ጦርነት ሕይወትን ማጥፋት ሕጋዊ ሁኖ በርካቶች በቡድን ተሠልፈው የሚገዳደሉበት እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ የመጠፋፋት ሒደት በርካቶች ከመሞታቸው ባሻገር፣ ንብረት ይወድማል፤ ይዘረፋል፤ እንዲሁም ዘግናኝ ግፎች ይፈጸማሉ።
በቀደሙት ዘመናት፣ ጦርነቶች ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች ስላልነበሩባቸው የተዋጊዎች ብቃት የሚታዩባቸው እንደነበሩ ይነገራል። ተፋላሚ ወገኖች ቦታ መርጠው፣ የሚዋጋውንም ብዛት ወስነው እንደክብራቸው መጠን ለመገዳደል ይሠለፉ ነበር። ጦርነቶች ረጅም ጊዜ የማይፈጁ ከመሆናቸው ባሻገር፣ አሸናፊው ወገን ለተሸናፊው ክብር ሰጥቶ አስከሬኖችም በክብር የሚቀበሩበት፣ ምርኮኛም በሥርዓት ተይዘው ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚደረጉባቸው እንደነበሩ መዛግብት ይጠቁማሉ። በተቃራኒው ግፍ የሚፈጽምባቸው፣ ምርኮኞችም የሚሰቃዩባቸው፣ በባርነትም እንዲማቅቁ የሚደረጉባቸውና አስከሬኖችም የአውሬ ሲሳይ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎችም እንደነበሩ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ጦርነት ተለይቷት አታውቅም እስኪባል ድረስ አባቶቻችን እየተዋጉ አገራችንን እንዳቆዩልን ይታመናል። ይህ እውነታ ቢታወቅም አሁን ግን ነገሮች ከዘመናዊነት ጋር በተገናኘም ይሁን ባለማወቅ መቀያየራቸው የሚታይ ነው። በተለይ ሰብዓዊነትን በተመለከተ ለሰው ልጅ ይሰጥ የነበረ ክብር እንደቀነሰ ይነገራል። ሰው በሰውነቱ ብቻ መከበር እንደሚገባው ከሚያምን ማኅበረሰብ የተገኘ ትውልድ ዘቅጦ፣ አሁን ሲደረጉ የምናያቸውንና የምንሰማቸውን ግፎች እየፈጸመ እንደሚገኝ ይታወቃል። እገሌ ከእገሌ ሳይል እንደዜጋ ድርጊቱ በማንም ይፈጸም በማን ልናፍር የሚገባን ኹላችንም መሆናችንን አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ምዕራባውያኑ አንድ አጥፊ ያደረገውን እንዲያደርግ ያደረገው ማኅበረሰቡ ነው የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ካለማስተማር ጋር በተገናኘም ይሁን እንዴት በገዛ ወገኑ ላይ እንዲህ ፈጸመ በሚል፣ ብንጎዳው ባንንከባከበው ነው እንጂ ይህን አያደርግም የሚል አስተሳሰብ እንዳላቸው የሚናገሩ አሉ። በእኛም አገር ሰው በተፈጥሮው ያለ ምክንያት አይበድልም የሚል እሳቤ ስለነበር፣ አንድ አጥፊ የሠራውን ያደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ በማወቅ እንዳይደገም ለማድረግ ይሞከራል።
ኢትዮጵያ አሁን ለአንድ ዓመት የተራዘመ ጦርነት ላይ እንደመሆኗ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተደረጉ ተግባራት ብዙዎችን ያሳዘኑ ነበሩ። በንጹኃን ላይ የሚፈጸሙ ግፎች የመበራከታቸውን ያህል፣ ድርጊቶቹን የፈጸሙትን አካላት ይዞ ወደ ሕግ የማቅረቡ ነገር ገና ብዙ እንደሚቀረው ይታያል። ይህ ቢሆንም ግን፣ አሁንም እየተፈጸሙ ያሉ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ለማስቆም መሠራት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
