በአማራ ክልል በሩዝ ማሳ ውስጥ አሣ ማምረት መጀመሩ ተገለጸ

0
997

በአማራ ብሔራዊ ክልል ሩዝ በሚተከልበት ማሳ ውስጥ፣ ትናንሽ ኩሬዎችን በማዘጋጀት አሣ ማምረት መጀመሩን የክልሉ እንስሳት ሀብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የኤጀንሲው የእንስሳት ዕርባታ ተዋጽዖ መኖ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ እንደገለጹት፣ የሩዝ ማሳ ውኃ ተኝቶበት ስለሚከርም ከሩዝ ምርት በተጨማሪ አሣ ማምረት ይቻላል ብለዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት ማብቂያ ገደማ በፎገራ ወረዳ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኖ ምርት የተገኘ በመሆኑ፣ በቀጣይም በጣና ሐይቅ ዙሪያ ባሉ ዐሥር ወረዳዎች በሚገኙ ሩዝ ማምረቻ ቦታዎች ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።

በተደረገው ሙከራ አሣ የሚራባበት ሩዝ፣ አሣ ከሌለበት ሩዝ በቅጠሉ ይለያያል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አሣዎች ከሩዙ መኖ ማግኘት ሲችሉ፣ ከአሣዎች የሚወጣው ጽድጃም ለሩዙ ማዳበሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። አክለውም፣ ሥራው በትንሽ መሬት ብዙ አሣና ሩዝ ማምረት ከማስቻሉም በላይ፣ የአሣ ምርቱን ቀጣይነት በማረጋገጥ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንዲሁም ውጤታማ ነው የተባለለት ይህ ፕሮጀክት፣ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ ውጤት እንዳላስገኘ ተጠቁሟል።

በባህር ዳር ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ሥራ የጀመረው የአሣ ጫጩት ማምረቻ ማዕከል ለዚህ ፕሮጀክት ትልቅ ዕገዛ እንዳለው ተገልጿል። ማዕከሉ በ2013፣ 198 ሺሕ 500 የአሣ ጫጩት በ12 ሰው ሠራሽ ግድቦች ለሚደረግ አሣ እርባታ ማሠራጨት ያስቻለ ሲሆን፣ በቀጣይ በዐሥሩም ወረዳዎች ተግባራዊ ለሚደረገው ከሩዝ ጋር የተቀናጀ አሣ የማምረት ሥራ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ይህም የተመናመነውን የአሣ ሀብት ለመታደግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው አስምረውበታል።

በሌላ በኩል፣ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ላይ ያለው ጦርነት አሣ በሕጋዊ መንገድ ለገበያ እንዳይቀርብ ትልቅ መሰናክል መፍጠሩ ተመላክቷል። ይህም የሆነው ከፍተኛ አሣ በሚመረትበት ተከዜ ወንዝ ላይ ያሉ መሠረተ ልማቶች በመውደማቸውና ምርት ማምረት በመቆሙ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከተከዜ አሣ በማመላለስ ወደ ገበያ የሚያቀርቡና እያንዳንዳቸው በአራት ሚሊዮን ብር የተገዙ አራት ዘመናዊ መኪኖች ተዘርፈዋል ነው የተባለው።

በተጨማሪም፣ ዘመናዊ መረቦች እና አሣ ማስገሪያ ጀልባዎች በመዘረፋቸው ምርት ማግኘት አለመቻሉ ተገልጿል። በዚህም በአበርገሌ እና ዝቋላ የመሳሰሉ የተከዜ አዋሳኝ ወረዳዎች የአሣ ግብይት ተቋርጧል። በሐይቅም እንዲሁ መሠረተ ልማቶች መዘረፋቸውንና ወጣቶች መበተናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ወቅታዊ ኹኔታውን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሕገ-ወጥ መረቦች ከውጭ (ከግብጽ) ስለሚገቡ ሕገ-ወጥ የአሣ ማስገርና ሕገ-ወጥ ንግድ በመስፋፋቱ አሣን በሕጋዊ መንገድ ለግብይት በማቅረብ ሒደቱ ላይ ችግር መፍጠሩ ተመላክቷል። ይህን የሚቆጣጠር ኮሚቴ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም፣ ላለው አገራዊ ቀውስ ቅድሚያ በመሰጠቱ ችግሩን ማስቆም እንዳልተቻለ ነው የተነሣው።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ በጣና ሐይቅ የአሣ ሀብት መጠን መቀነሱን ጠቅሰው፣ በምን ያህል መጠን ቀንሷል የሚለውን ለማውቅ ግን ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሆኖም የእንቦጭ አረም መሥፋፋት፣ ወደ ሐይቁ ከሚገቡ ገባር ወንዞች ጋር ተቀላቅለው በሚገባ ባዕድ ነገሮች እና በሕገ-ወጥ አሣ አሥጋሪዎች ምክንያት የሐይቁ አሣ ምርት መጠን መቀነሱ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

ክልሉ በአገሪቱ የአሣ ምርት መጠን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ ቀደም ያሉ ጥናቶች ከ30 እስከ 40 ሺሕ ቶን የአሣ ምርት ክልሉ እንደሚያስገኝ ያመላክታሉ። አሁን ላይ የተደረገ ጥናት ባይኖርም፣ በክልሉ ባለው ወቅታዊ ኹኔታና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ የአሣ ሀብት መጠን ሊቀንስ እንደሚችል ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here