የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ላለፉት ስድስት ወራት ተዘግቶ የቆየው እና አገራቱን የሚያስተሳስረው የጋላባት- መተማ ዋና መንገድ መከፈቱ ተነግሯል።
በኢትዮጵያ በኩል በምዕራብ ጎንደር አስተዳዳሪ የሚመራና ወታደራዊ አመራሮችን ያካተተ ቡድን፣ በሱዳን በኩል ደግሞ በኹለት የሱዳን ጦር ብርጋዴየር ጄነራሎች የተመራ ቡድን በምዕራብ ጎንደር መተማ ዮሐንስ ከተማ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ድንበሩ መከፈቱ ነው የተገለጸው።
ይህንን መንገድ በሱዳን በኩል ወይም በጋላባት አስተዳደር ከስድስት ወራት በፊት በመዝጋቱ የድንበር እንቅስቃሴው ተቋርጦ እንደቆየም ተገልጿል።
ከምክክሩ በኋላ ተዘግቶ የነበረው ድንበር ተከፍቶ የሰዎች እና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የንግድ ልውውጡም እንደተጀመረ ተጠቅሷል።
በዚህም ከባድ የጭነት ማጓጓዣዎች ገብተው የንግድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን የመተማ ዮሐንስ ከተማ አሳውቋል።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ወታደራዊ ቦታን የማስፋፋት ተግባር መቆም ቢችል፣ የድንበሩ ጉዳይ በድንበር ኮሚሽን ቢታይ በሚል አጀንዳ እና በስደተኛ ካምፕ ስም ኢትዮጵያን የሚጎዱ ጽንፈኛ ኃይሎች በሱዳን መኖራቸው በተመለከተ ምክከር እንደተደረገም ተገልጿል።
የተከፈተው የጋላባት- መተማ ዋና መንገድ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተነገረ ሲሆን፣ በሳምንታት ውስጥ አካባቢው ወደቀደመ እንቅስቃሴው ይመለሳል የሚል ዕምነት መኖሩም ተመላክቷል።
ሱዳን በትግራይ ክልል ግጭት ከተነሳ ከሦስት ቀናት በኋላ፣ ከጥቅምት 27/2013 ያላግባብ የያዘችውን መሬት ትልቀቅና ወደ ንግግር እንግባ የሚል ሐሳብ ኢትዮጵያ ስታነሳ ቆይታለች።
ሱዳን በበኩሏ የአገራቸው ሠራዊት ግዛቴ ነው ከሚላቸው ቦታዎች ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠሩንና ይህም የማይቀለበስ ዕርምጃ መሆኑን ትገልጻለች።
ኢትዮጵያ ይህ የሱዳን እንቅስቃሴ የሌሎች ኃይሎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ነው በሚል በተደጋጋሚ የምትጠቅስ ሲሆን፣ ሱዳን በበኩሏ ኢትዮጵያ የግዛቶቿ አካል የሆኑ መሬቶችን እንደወሠደች ትከሳለች።
በቅርቡም ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት ድንበር ላይ ተጨማሪ ወታደሮችን ማስፈሯን አስታውቃለች።
ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም፣ ቀጠናው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር እንደሆነም የሱዳን ጦር አመራሮች ሲናገሩ ይደመጣል።
ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014


