ሐሙስ ታህሳስ 28/2014 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ግድያ፣ ማፈናቀልና እስራት ትኩረት እንዲሰጠው እንዲሁም በተለያዩ ምክንያች እየታሰሩ የሚገኙ ጋዜጠኞች በአፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብታቸው እንዲጠብቀላቸው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ ) ታህሳስ 27 ቀን 2014 ባወጣው መግለጫ አሳሰበ፡፡
ኢሰመጉ ዕሮብ አመሻሹ ላይ ባወጣው መግለጫ ከመስከረም 2014 ጀምሮ ማንነትን መሰረት ያረገ ጥቃት በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች መከሰቱን በመጥቀስ ለዚህም መንግስት አስፈላውን ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ለአብነትም ታሳስ 23 ቀን 2014 በሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርቲ ወረዳ በኦነግ ሸኔ ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ገበያ ላይ አምስት ንጹሃንን እንዲሁም ታህሳስ 24 ቀን 2014 ጃርቲ ወረዳ ሆሮ ሎጌ በተባለ የገበያ ቦታ አንዲት ሴት በአሰቃቂ ሁኔታነ ተገድላ አስክሬኗም እንዳልተነሳ መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል፡፡
በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ መንቃታ በተባለ ቀበሌ ታሳስ 11 ቀን 2014 ሌሊት ላይ በስፍራው ለበርካታ ዓመታት ነዋሪ የነበሩ 10 የአማራ ተወላጆች ከአንድ ቤት ሶስት ሰዎችን ጨምሮ ግድያ ስለመፈጸሙም ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ታህሳስ 14 ቀን 2014 ጃርቲ ወረዳ ሰንባ ጨፌ ቀበሌ ሥብሰባ ላይ የተገኙ 7 የአማራ ተወላጆችን እንዲሁም ታህሳስ 22 ቀን 2014 አሞሩ ወረዳ ጃባ ጀቦን ቀበሌ 5 ሚሊሻዎች ለሥብሰባ ተጠርተው በሄዱበት ተደብድበው መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡
በዚሁ ቀን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ከተማ እና አካባቢው በሚኖሩ ዜጎች ላይ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት ቁጥራቸው ያልተገለጸ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ስለመገደላቸውና በከተማዋ የሚገኙ የባለሀብቶች ንብረት ላይ ዘረፋ መፈፀሙን መረጃ ደርሶኛል ብሏል፡
መግለጫው እንደሚያሳው ከመስከረም 27 ቀን 2014 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ ዳርጌ ቀበሌ (አዳኒ፣ ኡኩ፣ መሩሃ፣ ገጃ፣ ሬጂ እና ኮምቦልቾ መንደሮች) ነዋሪ የነበሩ ዜጎች ተፈናቅለው መኖሪያ ቤቶቻቸው ስለመቃጠሉና ግለሰቦች ስለመገደላቸው እንዲሁም ለመሰብሰብ የደረሰ በርካታ ሰብል ሳይሰበሰብ በእርሻ ላይ ተበላሽቷል፡፡
ኢሰመጉ በመግለጫው አገራዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም ዓለምአቀፍ ህግጋትን በተፃረረ መልኩ ክቡር በሆነው የሰው ልጅህይወት ላይ እየደረሰ ያለውን አሳዛኝ ድርጊት በማውገዝ፣ ጥቃቱን ተከትሎ ንብረታቸው የወደመባቸው እንዲሁም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ያሳስበኛል ብሏል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች እየታሰሩ የሚገኙ ጋዜጠኞች አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብታቸው እንዲሁም ሰብዓዊ አያያዛቸውን በተመለከተ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል ሲል ዋዜማ ራዲዮ ዘግቧል፡፡
መንግስት ድርጊቱን የሚፈፅሙ አካላትን በአግባቡ አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፤ ለዚህ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለጉ ላይ በብርቱ እንዲሰራ ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም ዜጎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ መገናኛብዙሃን፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎች ይህ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ የሚጠበቅባቸውን እገዛ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ላይ ውትወታ እንዲያደርጉ ኢሰመጉ ጥሪውን ጥሪ አቅርቧል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




