ለምን ብሎ መጠየቅ ዕውቀትን የምናገኝበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ዝም ብለን ወደተነዳንበት እንዳንነጉድ የማሰላሰያ መንገድ መሆኑን ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል። አንድ ግለሰብ የተባለውን እንደሠማ መቀበሉ እንደገደል ማሚቶ እንዲያስተጋባው ያደርገዋል እንጂ አመዛዝኖ እንዲረዳው አያደርገውም። ያልተረዳውን ነገር ማስተጋባቱ ደግሞ እንደሱ ዝም ብለው ለሚቀበሉ መሠሎቹ ይበልጥ አደገኛ ይሆናል። ለምን ብሎ የማይጠይቅም ማኅበረሰብ ይህ ድክመቱን ባወቀበት ግለሰብም ሆነ ቡድን እንደተፈለገ እየተሸከረከረ መጠቀሚያ ይሆናል እንጂ፣ ፍላጎቱ አይከበርለትም።
የመጠየቅ ባህል ከልጅነት ጀምሮ መዳበር ያለበት አስፈላጊ አስተሳሰብ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች። “እኛ ብቻ እናውቅላችኋለን፤ እመኑን” ከሚል የጨለማ ጉዞ ለመዳን ለምን ብሎ መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ዝለል ሲባል እስከዬት ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ እንዳይኖር ማድረግ የኹላችንም ሥራ መሆን አለበት። ወታደርም ቢሆን የታዘዘውን ኹሉ መፈፀም እንደሌለበት ዓለም አቀፍ ሕግም ጽንሠ ሐሳቡን ያስቀምጣል። ሕግና ደንብን የጣሰ ከመሠለው ከመታዘዝ ውጭ ለምን ይሆናል ብሎ መጠየቅ እንዳለበት፣ አለበለዚያም አልታዘዝም የማለት የማያስጠይቅ መብት እንዳለው በበርካታ አገሮች ሕግም ተደንግጓል።
ፖለቲከኞች ሕዝብንም ሆነ የሚመሩትን ቡድን ለማስከተል የተለያየ መንገድ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ሊታወቅ ይገባል። ኹሉን በግልጽ ለሕዝባቸው እያቀረቡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለውን ሥርዓት እንዲዘረጉ የሕግ ድንጋጌዎች ቢያስገድዷቸውም፣ ተግባራዊ ከማድረግ ሲቆጠቡ ማየት የተለመደ ነው። አገራዊ ምስጢር በሚል ሽፋን አሊያም የፓርቲ ደንብ በሚል ዘዴ ለሕዝብ ይፋ ማድረግና ማማከር የነበረባቸውን ጉዳይ ሲሸፋፍኑ ማየትም ብርቅ አይደለም። ይህ የሆነው ምስጢር መሆን የሚገባቸውና መደበቅ የሌለባቸውን የሚለይ ግልጽ ሕግ ስለሌለ፣ ጥፋታቸውንም ሆነ ድክመታቸውን ሽፋን ለመስጫ ምስጢራዊነትን ስለሚያላብሱት እንደሆነ ይታመናል። ይህ ባለሥልጣናትን አምባገነን የሚያደርግ በዘፈቀደ የሚደረግ ልምድ እንዲቆም ካልተደረገ፣ ለወደፊት ለምን ብሎ መጠየቅም በራሱ ወንጀል የሚሆንበት ጊዜ እንደሚያመጣ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
“አያ በሬ ሆይ ሳር ሳሩን እያየህ ገደሉን ሳታይ” የሚለው ተረት ሳር በእጃቸው ይዘው ወደ ገደል መርተው የሚወስዱ በሌሉበት ዘመን የተተረተ ቢሆንም፣ አሁንም እንደዘዴ መታየቱን ለማሳየት የቆየ ጽሑፍ ወይም ማስረጃ መምዘዙ አያስፈልግም። በሬውን ከተከለለለት ጋጣ ውጭ እየወሰዱ ገደል ለመክተት የሚቋምጡ በርካቶች እየታዩ ያለበት የጦርነት ወቅት ላይ እንደመሆናችን፣ በሬውን የሚያጓጉት በእውነተኛ ሳርም ሳይሆን የውሸት በሆነና ገደል አፋፍ ላይ በሆነ ርብራብ ጥልቁን ሸፍነው ሳሩን በመጎዝጎዝ ነው ማለት ይቻላል።
ሰው አገሩን ስለወደደ ለአገሩ ሲል ይሞታል ብሎ የሚወደውን እያሳዩ ወስዶ ማግዶ ማስቀረቱ አያዛልቅም። የሔደ በሬ አለመመለሱን ያስተዋለ ሌላ ኮርማ ለወደፊት እውነተኛ ሳር ቢመጣ እንኳን አመኔታው ስለሚሸረሸር ቅደም ልከተልህ ብሎ ከኋላ ይሸሻል፣ አሊያም ከባሰበት ከጀርባ ይወጋል። ይህ የተፈጥሮ ሕግ መሆኑን የዘመናችን ባለሥልጣናት መረዳት ካልቻሉ፣ መጨረሻቸው እንደማያምር ትንቢት ተናጋሪ መሆንን አይጠይቅም።
