በደባርቅ፣ ንፋስ መውጫ እና ሸዋሮቢት ብቻ 157 ሴቶች በህወሓት ታጣቂዎች ተደፍረዋል

0
1168

በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች በጥናት ላይ ናቸው

እስካሁን በተገኘው መረጃ የህወሓት ታጣቂዎች፣ በአማራ ክልል ደባርቅ፣ ንፋስ መውጫ እና ሸዋሮቢት ከተሞች 157 ሴቶች ላይ አስከፊ ፆታዊ ጥቃት መፈጸማቸውን የክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
የቢሮው የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ስማቸው ዳኜ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ መረጃ ማግኘት በተቻለባቸው ቦታዎች በተደረገ ጥናት፣ እስካሁን በደባርቅ (ሰሜን ጎንደር) 49፣ በንፋስ መውጫ (ደቡብ ጎንደር) 79፣ ሸዋሮቢት (ሰሜን ሸዋ) 35፣ በጥቅሉ 157 ሴቶች በህወሓት ታጣቂዎች የተደፈሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከዋግኽምራ ተፈናቅለው እብናት መጠለያ ጣቢያ ከነበሩ ሴቶች ውስጥ፣ ዘጠኝ የሚሆኑት መደፈራቸውን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ ልምድ የተነሳ እንዲሁም የሚደርስባቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍራት ብዙ ሴቶች ራሳቸውን ባለመግለጻቸው እንጂ፣ በእነዚህ ቦታዎች ብቻ በህወሓት ታጣቂዎች የተደፈሩ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ሴቶች ውስጥ ቋሚ ለሆኑ በሽታዎች የተጋለጡ መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ለአብነትም በቡድን በመደፈራቸው ምክንያት ለፊስቱላ በሽታ የተዳረጉ ሴቶች እንዳሉ ገልጸዋል። በባሎቻቸውና በልጆቻቸው ፊት የተደፈሩ ሴቶች መካከልም ቋሚ የሆነ የአእምሮ በሽታ ታማሚ የሆኑ ሴቶች አሉ ነው ያሉት።

ማንነታቸውን እየጠሩ እንዲህ ስለሆናችሁ ነው የምንደፍራችሁና የምናሰቃያችሁ እየተባሉና እየተሰደቡ በቤተሰቦቻቸው ፊት ከተደፈሩት ውስጥ፣ የደረሰባቸውን ስቃይ መቋቋም ያልቻሉ ኹለት ሴቶች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ዳይሬክተሩ ጨምረው ተናግረዋል።
በህወሓት ታጣቂዎች ከተደፈሩ ሴቶች ውስጥ የአስራ ኹለት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት የሚገኙ ሲሆን፣ በደባርቅ ከተደፈሩ 49 ሴቶች ውስጥ 18ቱ ሕፃናት ናቸው ተብሏል።
በሌላ በኩል የህወሓት ታጣቂዎች ለረዥም ጊዜያት በቆዩባቸው የሰሜንና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች የተደፈሩ ሴቶች እስካሁን በቁጥር አለመታወቁን ስማቸው ዳኜ ተናግረዋል።

በቦታዎቹ ያለው የጸጥታ ኹኔታ ገና አስተማማኝ ካለመሆኑ በተጨማሪ፣ በተወረሩ አካባቢዎች የሚገኙ የቢሮው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በመውደማቸው፣ እንዲሁም ሠራተኞች በደረሰባቸው የሥነ ልቦና ቀውስ ምክንያት በመበተናቸው ጥናት አልተደረገም የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ወቅት ኮሚቴ ተቋቁሞ በቅርብ ነጻ በወጡ ጥቂት አካባቢዎች ጥናት እየተደረገ ቢሆንም፣ ሥራው ጊዜ፣ በጄትና የሰው ኃይል የሚጠይቅ በመሆኑ መረጃውን በፍጥነት ማቅረብ አልተቻለም ሲሉ ነው የገለጹት ።
ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች በሚገኙ በርካታ ሴቶች ላይ የህወሓት ታጣቂዎች አሰቃቂ ግፍ እንደሚፈጽሙ ይታመናል ነው ያሉት።

ራሳቸውን በመግለጽ የደረሰባቸውን ጥቃት ላሳወቁ ሴቶች እስካሁን ከዩንቨርስቲዎች ጋር በመተባበር የሥነ ልቦና ምክርና ሥልጠና ተሰጥቷል ተብሏል። እነዚህ ሴቶች ከደረሰባቸው የአስገድዶ መደፈር ውጭ፣ የእጅ ስልካቸው ሳይቀር ያላቸው ንብረት በሙሉ በህወሓት ታጣቂዎች የተወሠደባቸው በመሆኑ የተወሰነ ገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

ጥቃት የደረሠባቸውን ሴቶችና ሕፃናት ጤናቸውን ለመንከባከብ ከኹሉም በፊት የወደሙ ጤና ተቋማት ሥራ መጀመር አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የተጎዱትን ለመደገፍና ለማቋቋምም፣ መረጃ በፍጥነት ለማወቅ የባለሙያ ዕጥረት በመኖሩ በጣም ለተጎዱት ለእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ የሚችል አካል ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here