ከሰዎች የእለት ተእለት የኑሮና የሕይወት እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ነው፣ ግብይት። ሻጭና ገዢ በገበያ ይገናኛሉ። ለዚህም መገናኛ የሚሆን ቦታና ጊዜን ይሰይማሉ። ሥልጣኔና ዘመናዊነት እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ ታድያ መደበኛ የግብይት ስፍራዎች በቋሚነት ተሠርተዋል።
በአገራችን ገበያ የምንላቸውን እነዚህን የግብይት ስፍራዎች አርብ አገራት ‹ሱቅ›፣ ፐርዢያዎች ‹ባዛር›፣ በጥንታዊት ግሪክ ‹አጎራ›፣ በስፔን ደግሞ ‹መርካዶ› እየተባሉ ይጠራሉ። በገበያ ከእለታዊና መሠረታዊ ፍጆታ አንስቶ የቅንጦት እስከሚባሉ እቃዎች ድረስ ይሸጣሉ፣ ይገዛሉ።
የገበያ ቦታ አመሠራረት የሰው ልጅ ግብይትን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አብሮ የዘለቀ እንደሆነ ይነገራል። ጥንታዊ ባዛር (ገበያ) ከፐርዢያ ተነስቶ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ብሎም ወደ አውሮፓ እንደተስፋፋ ይነገራል። ከዛ ጊዜ በኋላ የተለያዩ አገራት የራሳቸው የሆነ የግብይት ቦታን እየፈጠሩ አሁን ዓለማችን ወደደረሰችበት የድረ ገጽ ግብይት (online market) ዘልቀዋል።
የኢትዮጵያ የግብይት ታሪክ ከሌላው ዓለም ክፍል የተለየ አይደለም። ኢትዮጵያ በጥንት ዘመን በነበሯት ገዢዎች አማካኝነት ሰፋ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ታደርግ እንደነበር የተለያዩ ሰነዶች ያሳያሉ። ይህም በአፍሪካ ብሎም ከብዙ የዓለም አገራት ቀደምት ያደርጋታል።
በጥንታዊ አክሱም ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ በሰፊው ወርቅ፣ የዝሆን ጥርስ፣ የኤሊ ቅርፊት እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን ወደተለያዩ የዓለም አገራት ትልክ ነበር። በምትኩም ሐር እንዲሁም የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን በብዛት ታስገባ እንደነበር ይነገራል። እነዚህንና በርካታ ግብይቶችንም ከሕንድ እንዲሁም ከሜዲትራኒያን አገራት ጋር የምታደርጋቸው ነበሩ።
ስለታታላቅ ገበያዎች
በተለያዩ ጊዜያት የዓለም አገራት የንግድ ታሪኮች ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበራቸው ታላላቅ ገበያዎች አሉ። እነዚም ዘለግ ያለ እድሜን ያስቆጠሩ እና ታሪካዊ ናቸው። እዚህ ላይ ኹለት ገበያዎችን በጥቂቱ እናነሳለን። አንደኛው ‹የኢስፋሃን ባዛር/ገበያ› የሚባለው ገበያ ነው። ይህም የሚገኘው በኢራን ሲሆን የተገነባው በ1620 ነው።
ይህ ገበያ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ ባዛሮች ጥንታዊውና ታላቁ ነው። የዚህ ባዛር የጣራ ከፍታም በዓለማችን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነው። አብዛኛውን ጊዜ በጎብኚዎች የተጨናነቀ ሲሆን ውብ የሚባሉ የፐርዢያ የእጅ ሥራ ውጤቶች የሚገኝበትም ነው።
ኹለተኛው ‹ታላቁ የአስታንቡል ባዛር/ገበያ› ነው። ይህ ገበያ በቱሪክ ኢስታንቡል ከተማ የሚገኝና ሰፊ ቦታን የሚሽፍን ገበያ ነው። ለጨርቃ ጨርቅ ግብይት ታስቦ በ1455 የተጀመረውና በ1560 ግንባታው የተጠናቀቀው ይህ ገበያ፣ በውስጡ ከአራት ሺሕ በላይ ሱቆችን የያዘ ነው። በአሁን ጊዜ ቦታው በየእለቱ ከ250 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ የሚደርሱ ጎብኚዎችን ያስተናግዳል።