በጦርነት ወቅት ከፍልሚያው ቀጥሎ ትልቁን ቦታ የሚይዘው የፕሮፓጋንዳ ሥራ መሆኑ ይታወቃል። ጠቃሚነቱ አጠያያቂ ባይሆንም፣ ሥርዓትና መርህን የተከተለ እንጂ፣ ጠላት ስለተጠቀመበት ብቻ በፉክክር መደረግ የሌለበት ነው።
በቀደመው ዘመን ሥማቸውን መጥቀስ የማያስፈልግ የጦር መሪ በሚዋጉበት ወቅት፣ ጠላቴ ብለው የሚፋለሙት ወገን የተማረከ ወታደራቸውን አካል ቆርጦ በመላክ ጭካኔውን ለማሳየት ሞክሮ ነበር። እኚህ ታዋቂ መሪ ፈሪ ከምንባል ብለው የጠላታቸውን ሰው አስይዘው የበለጠ አካሉን አስቆርጠው በመንገድ ላይ ያስቀምጡና ወደወገኖቹ እንዲመለስ ያደርጋሉ። ያኛው ሲያይ ይበሳጭና ከእኛ ብሶ በሚል አስተሳሰብ ሌላ ምርኮ አስመጥቶ ሙሉ እጅና እግሩን አስቆርጦ እንዲደርስ ያስደርጋል። ሒደቱ በዚህ መልክ ቀጥሎ እኔ እብስ፣ እኔ የበለጠ እጨክናለሁ፣ በሚል አፍንጫ፣ ጆሮ፣ ዐይንና ሌሎች መቆረጥ የሚችሉ የአካላት ክፍሎችን ሰዎቹ እንዳይሞቱ አድርገው በጥንቃቄ እየቆራረጡና እየከታተፉ ግፍ ሲለማመዱ ቆይተው በኋላ ላይ በምክር እንደተመለሱ ይነገራል። የሚዋጉበትን የሰብዕና ዓላማ ረስተው እንደጠላታቸው ጨካኝና ግፈኛ ከሆኑ ከጠላታቸው እንደማይሻሉ ስለተረዱ ለአገርና ሕሊናቸው ሲሉ በግፈኛነት ተበልጠው እስካሁን በአሸናፊነት ይጠቀሳሉ።
አሁን እየተካሄደ ካለው ጦርንት ጋር በተገናኘ ምርኮኛን ቃለ መጠይቅ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል። አንዳንዴ “ገለውኝ ሔዱ” የሚል የሟች ዕማኝነት የሚሠጥበት አዝናኝ የቅስቀሳ ፕሮፓጋንዳ ሲደረግ ቢሰማም፣ በአብዛኛው ግን ሒደቱ ውጤታማ እንደማይሆን አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ምርኮኛ በዓለም አቀፍ ሕግም ሆነ በሞራል ሊከበርለት የሚገባ መብቱ ሊኖር ይገባል። ከኢትዮጵያዊነት ሥነ-ልቦና ያፈነገጡ ማሸማቀቆችን፣ ማሳጣቶችንና ተመልሰው ሠላማዊ ሕይወታቸውን ለመግፋት የሚቸገሩበትን ሒደት እንደመደበኛ ሥራ የሚያቀርቡ አካላት ከኹለቱም ወገን መደጋገማቸው ይታያል። ብዛት አሸናፊ እንደማያደርግ የሚያምን ማኅበረሠብ ውስጥ ሁኖ መብዛቱን ለማሳየት፣ እንዲሁም ብዙ መማረክ ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ ዕልህ ውስጥ ሊከት እንደሚችል የሚያምን የሕብረተሰብ ክፍል፣ በተቃራኒው ሲደረግ ከመቃወም ይልቅ እንደጠላት ልታይ እችላለሁ በሚል ፍራቻ ተለጉሞ ቁጭ ማለት አይኖርበትም።
በሌላ በኩል፣ በጦርነት ወቅት የቆሰሉንም ሆነ የሞቱትን በምስል እየቀረጹ በተለያዩ መንገዶች ለሕዝብ ማሠራጨት እንደጀብድና እንደጀግንነት መለኪያ እየተደረገ መጥቷል። ይህ አሳፋሪ መንገድ የአሸናፊነት ማረጋገጫና ድልን ማቅረቢያ ካለመሆኑ ባሻገር፣ “የማይታመን ብዙ ማስረጃ ያቀርባል” እንደሚባለው እንዳያስገምት ጥንቃቄን ይፈልጋል። የማያውቀው አስከሬን ሲያልፍ ቆሞ በሀዘኔታ ከሚያሳልፍ ማኅበረሰብ ውስጥ ወጥተን፣ በአስከሬኖች መካከል ሆኖ ምንም ሳይሰቅቀው የሚፎክርና የሚዘባበት እየተመለከትን ነው።
