የኅዳር ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33 በመቶ ሆኗል

0
607

የኅዳር ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ33.0 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የምግብ ዋጋ ግሽበት የኅዳር ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ38.9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

በተያዘው ወር በእህሎች፣ በአትክልትና ጥራጥሬ ዋጋ በአብዛኛው ቅናሽ አሳይቷል። ሩዝ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽንብራና ምሥር የዋጋ ቅናሽ አሳይተዋል። በተጨማሪም ሥጋ፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላል፣ ቅመማ ቅመም (በዋናነት ጨውና በርበሬ) ቅናሽ አሳይተዋል። የምግብ ዘይትና ቅቤ በመጠኑ ቅናሽ ያሳዩ ሲሆን፣ በአንፃሩ ቡናና ለስለሳ መጠጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የ‹ኢንዴክሱ› ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ ጫት፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ኪዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰጌጫዎች)፣ ሕክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው።

በክልል ደረጃ ሲታይ በኅዳር ወር በአዲሰ አበባ ከተማ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር የዋጋ መቀነስ ሁኔታ ታይቷል።

አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ጥቅምት ወር 2014 ጋር ሲነጻጸር በ0.6 ነጥብ ከመቶኛ እና የምግብ የኢንደክሱ ክፍሎች በ1.7 ነጥብ ከመቶኛ ቅናሽ አሳይተዋል። በተመሳሳይ ወቅት የምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት በ1.0 ነጥብ ከመቶኛ ጭማሪ አለው። ባለፈው ወር 34.2 በመቶ ከደረሰ በኋላ፣ በኅዳር 2014 ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 33.0 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የኅዳር 2014 ወራዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1.8 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት 1.0 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የረዥም ጊዜ ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት አዝማሚያ እንደሚያሳየው ከመኸር ወቅት የግብርና ምርት ጋር በተያያዘ በሚቀጥሉት 3 ወራት የምግብ ዋጋ ይቀንሳል ተብሎ ይገመታል።
መረጃው የተገኘው ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here