የኢትዮጵያ ቱሪዝም ለኢኮኖሚው ዘርፍ የሚያበረክተው አስዋጽዖ ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት በነበሩት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያስመዘገበ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ከተጠቀመች ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ፣ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘረፍ ተደራራቢ ችግሮች ተጭነውታል። በዚህም በዕድገት ላይ የነበረው የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ወደ ኋላ እየተጓዘ ነው። የዘርፉ ዕድገት የተገታው መጀመሪያ በኮቪድ-19 ሲሆን፣ ኮቪድ-19 ካስከተለው ፈተና በማገገም ላይ የነበረው የቱሪዝም ዘርፉ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሌላ ፈተና ሆኖበታል።
ጦርነቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲቋረጥ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መውደማቸው ችግሩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርጎታል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ዘርፉ ያስተናገደውን ችግር በማንሳት፣ የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብትነት የምትጠቀማቸው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ጥብቅ የማኅበረሰብ ሥፍራዎች፣ ብርቅየ የዱር እንሰሳቶች እና የማይዳሰሱ ደማቅ የማኅበረሰብ በዓላት ያሏት አገር ናት። እነዚህን ሀብቶች ለመጎብኘት ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
ይሁን እንጅ ሳይጠበቅ ተከስቶ የዓለምን ኢኮኖሚ የተፈታተነው ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሠተበት 2012 ወዲህ የኢትዮጵያ ቱሪዝም በእጅጉ እየተፈተነ ነው። በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 መከሠቱን ተከትሎ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቶ፣ ባሳለፍነው 2013 በጄት ዓመት ከውጭ ጎብኝዎች ይገኝ የነበረውን ውጭ ምንዛሬን በከፍተኛ መጠን ማሳጣቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም መፈተን የጀመረው ኮቪድ ከተከሰተበት 2012 ጀምሮ ሲሆን፣ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ከፍል በ2013 መጀመሪያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሌላ ተደራቢ ፈተና ገጥሞታል።
ኮቪድ-19 በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ባሳደረው ጫና ተጎጅ ከሆኑት መካከል አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ የቱሪዝም መዳረሻ ፓርኮች፣ ጥብቅ የማኅበረሰብ ሥፍራዎች እና በዘርፉ በተሠማሩ ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩ ግለሰቦችና አጋዥ ተቋማት፣ እንዲሁም በቱሪስት መዳረሻ አካባቢ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል።
ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ በገባ በወራት ልዩነት ጉዳት ካጋጠማቸው የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ተቋማት መካከል፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ 98 በመቶ ኪሳራ ውስጥ መግባቱን የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር መግለጹ የሚታወስ ነው። ይህንን ተከትሎ ሆቴሎች የቀጠሯቸውን ሠራተኞች ከሥራ እስከማሠናበት ደርሰው ነበር።
ቱሪዝም የኢትዮጵያን ክፍለ ኢኮኖሚ ከሚደግፉ ዘርፎች አንዱ ቢሆንም፣ በኮቪድ-19 ላይ ተደርቦ የመጣው የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት፣ የውጭ አገር ዜጎች ይበልጥ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ከማድረግ ባሻገር፣ የአገር ውስጥ ጎብኝዎችንም ጉዞ የገታ ሆኗል።
በተከታይ፣ በኮቪድ-19 እና በጸጥታ ችግር የተፈተነው የኢትዮጵያ ቱሪዝም፣ በጎብኝዎች እንቅስቃሴ መቋረጥ ካጣው ገቢ በተጨማሪ፣ ከአንድ ዓመት በላይ በተካሄደው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት የቱሪስት መዳረሻዎች በጦርነቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባለፈው ሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጿል።