ወደ አገራችን ስንመለስም ዘመናትን የተሻገሩ፣ ትውልድ የተጋራቸውና አሁንም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ገበያዎች ይገኛሉ። እነዚህም የግብይት ቦታዎች ሥያሜቸውን የተለያዩ ሁኔታዎችን መሠረት አድረገው አግኝተዋል። ለምሳሌ ገበያው ክፍት በሚሆኑበት ቀን መሠረት አድርገው አርቢት፣ ሐሙሲት፣ ቅዳሚት ተብለው የተሰየሙ ገበያዎች ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በገበያው በብዛት በሚቀርበው ምርት ሥያሜ ይሰጣቸዋል። ከሌሎች አገራት በተለያየ አጋጣሚ በተውሶ የመጡ፣ በግለሰቦች ሥም የሚጠሩ ገበያዎችም በተመሳሳይ አሉ።
አዲስ አበባ እና እድሜ ጠገብ ገበያዎቿ
በአዲስ አበባ ከተማ በርከት ያሉ ዘመናትን ያስቆጠሩ ገበያዎች ይገኛሉ። አጎዛ ገበያ ከእነዚህ ገበያዎች መካከል ነው። ይህ ገበያ 126 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።‹‹ከእንጦጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ› የተሰኘው የዳሰሳ ጥናት መጽሐፍ አዘጋጅ ብርሀኑ ሰሙ የአካባቢውን ሰዎች ዋቢ አድርጎ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው፤ አጎዛ ገበያ መጠሪያ ሥያሜውን ያገኘው አጎዛ ቦረዳ ከተባሉ ታዋቂ ነጋዴ ነው።
ከቅርብ ዓመት ወዲህ የተመሠረተው የአጎዛ ገበያ አክሲዮን ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ አበባው በየነ ይህን ነጥብ አረጋግጠዋል። አጎዛ ቦረዳ የከፋ ተወላጅ ሲሆኑ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ1778 ነበር በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። ያኔ ካዛንችስ ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስተያን አካባቢ ሰፋ ያለ የጉሊት ንግድ ከነበራቸው ግለሰቦች ዋነኛው እንደነበሩ ይነገራል፣ አጎዛ።
ሆኖም በ1960ዎቹ ከቅዱስ ዑራኤል ካዛንቺስ ድረስ ያለው መንገድ የአስፋልት መንገድ ሲዘረጋለት የጉሊት ገበያቸው እንዲነሳ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ገበያው የእርሳቸውን ሥም እንዲይዝ ያደረገው አጎዛ ራሳቸው የተለያዩ እንስሳትን ቆዳ ወይም በጊዜው ‹አጎዛ› የሚሸጡ በመሆኑ ነው።
አፀደ ምላሹ ከኃይለሥላሴ ዘመን ማብቂያ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አስቀድሞ በአጎዛ ገበያ ሥራ እንደጀመሩ ያስታውሳሉ። እኚህ እናት እንደ ብዙዎቹ የአጎዛ ገበያ ነጋዴዎች እድሜ የተጫናቸው ናቸው። አዲስ ማለዳ ‹‹እድሜዎ ስንት ነው?› ስትል ጠይቃለች። እርሳቸውም ‹‹እባክሽ ዓመተ ምህረት አትጠይቂኝ›› አሉ ቆጣ ካሉ በኋላ፣ ‹‹…ብቻ ከ75 እስከ 80 አይሆንም ብለሽ ነው?›› አሉ በጥርጣሬ እና እርግጠኝነት ባጣ ስሜት።
አፀደ ለእድሜ መግፋት እጅ አልሰጡም፤ አሁንም ይነግዳሉ። ጥንት በሜዳ ላይ እንደነበሩ ያወሱ ሲሆን አሁን ግን ሱቅ አላቸው። ታድያ በዚህ ሱቃቸው ቡና እና ጥራጥሬ እህሎችን ከገበሬ እየተረከቡ ለተጠቃሚ በችርቻሮ ይሸጣሉ።
ብዙ የአጎዛ ነጋዴዎች እንደ አፀደ እድሜና ኑሮ ፈትኗቸዋል። ‹ያኔ› እያሉ በሚጠሩት የወጣትነትና ጉልምስና ጊዜያቸው በአንድ ብር ስምንት እንቁላሎችን፣ በአምስት እና በስድስት ብር ዶሮ ይሸጡ የነበሩ በገበያው ይገኛሉ። አሁን ገበያው እንደድሮው አይደለም። ከፍ ያለ ዋጋ ይተመናል፣ ወጪውም በዛው ልክ ከፍ ብሏል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እናቶችና ጥቂት አባቶች የአጎዛ ገበያ ነጋዴዎች፣ ገበያው ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፉበት እና መስዋዕትነትን የከፈሉበት አንደሆነ ይናገራሉ። አሁን ላይ ገበያው የከተሞች መስፋፋት እና የመሠረተ ልማት ማደግን ተከትሎ የተለያዩ ችግሮች ገጥመውታል። ‹‹የተዘረጋው የባቡር ሀዲድ ከደንበኞቻችን ጋር እንዳንገናኝ አድርጎናል›› ይላሉ፤ ብዙዎቹ። በዚህ የተነሳ የነበሯቸውን ታማኝ ደንበኞች ማጣታቸውን አልደበቁም። ለዚህም መፍትሄ ለማግኘት በተወካዮቻቸው አማካኝነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
