ዘራፊው ሌላ ተከልካዩ ሌላ!

0
534

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጊዜ አንስቶ አንድ ጊዜ አልቻልኩም፤ አንድ ጊዜ መኪኖቼ ቀሩ እያለ ዕርዳታ መስጠቱ እንደተስተጓጎለ ሲናገር መቆየቱ ይታወሳል። የሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማድረስ የማደርገው ጥረት ተስተጓጎለ እያለ፣ የተለያየ አካላትን ተጠያቂ ሲያደርግ የቆየው ይህ ተቋም ስሞታም ሲቀርብበትም ነበር።

በመንግሥት አሸባሪ ተብሎ ለተፈረጀው ቡድን ዕገዛ ያደርጋሉ የተባሉ የዓለም አቀፉ ድርጅት ሠራተኞች ስሞታ ሲቀርብባቸው ከአገር ሲታገዱም ቆይተዋል። ይህ ቢሆንም ግን፣ ዕርዳታ ማከፋፈሉን አቁሜያለሁ ሲል ራሱ አምርሮ እንደሰሞኑ አልተናገረም ተብሏል። በያዝነው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ኮምቦልቻና ደሴ የማከፋፍለውን ዕርዳታ አቋርጫለሁ ማለቱ ብዙዎችን አነጋግሯል።

ታጣቂዎች አስፈራርተው የመጋዘን ሠራተኞችን አልፈው የዕርዳታ እህል ስለዘረፉ ከእንግዲህ በኹለቱ ከተሞች የማከፋፍለው ዕርዳታ አይኖርም ማለቱ ብዙዎችን አስገርሟል። አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ከተሞቹን እንዲለቅ ከተገደደ በኋላ ቀናትን አልፎ ስለተዘረፍኩ ማደል አቁሜያለሁ ማለቱን ብዙዎች ተችተዋል። ውሳኔው አልዘገየም ወይ በሚል አሁን መረዳት ያለበት ሕብረተሰብ ሲቀር ማቋረጡ ተገቢ አይደለም ብለው ስሙ በእንጥልጥል ላይ የቀረውን ተቋም ያብጠለጠሉ በርካቶች ናቸው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይህን የማቆም ውሳኔ የወሰደው የሚለግሰው እህል ሁሉም ተዘርፎበት በማለቁ እንዳልሆነ ምክንያቱ ያልጣማቸው ግለሰቦች መላምታቸውን እያስቀመጡ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ተቋሙ ሠራተኞቹን በመሣሪያ አፈሙዝ አስገድደው የወሰዱት ታጣቂዎች የህወሓት መሆናቸውን ጠቁሟል። ይህ ቢሆንም፣ ታጣቂዎቹ ከወጡ ከቀናት በኋላ ዘራፊዎቹ በሌሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ተረጂዎችን ለመርዳት ቀሪ እህሉን እንደማያከፋፍል መናገሩ ታውቋል።

የተዘረፈው መጠን በጣም ብዙ ነው ከማለት ውጭ ምን ያህል እደሆነ ያላሳወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የሕፃናት አልሚ ምግብና የተለያዩ ለተጎጂዎች ተብለው ታስበው የተከማቹ እህሎች መዘረፋቸው ተናግሯል። ይህ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ሳይዘረፉ ከተሰረቀባቸው ሰዎች ላይ አስቀርቶ ጭራሹኑ መከልከሉ ተገቢ አይደለም በሚል ብዙዎች ሐሳቡን ሞግተዋል። አለመስጠት መብታቸው ነው ያሉ አንዳንዶች፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንደመታሰቡ እነሱም ታጥቀው እንዲዘርፉ መደረግ የለበትም ብለዋል። የራበው ማኅበረሰብ በመጋዘን የተከዘነ ምግብ እንዳለ እያወቀ ጠላቴ ብሎ በሚያስበው ድርጊት እንደተከለከለ ሲያውቅ ምን ይላል በሚል ሥጋታቸውን ያስቀመጡም አሉ።

አንዳንድ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ የሰጡ ፣የተዘረፈበት ቀን ለውሳኔው ወሳኝ ነው ሲሉ ዘራፊና አዘራፊ ተስማምተው ተረጂን ለመለየት የተጠቀሙበት ነው በሚል ጉዳዩን ወደሴራ ደረጃ ለማሳደግም ሞክረው ነበር።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here