የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል በደሴና በኮምቦልቻ ከተሞች የነበሩት መጋዘኖቹ በህወሓት ኃይሎች በመዘረፋቸው በአካባቢዎቹ የምግብ ዕርዳታ ማቅረብ ማቋረጡን አስታውቋል።
የዕርዳታ ምግብ ተከማችተውባቸው የነበሩት መጋዘኖቹ በታጣቂዎቹ በተዘረፉበት ወቅት በሥፍራው የነበሩ ሠራተኞቹ መሣሪያ ተደግኖባቸው እንደነበረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት እንደገለጸው፣ በመጋዘኖቹ ላይ በአማፂያኑ በተፈጸመው ዝርፊያ በምግብ ዕጥረት ለተጎዱ ሕፃናት የሚቀርቡ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ አቅርቦት ክምችት ከመጋዘኖቹ ተወስደውበታል።
በሥፍራዎቹ የነበሩ ሠራተኞቹም በጦር መሣሪያ ጭምር ጫናና ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው ይህንን ዝርፊያ ለመከላከል ሳይችሉ መቅረታቸውም ነው የተነገረው።
ዝርፊያው በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በምግብ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ በሆነበት በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግርና የተመጣጠነ ምግብ ዕጦትን የበለጠ እንደሚያባብሰው ድርጅቱ ተናግሯል፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን ከሳምንት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014