በየትኛውም አገር ሆነ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አስከሬንን ማሳየት ለምን እንደተከለከለ በማገናዘብ፣ እንዲህ አይነት ተግባሮችን ከመፈጸማችን በፊትም ሆነ ከማሠራጨታችን አስቀድሞ ልንጠነቀቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። የማንም ወገን ይሁን አስከሬንን በግል አክብሮ መቅበር፣ የማይቻል ከሆነ ደግሞ በቡድን መቅበር እንደሚገባ ይታወቃል። በእንዲህ ዓይነት ወቅት የሟች ቤተሰቦች በዘግኛኝ ሁኔታ ውስጥ ሁነው የሞቱ ወገኞቻቸውን እንዳያዩዋቸው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ቤተሰቦች ዕርማቸውን እንዲያወጡም ሆነ ለፍትሕ ሥርዓቱ ጠቃሚ የሚሆን ከሆነ፣ የሞቱትን ለይቶ ለማስረጃ እንዲሆን ቀርፆ ማስቀመጡ ላይከፋ ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን ለቡድን ዓላማ ማስፈጸሚያ ወይም ለፕሮፓጋንዳ በሚል ባህል የማይፈቅደውን ነገር ማድረግም ሆነ፣ ሲደረግ መመልከት፣ አሊያም በማሰራጨት መተባበሩ መቆም ይኖርበታል።
ግፍ ግፍን ይወልዳል እንደሚባለው፣ የጭካኔ ተግባራትንም ሆነ ዘግናኝ የቅስቀሳ መንገዶችን ከመለማመዳችን በፊት ከአሁኑ ልናስብበትና ልናስቆመው ይገባል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጠላት የምንለውንም ከመስደብ ምንም የምንጠቀመው ነገር እንደሌለ መረዳት ይኖርብናል። ኹሉም ኢትዮጵያዊ የሚያከብረው፣ የሚወደውና ክፉውን የማመኝለት ወዳጅ ዘመድና ቤተሰብ እንዳለው መዘንጋት የለበትም።
አንድ ተከታይ ያለውን ሰው መስደብም ሆነ ለማዋረድ መሞከር ሠላምን ከማምጣት ይልቅ ጠላትን ያበዛል። ጦርነት አልቆ ሠላማዊ ኑሮ እንዲጀመር ከማድረግ ይልቅ ቂም የሚቋጥርና ለበቀል የሚነሳ ትውልድ እንዲኖር ማድረጉ ዕሙን ነው። ምን ያመጣሉ በሚል የሚደረጉ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት የሰውን ልብ ለማሸነፍና የጦርነቱ ድልነሺ ለመሆን የሚደረገውን ጥረት ገደል ሊከተው ይችላል። የውጊያና የፕሮፓጋንዳ ዓላማ የጠላትን ደጋፊ አመናምኖ የራሥን ለመጨመር እንጅ፣ በተቃራኒው መሀል ሠፋሪ እንዲበዛ ለማድረግ መሆን የለበትም።
እንደአዲስ ማለዳ ዕምነት አንድ ሠው ተወልዶ ወጣትነት ደረጃ እስከሚደርስ በዚህች ድኃ አገር ኢኮኖሚ ቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡም ትልቅ ዋጋ ከፍሏል። ታዲያ ብዙ የተደረገለትን የሕብረተሰብ ክፍል ለሞት መዳረግ የማይገባ ቢሆንም፣ ለብዙኃኑ ደኅንነት ሲባል ሊገድል የመጣን መግደል ሊገባ ይችላል። ነገር ግን፣ የተገደለንም ሆነ የተማረከን በማይገባ መልኩ እያቀረቡ ቤተሰቡን አሳዝኖ ወደሌላ ተግባር እንዲገቡ ማድረግ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል። ይህ ከፍርሃት የመነጨ ሳይሆን የጀግንነት መለኪያ ነው። ለወደፊቱ ኢትዮጵያውያኖች የሠሩት መባሉ ስለማይቀር እንደአገር ለቀጣዩ ትውልድ የሚያሳፍር ሥራ ትተን እንዳናልፍ ማሰብ ይጠበቅብናል።
ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014