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በደረሰባቸው አማራ እና አፋር ክልሎች የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎችን ማጥፋቱ ተገልጿል። ከደረሱት ጉዳቶች መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን በሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች ላይ ብቻ ባደረሰው ጉዳት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱ ተጠቁሟል። የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ በሠጠው መግለጫ፣ የህወሓት ቡድን ወረራ ባደረገባቸው የአማራ እና አፋር ውስን አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ የደረሰውን ሙሉ ጉዳት ለመለየት ጥናት እንደሚደረግ ተገልጿል።
መንግሥት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ብቻ በስድስት የኃይማኖት ተቋማት፣ ኹለት የባህልና ቱሪዝም ተቋማት፣ በ22 የቱሪዝም አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ላይ ህወሓት ጉዳት አድርሷል። የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከጎብኝዎች ያገኝ የነበረውን ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በዚሁ ጦርነት ማጣቱም ተገልጿል።
ፈተና የበዛበት የቱሪዝም ኢኮኖሚ
የኢትዮጵያ ቱሪዝም የአጠቃላይ ኢኮኖሚው አንድ ዘርፍ ሲሆን፣ ዘርፉ አሁን ላይ በድርብርብ ችግሮች እየተፈነ ይገኛል። የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ሚና ዘርፈ ብዙ ሲሆን፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እንዲሁም ከውጭ አገር ጎብኝዎች የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ኢኮኖሚውን ይደግፋል።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች በምትገኘው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ(2013-2022) ላይ ከተቀመጡት ሰባት ዘርፎች ቱሪዝም አንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ የልማት ዕቅድ አካል ሆኖም ተካቷል።
ይሁን እንጅ፣ አሁን ላይ ዘርፉ ኢኮኖሚውን መደገፉ ቀርቶ በራሱ ተደራራቢ ችግሮች ገጥመውታል። በኮቪድ-19 የጀመረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢኮኖሚ ፈተና ከአንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ፣ ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከጎብኝዎች መቋረጥ ጀምሮ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች የጦርነቱ ሰለባ እስከመሆን ደርሰዋል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት፣ ቱሪዝሙን በእጅጉ እንደጎዳው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ቱሪዝም ሥራ ላይ በንቃት ከሚሳተፉት የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል የቱሪዝም ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም አንዱ ነው። የሰሜኑ ጦርነት የኢትዮጵያን ቱሪዝም እንደጎዳው የሚገልጸው ሄኖክ፣ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የውጭ አገር ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የሚመጡበት ዕድል የለም ይላል።
“ቱሪስት ዕምነት ይፈልጋል” የሚለው ጋዜጠኛ ሄኖክ፣ ኢትዮጵያ አሁን በገጠማት ችግር ቱሪስት አመንጭ የሚባሉ አገራት በአገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸው፣ ቱሪስቶቹ ዕምነት ኖሯቸው ለጉብኝነት ወደ ኢትዮጵያ እንዳያቀኑ ያደርጋል ይላል።
የሰሜኑ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መስመር ባለፈው አንድ ዓመት ጉዳት ማስተናገዱን የሚገልጸው ሄኖክ፣ የሰሜኑ የቱሪዝም መስመር ከአዲስ አበባ እስከ ትግራይ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ያቀፈ በመሆኑ ለዘርፉ መጎዳት መሠረት መሆኑን ጠቁሟል።
የሰሜኑ የቱሪዝም መስመር እንቅስቃሴ መቋረጥ በዘርፉ ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ከማሳጣቱ በተጨማሪ፣ በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች ኑሯቸውን ያደረጉ እና በቱሪዝም ዘረፍ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የችግሩ ተቋዳሽ ሆነዋል።
ኑሯቸውን በቱሪዝም ዘርፍ ያደረጉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቱሪዝም መቋረጡን ተከትሎ፣ ለከፋ ችግር እንደተጋለጡ እየተገለጸ ነው። በቱሪዝም ዘርፍ ከሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል የላሊበላ ከተማ ማኅበረሰብ አንዱ ነው። ማኅበረሰቡ ኑሮውን የሚመራው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትን ለመጎብኘት ወደ ቦታው ለሚያቀኑ ጎብኝዎች ከሚሰጠው የአገልግሎት ገቢ ነው።
