንደመሆኑ በየትኛውም ወገን የጦር ምርኮኛ እንደሚኖር ይጠበቃል። በዓለም አቀፍ ሕግም ይሁን በኢትዮጵያዊ ሥነ-ልቦና እስረኛ ልሁን ብሎ እጁን አሳልፎ የሰጠ ምርኮኛ ደኅንነቱ ሊጠበቅ ይገባል። የአሸባሪ ቡድን አባል ሆኖ ተገዶም ይሁን ሳይገደድ ለተሳተፈበት ድርጊት፣ ሰዎችን ፈርቶ ቢገባም ሕግን ባለመፍራቱ ብቻ ከፍትሕ ሊያመልጥ አይችልም። ዕድሜው ያልደረሰ በሚልም ሆነ ተገዶ እንደገባ ደጋግሞ በመደስኮር ተጠያቂነት እንዳይኖር የሚደረግ ከሆነ በተመሳሳይ እንዲያ ዓይነት ተግባር በሌሎች መሰሎቻቸው እንዲፈጸም መመልመያና መፈልፈያ መንገድ እንዳይሆን መጠንቀቅ ግድ ይላል።
ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው በዓለም አቀፍ ሕጎችም ሆነ በሞራል፣ አንድ የጦር ምርኮኛ ምስሉ በአደባባይ ተለቆ መቀስቀሻ መሆን እንደማይገባ ይታወቃል። ይህ ዓይነት መርህ በጦርነት ወቅት ተፈፃሚ ከመሆኑ ይልቅ፣ በማንኛውም ወገን ሲጣስና በተቃራኒው ሲደረግ ይስተዋላል። ይህ ቢሆንም ግን ለአስከሬን ከሚደረገው ክብርና ጥንቃቄ በላይ፣ ለምርኮኞችም መደረግ እንዳለበት ግልጽ ነው። የተማረኩት ከሚደረግላቸው እንክብካቤ አንጻር ብዛታቸውን በመደዳም ሆነ አሰልፎ ማሳየቱ ሌሎችን ለመጋበዝም ሆነ ለማስፈራራት ተብሎ የሚደረግ ተግባር ስለሚሆን፣ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች በማንም ይፈጸሙ ከኢትዮጵያዊ ሥነ-ልቦና ያፈነገጡ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ታምናለች።
የምርኮኛ ማንነት መደበቅ አለበት የመባሉን ያህል ደግሞ፣ በተቃራኒው ከመካከላቸው ከባድና ዘግኛኝ ግፍ ፈጽመው በምርኮኛ ሥም ተደብቀው የሚጠብቁ ይኖራሉ በሚል ምስጢራዊነቱን የሚቃወሙት አሉ። የምርኮኛ ልውውጥ ይኖራል በሚል ተስፋም ይሁን በምህረትና በይቅርታ በጅምላ እንለቀቃለን በሚል ተስፋ፣ የሠሩትን ደብቀው ለማለፍ እስር ቤቶችንም ሆኑ ለይቶ ማቆያዎችን መሸሸጊያ የሚያደርጉ ይኖራሉ። ሌባ የሰረቀውን ዕቃ ተሰራቂው ቤት ውስጥ ይደብቃል ተብሎ ስለማይገመት፣ የጠፋበት ሰው ዕቃውን ቤቱ ውስጥ እንደማይፈልገው ኹሉ፣ ግፍን በማን አለብኝነት ፈጽመው ሠላማዊ ኑሮ እንቀጥላለን ብለው የሚያስቡ በማይገመት ቦታ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሊታሰብ ይገባል።
ተማርከው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ከሚገኙት መካከል በሕፃናትና አዛውንት፣ እንዲሁም በመነኮሳትና ባለትዳሮች ላይ አስገድዶ የመድፈር ተግባርን የፈጸሙ ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ግፉ የተፈጸመባቸው የማኅረሰብ ክፍሎች በቀላሉ ዐይተው ሊለዩአቸው የሚችሉበት ዘዴ መመቻቸት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።
