በዓል ሰሞን የሴቶች የቤት ውስጥ ሥራና ኃላፊነት ይጨምራል። በተለይ የቤት እመቤት ላልሆኑና የቤት ውስጥ ሥራን የሚያግዝ ሠራተኛ ያልቀጠሩ ከሆኑ፣ ከውጪ ሥራ ጋር ቀላል አይሆንላቸውም። አዎን! ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ሥራን ቀለል የሚያደርጉ የተለያዩ አሠራሮች መጥተው ሁኔታውን ቀለል ያደረጉት ይመስላል። ይሁን እንጂ ሥራው ውጥረት ያለውና አድካሚ መሆኑ አይቀርም።
የበዓል ሰሞን በርካታ ወንዶች እንደ ትዳር አጋር፣ እንደ ወንድም ወይም እንደ ልጅ ባላቸው ኃላፊነት በተጨማሪ ከወትሮው በተለየ የቤት ውስጥ ሥራ ላይ በመሳተፍ ያገለግላሉ። ሁሉም ወንዶች እንዲያ ናቸው ማለት ግን አይደለም። ነገር ግን ገበያ ወጥቶ ከመሸመት አንስቶ የበሰለውንና የተዘጋጀውን በማቀራረብና ብሉ ጠጡ ብሎ በማስተናገድ እስከማገዝ ድረስ ተሳታፊ ወንዶች ያጋጥማሉ፤ አሉም።
እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ የምንዘነጋው የባለሞያ ወንዶችን ጉዳይ ነው። ሚስቱን ወይም እናቱን ዶሮ ከማረድ ባለፈ በመገንጠል የሚረዳ፣ በምግብ ማብሰል ሥራ ላይ ባስፈለገበት ቦታ በማገዝ የሚሳተፍ ወንድ ብዙ አለ። አልፎም እንጀራ የሚጋግር፣ ገበያውን ጠቅልሎ የሚሸፍን፣ ዶሮ ገንጥሎ ወጡን አጣፍጦ የሚሠራው ጥቂት አይደለም። እውቅና ግን የተሰጠ አልመሰለኝም!
ተመሳሳይ ልምድ ያለውና የበዓል ቀንም በተመሳሳይ መስተንግዶውን በማቀላጠፍ የሚሠራ ባለትዳር ወንድ አውቃለሁ። ነገር ግን ይህ ሰው ከሙገሳ ይልቅ ‹ምንድን ነው እንደሴት ጓዳ ለጓዳ!› የሚል አስተያየት የሚሰጠው ብዙ ነው። ባለቤቱም በሥራው እምብዛም ደስተኛ አይደለችም። በአንድ ጎን ‹እኔ እንደምሠራው አይሆንለትም!› ብላ በማሰብ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተለመደ ጉዳይ ስላልሆነ አልዋጥ እንደሚላት በጨዋታ መካከል ታነሳለች።
ይህ ሰው አንድ ቀን ‹ተይዋ!› ብሎ የቤት ውስጥ ሥራ ላይ ያለውን ተሳትፎና እገዛውን ይተው ይሆን ብዬ እሰጋለሁ። ለዛ ነው ማመስገንና እውቅና መስጠት የሚያስፈልገው ብዬ አስባለሁ። እንዲህ በዓል ሲቃረብም የሚያግዙ ወንድሞችን፣ ባሎችና ልጆችን ለእገዛቸው ማመስገን፤ ከበዓል አልፎ በአዘቦቱም እገዛቸው እንዲኖር ‹ይበል! ይልመድባችሁ!› ማለት መልካም ነው። ሰው በግዴታውም ሆነ በውዴታው ለየትኛውም ሰው ለሚሰጠው አገልግሎት ማመስገን ምንም አያጎድል!
እና ወንድሞች ሆይ! በቤት ውስጥ ያለውን ሥራ በማገዝ ስለምታደርጉት ሱታፌ ሴቶች ያመሰግኗችኋል፤ እናመሰግናችኋለን። የበዓል ሰሞን ‹ግዴታሽ ነው ምን አገባኝ!› ሳትሉ ቤታችሁ በዓል እንዲመስል አብራችሁ እንደምትጨነቁና እንደምታስቡ ሁሉ፣ በአዘቦቱም የቤት ውስጥ ተሳትፏችሁን እንዲህ ልብ ብላችሁ ተመልከቱት። ብዙ ልታደርጉትና ልታግዙት የምትችሉት አለ። መልካም በዓል!
ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014