በዚህም ህወሓት ወደ አማራ ክልል ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ በመቋረጡ፣ አብዛኛው የላሊበላ ከተማ ማኅበረስብ ለችግር መጋለጡ ከሰሞኑ ተሰምቷል። ችግሩ ጎልቶ የወጣው ላሊበላ ከተማ ከህወሓት ነጻ መውጣቷን ተከትሎ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ ለከተማው ማኅበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
የላሊበላ ከተማ ማኅበረሰብ በቁጥር ወደ 70 ሺሕ የሚገመት ሲሆን፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ከቱሪዝም ጋር በተገናኙ አገልግሎቶች የሚተዳደረው ነው። ቀደም ሲል በኮቪድ-19 የተዳከመው የላሊበላ ቱሪዝም፣ ህወሓት በከተማዋ ከአራት ወራት በላይ በመቆየቱ፣ በዘርፉ የሚተዳደረውን ማኅበረሰብ ለከፍተኛ ችግርና ርሀብ ተጋልጦ ሕልውናው አድጋ ላይ ወድቋል ተብሏል። በአሁኑ ወቅት ቦታው ከህወሓት ነጻ በመሆኑ ለዚህ የታሪክ ባላደራና ቅርስ ጠባቂ ለሆነው ማኅበረሰብ በሕይወት ለመድረስ ”አንድ ሰው አንድ ኩንታል” በሚል ስያሜ የድጋፍ አሰብሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ጦርነት ምክንያት የተቋረጠው የቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ እንደ አገር ያለውን እንቅስቃሴ የገታ ቢሆንም፣ ጦርነቱ በተካሄደባቸው በአማራ እና በአፋር ክልሎች የተባባሰ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአስጎብኝ ድርጅት ባለቤት ይገልጻሉ። በኹለቱ ክልሎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለጉብኝት ዝግ መሆናቸውን ተክትሎ፣ ጉዳቱ ከግለስብ አስከ አገር የዘለቀ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጭ ይገልጻሉ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአስጎብኝ ድርጅት ባለቤት እንደሚሉት፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በተለይ በአማራ እና በአፋር ክልሎች መቋረጡን ተከለትሎ አስጎብኝ ድርጅቶች ኪሳራ ውስጥ ገብተዋል ብለዋል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ድርጅታቸው የውጭ አገር ደንበኞቹን በአፋር ክልል ለማስጎብኘት ቀጠሮ ይዞ በጦርነቱ ምክንያት የያዘውን ቀጠሮ መሠረዙን ይገልጻሉ።
የቱሪዝም ጋዜጠኛው ሄኖክ በበኩሉ፣ በሰሜኑ ጦርነት በዋናነት ተጎጅ የሆኑት ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች መሆናቸውን ይገልጻል። አፋር ክልል የሚገኙት ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች የዚህ ጦርነት ሠለባዎች መሆናቸውን የሚገልጸው ሄኖክ፣ በጦርነቱ የቱሪዝም አገልግሎቱ ከመቋረጡ በላይ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መውደማቸው ለዘርፉ ሌላ ፈተና መሆኑን ጠቁሟል።
የተዳከመውን ቱሪዝም ማነቃቃት
በተደራራቢ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከገጠመው ችግር እንዲወጣ አስቸኳይ የማገገሚያ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው ሄኖክ ይገልጻል። ቱሪዝም እያስተናገደ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቀልበስ በተለይ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የማኅበረሰቡን እንቅስቃሴ በፍጥነት እንዲያገግም ማድረግ ይገባል ይላል።
እንደ ላሊበላ ያሉ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጉዳት ያስተናገደውን ማኅበረሰብ በማነቃቃት፣ የወደሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ማልማት መሠረታዊ የቤት ሥራ መሆኑን ሄኖክ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም የኢንሹራንስ አግልግሎት የሌለው መሆኑ ደግሞ በጦርነቱ ጉዳት ያስተናገዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ሥራውን ፈታኝ እንደሚያደርገው የሚገልጸው ሄኖክ፣ በተቻለ መጠን ባለድርሻ አካላት ዘርፉን መደገፍ እንዳለባቸው አመላክቷል።