በየገጠሩ የተፈጸመበትን ግፍ ደብቆ የሚጠብቀው የሕብረተሰብ ክፍል ብዙ ሊሆን እንደሚችል ከማኅበረሰቡ ባህል ተነስቶ መገመት ስለሚቻል፣ እስረኞቹ ባሉበት ተጎጂዎቹ ተገኝተው እንኳን በአካል እያዩ ለመለየት ኹኔታዎች ቢመቻችላቸው እንኳን፣ በአደባባይ ከሆነ እንደሚቸገሩ ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት በየቦታው በማይገለጽ ቦታ በከፍተኛ ጥበቃ ሥር ያሉትን ጨምሮ፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም ምስላቸውን የያዘ ዝርዝር መለያ በዘመናዊ መልክ ተዘጋጅቶ ወደ አንድ የመረጃ ቋት መካተት ይኖርበታል። የተጠርጣሪውንም ሆነ የተበዳዩን ድካም በቀነሰ መልኩ መንግሥትንም ከከፍተኛ ወጪ የሚያስቀር እንዲህ ዓይነት ዘዴ ሊዘጋጅ እንደሚገባው አዲስ ማለዳ ትጠቁማለች።
ምርኮኞቹም ሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ከመታሠራቸው በፊት የነበራቸውን ገጽታ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መቀየር ሳይችሉ፣ የበፊት ምስላቸውንና የነበሩበትን አካባቢ በቀላሉ በመለየት ለተበዳዮቹ ቀላል በሚሆንበት ልክ ማመቻቸት ይጠበቃል። በደል ለተፈጸመባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የጥቆማውንም ሆነ የመመስከሩን ሒደት ማቀላጠፍ የሚቻለው በቂ የሰው ኃይል፣ ባለሙያና አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ቅድሚያ መስጠት በመቻል ነው። በዚህ ረገድ ፍጥነት ዋናው መስፈርት ሆኖ የተበዳይ ምሬት ሳይጨምር የምስክርም ትውስታ ሳይደበዝዝ መሆን እንዳለበት ይታመናል።
እንዲህ ዓይነት ግፈኞችን ለይቶ ለፍትሕ ለማቅረብ በአፋጣኝ ሥራው ካልተጀመረ፣ በዳዮቹ እንዲሸሹ እድል ከመስጠቱ ባሻገር፣ የተበደሉትም ተስፋ እንዲቆርጡና እየተሠማ እንዳለው ራሳቸውን እንዲያጠፉ ጭምር ሊያደርጋቸው ይችላል። ማፈር ያለበት ግፍ ፈጻሚው ተጸጽቶ ራሱን ባላጋለጠበት ኹኔታ፣ ተበዳዮች በማኅበረሰቡም ሆነ በፍትሕ ሥርዓቱ ተስፋ የቆረጡ እንዳይሆኑ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃዎች ወደሩጫ መለወጥ ይኖርባቸዋል።
እንደ አዲስ ማለዳ ዕምነት በግፈኞች ላይ ሊወሰድ የሚገባ ቅጣት የማያዳግም ብቻ ሳይሆን፣ ሌላውም እጅግ ፈርቶ ግፍን በምንም ምክንያት እንዳይፈጽመው የሚያደርግና ኹሉንም ከተመሳሳይ ተግባር የሚያቅብ መሆን አለበት። ወገኔ ዘመዴ በሚል ምንም ዓይነት መድሎ ሳይኖር የሚካሄድ ፍትሐዊ የሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ፣ በግል የሚወሰዱ የአጸፋ ዕርምጃዎችን ከማስቀረቱ ባሻገር፣ ሥርዓት አልበኝነት ተስፋፍቶ ድርጊቱ እንዳይደጋገም ያደርጋል። “ዐይንን ያወጣ ዐይኑ ይውጣ” በሚል ኹላችንም ማየት የምንችል ዕውር ሆነን የጋራ ጠላቶቻችን መቀለጃ ከመሆናችን በፊት፣ አጥፊዎችን በሚያስተምር መልኩ ተቀጥተው፣ የበደሉትን ማኅበረሰብ በኃብትም ሆነ በጉልበት እንዲክሱ ሊደረግ ይገባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



