ያዢ!

0
994

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

እድል በጠፋና ባልተሰጠ ሰዓት እድል የነፈጉ ሰዎችን ወይም ስርዓትን መውቀስ ቀላል ነገር ነው። ያም ብቻ አይደለም! ይመስለኛል በተፈጥሮአችን ከምናደርገው ይልቅ ልናደርግ እንችላለን ብለው የምንገምተውን እናገዝፋለን። ለዛም ነው ብዙዎቻችን እንደ ሰው በሕይወት የሚሰጡንን እድሎች መጠቀም ትተን፣ በአንጻሩ ሌሎችን እያየን ‹እንደ እገሌ ብሆን የማደርገውን እኔ አውቅ ነበር!› የምንለው።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም የእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ እየተደረገ ይገኛል። ይህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክክር ማቋቋም አስፈላጊ ነው ብሎ በማመን ባጸደቀው አዋጅ መሠረት የሚመሠረት ኮሚሽን፣ ‹እገሊት አባል ትሁን/ እገሌ ይካተት› ብሎ ማንኛውም ሰው ጥቆማ እንዲያቀርብ እድል የከፈተ ነው። ይህ ኮሚሽን ታድያ እጩዎቹ ታውቀው ከተመሠረተ በኋላ ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት የሚረከብ ነው።

ያዢ! ጥቆማ ስጪ። በአገርሽ ጉዳይ እንደሚያገባሽና ነገም እንደሚያሳስብሽ፣ የተሻለችና መግባባት ያለባት አገር እንድትፈጠር ድምጽሽን አዋጪ። በእውቀትና መረዳትሽ ልክ እገሊት ወይም እገሌ በዚህ አገራዊ ምክክር መድረክ ላይ በባለቤትነት ቢሳተፉ ይወክሉኛል፣ ለውጥ እንዲመጣ ገንቢ ነጥብ ይሰጣሉ፣ ይሞግታሉ፣ ለአገር ይጠቅማሉ ወዘተ ብለሽ ያመንሽባቸውን ጠቁሚ!

በአደባባይ ሥማቸው የሚታወቁ ብቻ ሳይሆን ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉና ብዙ ሥራን የሠሩ ሴቶች እንዳሉ ለማሳየት ይህ ጥሩ አጋጣሚና እድል ነው።

ያዢ! ጥቆማ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ተጠቁመሽ ከሆነ አታፈግፍጊ። ኃላፊነትን ተቀበይና ለአገርሽ በዚህ መንገድ ደግሞ አበርክቺ። አቅምና እውቀት እያለሽ ወደኋላ አትበይ። እድሉን ያዢ፣ ሞክሪ። ለብዙ እህቶችሽ አረአያ መሆንሽ ወለዱ ነው፤ ዋናው ደግሞ ለአገርሽ የምታበረክቺው አስተዋጽኦ!

ያዢ! ስለአገርሽ ጉዳይ ስሚ፣ ተከታተይ። ተመልከች! አንዳንድ ሰዎች በአውሮፓና ኢንግሊዝ እግር ኳስ ጨዋታ ላይ ትንታኔ ይሰጣሉ። ‹እገሌ እንዲህ ባያደርግ ኖሮ› እያሉ ይሞግታሉ። እነርሱ በርቀት ለሚገኙና አስተያየታቸውን ለመቀበል እንኳ ለማያውቋቸው እግር ኳስ ተጫዋቾች እንዲህ በርትተው ከሞገቱ፣ አገር ከዚህ ምንኛ ትቀርባለች? አንቺ ለአገርሽ ድምጽሽን ብታሰሚ፣ ባለጆሮ እስኪሰማሽ ድረስስ ብትደጋግሚ? ያዢ! ስለአገርሽ ስሚ፣ ተወያይ፣ ሐሳብ ተለዋወጭ፤ ተነጋገሪ።

ያዢ! የእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ አስቀድሞ ጥር 6/2014 ይጠናቀቃል የተባለ ቢሆንም አሁን እስከ ጥር 13/2014 ድረስ መራዘሙ ተዘግቧል። በቀጥታ የስልክ መስመር 011-130-03-40 ካልሆነ በኢሜይል አድራሻ [email protected] ወይም [email protected] ላይ ከwww.hopr.gov.et በሚገኝ የመጠቆሚያ ቅጽ ሞልተሽ ጥቆማ አድርሺ። ስለአገርሽ ያገባሻል…ያዢ እድል!
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here