በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች እና ከወልዲያ ዩኒቨርስቲ በጊዜያዊነት አምቦ ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎች፣ የተመደቡበት ዩኒቨርስቲው እስካሁን ምላሽ እየሰጣቸው ባለመሆኑ ቅሬታ አቀረቡ።
ተማሪዎቹ በ2013 ሲማሩባቸው የነበሩ ዩኒቨርስቲዎች በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በመሆናቸው ትምህርት ሚኒስቴር ወደ አምቦ ዩኒቨርስቲ በጊዜያዊነት ቢመድባቸውም፣ የተመደቡበት ዩኒቨርስቲ ግን እስካሁን ጥሪ እንዳላደረገላቸው ነው ከቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎቹ መረዳት የተቻለው።
በተመሳሳይ ችግር ምክንያት ወደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ ጓደኞቻችን በተመደቡበት የትምህርት ተቋም ተጠርተዋል የሚሉት ተማሪዎቹ፣ እንደ ጓደኞቻቸው ተጠርተው የተቋረጠ ትምህርታቸውን መከታተል ባለመቻላቸው ቅሬታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲው እስካሁን ለምን እንዳልጠራቸው ቢጠይቁም ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት ምላሽ እንዳለገኙ ነው ከተማሪዎቹ መረዳት የተቻለው። በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበን ነበር የሚሉት ተማሪዎቹ፣ በመጨረሻ ከአምቦ ዩኒቨርስቲ ጸሐፊዎች ያገኙት ምላሽ፣ “ጥሪ ሊደረግ የሚችለው ለማስተር ተማሪዎች ነው እንጂ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን አስመልክቶ የደረሰን መረጃ የለም” የሚል መሆኑን ነው የተናገሩት።
ያልተጠራነው በጦርነቱ ምክንያት ነው እንዳንል፣ በአምቦ ዩኒቨርስቲ የሚማሩት ነባር ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ የትምህርት ጊዜያችን እየባከነ በመሆኑ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የመደባቸው ተማሪዎች ተጠርተዋል፤ በመጠራት ላይ ያሉም አሉ ሲሉ ያብራሩት ተማሪዎቹ፤ ለአብነትም ከአክሱም፤ ከአዲግራት እና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲው በኅዳር 27 እና 28፣ 2014 የምዝገባ ጥሪ እንዳደረገላቸው ጠቁመዋል።
እኛም በተመደብንበት ዩኒቨርስቲ ተጠርተን ትምህርታችንን ልንከታተል ይገባል የሚሉት ቅሬታ አቀራቢዎቹ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ ተመድበው ከተጠሩት በተጨማሪ ወደ ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎችም ተጠርተዋል ነው ያሉት።
አያይዘውም፣ በትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ሲማሩ የቆዩና ወደ ድሬዳዋ የተመደቡ ተማሪዎች ባሳለፍነው ኅዳር 23 እና 24/2014 የምዝገባ ጥሪ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት ሚኒስቴር ከወልዲያና ከአክሱም ዩኒቨርስቱ ወደ መቱ ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎች በታኅሳስ አራት እና አምስት 2014 “ለምዝገባ ኑ” ተብለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ አክለውም፣ ወደ ኦዳ ቡልቱ የተመደቡ ተማሪዎችም በተመሳሳይ ማለትም በኅዳር 23 እና 24 ለምዝገባ እንደተጠሩ ነው የጠቆሙት።
ከአዲግራት ዩኒቨርስቲ ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎች በበኩላቸው፣ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የተፈናቃዮች ማረፊያ ሆኗል በመባላቸው አለመጠራታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎቹ በመጨረሻም የተመደብንበት ዩኒቨርስቲ ጥሪ እንዲያደረግልን እናሳስባለን፤ ጥሪ የማያደርግበት ምክንያት ካለው ደግሞ ቁርጡን ያሳቀውቀንና የሚመለከተው አካል መፍትሔ ይስጠን ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
አዲስ ማለዳ ተማሪዎቹ ላቀረቡት ጥያቄ ያላቸውን ምላሽ ለማግኘት ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው የአምቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ባይሳ ለታ (ዶ/ር) ስልክ ብትደውልም ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሐሳባቸውን ማካተት ሳይሳካላት ቀርቷል።
ፕሬዝዳንቱ በመጀመሪያ ስልካቸውን አንስተው “ከቢሮ የማዋራው ባለ ጉዳይ አለ” ብለው ከ30 ደቂቃ በኋላ እንዲደወልላቸው ቀጠሮ ቢሰጡም፣ በቀጠሩት ሰዓት በተደጋጋሚ ቢደወልም ስልካቸውን ሊያነሱ ፈቃደኛ አልሆኑም።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ሲማሩ የነበሩ 10ሺሕ 164 ተማሪዎች በአፋር ክልል በኩል አድርገው እንደመጡና ከጊዜ በኋላ ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚመደቡ ባሳለፍነው ዓመት ነሐሴ 7/2013 መግለጫ ሰጥቶ ነበር።
ቢሆንም ግን፣ ተማሪዎች “የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በገባው ቃል መሠረት ወደ ሌላ ዩኒቨርስቲ ሊመድበን አልቻለም” በማለት ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ ማቅረባቸውን ስትዘግብ ቆይታ ነበር። በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎቹ ወደተለያዩ ዩኒርስቲዎች እንዲመደቡ በቅርቡ መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