አስኮ ጨረታ
ይህ ገበያ በዋነኝነት የተጀመረው ቤት ለቤት እየዞሩ እቃን በልብስ ይለውጡ በነበሩ በተለምዶ “ልዋጭ” የሚል በሚታወቁ ነጋዴዎች አማካኝነት ነው። ልዋጮች በየሰፈሩ እየዞሩ አስቀድሞ ግልጋሎት ላይ የዋሉ አልባሳትን ከግለሰቦች ላይ በመረከብ በምትኩ ቀለል ያሉ የቤት ቁሳቁሶችን ይለውጣሉ። ቀጥለውም የሰበሰቧቸውን አልባሳት የሚጠገነውን ጠግነው ለሌላ ለባሽ ተመጣጣኝ በሚባል ዋጋ ያቀርቡታል።
የገበያው ጅማሬ በኮልፌ አጠና ተራ ገበያ እንደነበር ይነገራል። በዚህ መልኩ የግለሰቦችን አልባሳት በመሰብሰብ የተጀመረው ንግድ በኋላ ላይ አልባሳት ከድሬዳዋ በቦንዳ (በብዛት) መግባት ሲጀምሩ እየሰፋ ሄዷል። ሰልቫጅ (ልባሽ ጨርቅ) በቦንዳ እየታሰረ መምጣት ሲጀምር ከልዋጮች በተጨማሪ ትላልቅ እና ልምድ ያላቸው ነጋዴዎችን መሳብ ችሏል። ቀጥሎም በ1983 የነበረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በርከት ያሉ ግለሰቦች ወደዚህ ንግድ መቀላቀላቸውን ‹ከእንጦጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ› የተሰኘው መጽሐፍ ያስረዳል።
ይህ ገበያ ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውታል። ረዘም ያለ ጊዜ ቋሚና የተወሰነ ቦታ አልነበረውም። በተጨማሪም ከሕጋዊነት ጋር በተያያዘ አብዛኛዎቹ የሰልባጅ አልባሳት ምንጭ ኮንትሮባንድ (ሕገወጥ ንግድ) ስለሆነ በተለያየ ጊዜ በመንግሥት እርምጃ ይወሰድበት ነበር። ገበያው አሁን ያለበትን ቦታ ማግኘት የቻለውም በ1990ዎቹ እንደሆነ ይነገራል። የአስኮ ጨረታ ነጋዴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ንግዱን እያካሄዱ ይገኛሉ።
ታይዋን ገበያ
እንደ አስኮ ጨረታ ሁሉ ታይዋን ገበያም በኮንትሮባንድ ንግድ አማካኝነት እውቅና የተነፈገው ገበያ ሆኖ ረዘም ያሉ ዓመታትን የዘለቀ ነው። በገበያው አመሠራረት ዙሪያ አንድ ወጥ የሆነ ታሪክ የለም። የመርካቶ ራጉኤል ገበያ ሲቃጠል ከዛ የተፈናቀሉ ነጋዴዎች ናቸው የመሠረቱት የሚሉ አሉ። በአንጻሩ ከመርካቶ ሞላ ማሩ አካባቢ የተባረሩ ነጋዴዎች የተሰባሰቡበት እንደሆነ የሚናገሩ ይገኛሉ። የተወሰኑ ደግሞ በ1970ዎቹ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ በባቡር በመመላለስ የኮንትሮባንድ ንግድን ያስፋፉ የንግድ ሰዎች የመሠረቱት እንደሆነ ይናገራሉ።
የገበያውን ምሥረታ በሚመለከት ታድያ ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ታሪክ ማግኘት ከባድ እንደሆነ ‹ከእንጦጦ ሀሙስ ገበያ እስከ መርካቶ› መጽሐፍ ያስረዳል። በዚህ ገበያ የጨርቃ ጨርቅ፣ የኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም የመዋቢያ እቃዎች በኮንትሮባንድ ገብተው በሰፊው ለሽያጭ ይቀርቡ ነበር።
በአዲስ አበባ ከላይ ሰፋ አድርገን የተመለከትናቸው ነባር ገበያዎች ጨምሮ በዛ ያሉ ገበያዎች ይገኛሉ። ብዙ የተባለላቸውን መርካቶና ሾላ ገበያን ማንሳትም ይቻላል። በ1970ዎቹ በመርካቶ የንግድ እንቅስቃሴው በመብዛቱ የተነሳ ሁሉም በየአካባቢው እንዲገበያይ ተወስኗል። ይህም እንደምክንያት ሆነና በመላው የመዲናይቱ ክፍሎች በርከት ያሉ ገበያዎች ተጀመሩ።
ሽሮሜዳ፣ ቄራ፣ ሳሪስና ፈረንሳይ ገበያዎች የዚህ ውጤቶች ናቸው። በአመዛኙ ድሮ የነበሩ ገበያዎች አሁንም አሉ። ገሚሶቹ ሲመሠረቱ የነበራቸውን ቅርጽ ሳይቀይሩ የነጋዴዎቹም ኑሮ ሳይቀየር ባሉበት እየረገጡ፣ ነጋዴዎቹም ሕይወት ከብዷቸው አሁንም አሉ። እንደመርካቶ ያሉት ደግሞ ዘመናቸውን እየመሰሉ እያደጉ ለግብይት ብቻ ሳይሆን ለጉብኝትም የሚበቁ ዓይነት ሆነው ቀጥለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