የቱሪዝም ዘርፉ ከገጠመው ችግር የሚያገግምበት ሁኔታ በአስቸኳይ ካልተሠራ፣ የቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች መዳከምና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ሄኖክ ገልጿል። በመሆኑም ቱሪዝም ከደረሰበት ጉዳት እንዲያንሠራራ የማድረግ ሥራው በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማነቃቃትና መሠረተ ልማቶችን በማልማት ማከናወን እንደሚገባ ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ቱሪስት አመንጭ የሚባሉ አገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በተደጋጋሚ መግለጻቸው፣ ከእነዚህ አገራት የሚመጡ ጎብኝዎች ስለማይኖሩ፣ እንደ አማራጭ ለሌሎች ቱሪስት አመንጭ አገራት ገበያ መፍጠር እንደሚገባ ሄኖክ ጠቁሟል። እንዲሁም የውጭ ጎብኝዎች መቀነስን ለማካካስ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታተት ሌላ አማራጭ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኮቪድ-19 የዓለም ቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደጎዳ የሚገልጸው ሁኖክ፣ የዓለም ቱሪዝም ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም አገራት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን እያጠነከሩ መሆኑን ጠቁሟል። ኢትዮጵያም ችግር የገጠመውን የቱሪዝም ዘርፉን ለማጠናከር የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታታት አለባት ብሏል።
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ፈተና ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት ለቱሪዝሙ መነቃቃት አሰተዋፆዖ ያበረክታል ተብሎ የሚጠበቀው ገናን በኢትዮጵያ ለማክብር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ለአንድ ሚሊዮን ዲያስፖራዎች የቀረበው ጥሪ ነው።
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሚቀጥለው ታኅሳስ 29/2014 የሚከበረውን የገና በዓል በኢትዮጵያ እንዲያከብሩ የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ ከወዲሁ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ተብሏል።
ከዝግጅቶቹ መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገናን በኢትዮጵያ ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን የ30 በመቶ የትኬት ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል። እንዲሁም ሌሎች በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅናሽ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
የገናን በዓል በኢትዮጵያ ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዲያስፖራዎች በቱሪዝም ዘርፉ ላይ መነቃቃት እንዲፈጥሩ ከወዲሁ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ የቱሪዝም ጋዜጠኛው ሄኖክ ይገልጻል። እንደ ሄኖክ ገለጻ ዲያስፖራዎች በቱሪዝሙ ላይ መነቃቃት እንዲፈጥሩ የጊዜ ቆይታ ማራዘምና የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲጎበኙ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሟል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዲያስፖራዎች ለአጭር ቀናት በከተማ ቆይታ አድርገው የሚመለሱ ከሆነ፣ ለቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት እንዲኖረው የሚያበረክቱት ሚና የጎላ እንደማይሆን ሄኖክ ጠቁሟል። በመሆኑም ሊጎበኙ የሚችሉ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማዘጋጀት እና ዲያስፖራዎች ተከፋፍለው የተለያዩ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ማድረግ ይገባል ብሏል።
በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብዛት በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት አንድ ሺሕ 348፣ በ2022 ወደ ኹለት ሺሕ 696 ለማሳደግ፣ እንዲሁም በዚሁ ጊዜ የጎብኝዎችን እርካታ መጠን ከ50 በመቶ ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል።
የአገር ውስጥ ቱሪዝምን በማስተዋወቅና የጉብኝት ባህል እንዲዳብር በማድረግ የጎብኚዎችን ቁጥር በ2012 በጀት ዓመት 23.7 ሚሊዮን በ2022 በጀት ዓመት ወደ 70 ሚሊዮን ማሳደግ፣ እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም የሠለጠነ የሰው ኃይልን ቁጥር በማሳደግ ሠልጥነው አገልግሎት የሚሰጡ ሙያተኞችን ከ23 ወደ 59 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል። በተጨማሪም ዘርፉን በማልማትና በማሳደግ ለዜጎች የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት ከ1.64 ሚሊዮን፣ በ2022 በጀት ዓመት ወደ 5.2 ሚሊዮን ለማሳደግ ታቅዷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



