ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ተቋም (CPJ) ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት በ2021፣ 24 ጋዜጠኞች ሲገደሉ 293 ደግሞ ታሥረዋል ብሏል።
በዚሁ ዓመት በአጠቃላይ 293 ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት የታሠሩ ሲሆን፣ ከዓለማችን ቻይና ብዙ ጋዜጠኞችን ስታሥር፤ ከአፍሪካ ደግሞ ግብጽ ቀዳሚ ሆናለች ተብሏል። ይህም በታሪክ ብዙ ጋዜጠኞች የታሠሩበት ዓመት መሆኑን ነው ተቋሙ በሪፖርቱ ያመለከተው።
ቻይና 50 ጋዜጠኞችን በማሠር ቀዳሚ ስትሆን፣ ማይናማር 26 እንዲሁም ግብጽ 25 ጋዜጠኞችን በማሠር ቀዳሚ የዓለማችን አገራት ናቸው ይላል ሪፖርቱ።
መንግሥታት መረጃን በማፈን መጠመዳቸውና ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚዲያ ነጻነት ችግር ውስጥ መሆኗም ተመላክቷል።
ባለፈው ዓመት በሙያቸው ምክንያት ለእሥር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ብዛት 280 የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ቁጥሩ በ13 መጨመሩን ሪፖርቱ ያሳያል።
ቬትናም፣ ቤላሩስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአንጻራዊነት ብዙ ጋዜጠኞችን በሙያቸው ምክንያት ያሠሩ አገራት ናቸው።
በአፍጋኒስታን፣ በሜክሲኮ እና በማይናማር ጋዜጠኞች በዘገባ ላይ እያሉ በጸጥታ ኃይሎች ተገድለው ሕይወታቸው እንዳለፈ ተቋሙ በሪፖርቱ ገልጿል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014