አገር በዘፈቀደም ሆነ በአንድ ሰው አስተሳሰብም ሆነ ጭንቅላት መመራት እንደሌለባት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች። ለሕዝብ ብሎ የተመሠረተ መንግሥት፣ ገዢ ነኝ ብሎ በግልጽ አምባገነንነቱን እስካልተናገረ ድረስ የፈለገውን እንዳሻው የማድረግ ልምዱ ሊቆም ይገባዋል። ማንኛውንም የሕዝብን ቁጣ ሊቀሰቅስ የሚችል ተግባር ከመፈጸሙ በፊት ጉዳዩን በደንብ ሊያስብበትና ግራ ቀኙን ሊያመዛዝን ግድ ይለዋል። አንዱን ለማስደሰትም ሆነ የራስን ዕድሜ ለማራዘም ብሎ በስንት መስዋዕትነት የተገኘን ውጤት አሳልፎ መስጠት ዋጋ ያስከፍላል።
የጥንት አባቶቻችን፣ “ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” ሲሉ ከተረቱት ልንማር ግድ ይለናል። መንግሥት አትራፊ ነጋዴ ሳይሆን የሕዝብን ጥቅም አስጠባቂ መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል። የተሻለ ጥቅም ያስገኛል በሚል አገርን ለድርድርም ሆነ ለገበያ የሚያቀርብን አካሄድ ማንም ቢሆን ሊጠየፈው የሚገባ ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኹሉንም የፈጠረ አምላክን በጸሎቱ ሲለምን፣ የታመሙትን እንዲያድን፣ እንዲሁም የታሠሩትን እንዲያስፈታ መሆኑ ይታወቃል። በደፈናው የታሠሩ ይፈቱ ብሎ አምላኩን የሚለምን ሕዝብ ጸሎቱ በከፊል ሰምሮ የተወሰኑ ሲለቀቁ ለምን ከፋው ብሎ መጠየቅ ብልህነትን ይጠይቃል። ሰው ሲሞት እሰይ ማለት ነውር በሆነበት አገር፣ ማንም ይሁን ማን ሲፈታ ለምን ብሎ ከተጠየቀ ሕዝብ ለምን ተቃወመ ማለት ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ ከማዘኑ በፊት መገመት መቻል ይጠበቅ ነበር።
እንደቀድሞ ዘመናት መሪዎች፣ የአሁኑ መንግሥት አራት ዐይና የሆኑ የኋላውንም ሆነ መጪውን የሚያስተውሉ ዐይናማ ባለ ብሩህ አእምሮ አማካሪዎች እንደሌሉት ለማሳየት በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። ዙሪያውን የሚከቡ ጥቅም ፈላጊዎች እንጂ መስዋዕት ለመሆን የሚሽቀዳደሙ ባለመሆናቸው፣ እንዲህ ዓይነት ሕዝብን የሚያሳዝን፣ ተስፋውንም የሚያሟጥጥ ውሳኔ ሲፈጸም ማየት አያስገርምም። የሕዝብን ልቦና ማወቅ የሚችል ባይኖርም፣ ስስ ጎኑን በመፈተሸ እንዲህ ግዙፍ የሆነ ቅቡልነትን የሚያሳጣ ተግባር ላይ ድንገት መግባት ውጤታማ እንደማያደርግ ሊገመት በተገባ ነበር።
ሕዝብ ክፋት ኖሮት ወይም ጥላቻ አውሮት ሳይሆን የተበደለው በደል ግዝፈት የሚጸልየውን እንኳን እንዳያስተውለው ማድረጉን መረዳት ያስፈልጋል። ሕዝብ ለሕዝብ ምንም ቢቆራቆዝ እንኳን፣ በዘላቂነት የሚቆይ ቂም በቀል አንደማይኖርበት ከታሪካችን መረዳት እንችላለን። ይህ ቢሆንም ግን፣ ዘመኑ የፈጠረው ቴክኖሎጂ ቁስል በቶሎ እንዲያሽር የማያደርግ ታሪክን ሠንዶ ለዓመታት አንደነበረ ትኩስ አድርጎ ስለሚያስቀምጥ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ውስጣዊ ድጋፍ በሚያስፈልገው ወቅት ከጎኑ የተሰለፉትን የሚያሸሽ፣ ለውጭ ድጋፍ ማግኛ ብሎ ቁማር ውስጥ ራሱንም ሆነ ሕዝቡን መክተት እንደሌለበት ሊታመን ይገባል። የቆጡን ለማውረድ ተብሎ በእጅ ያለ ወርቅን መጣል በባዶ እንደሚያስቀር መረዳት ያስፈልጋል። የማሪያም መንገድ ለመስጠትና ውጭ ተሠደው እንዲቀሩ ማለፊያ መስመር ለማመቻቸት ሲባል፣ ከሕዝቡ ጀርባ የሚዶለት የውጭ ጫና ካለም ሕዝቡ አውቆት አብሮ ቢወስን መልካም እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ታሳውቃለች።
ከዕሥር እንደወጡ ታመሙ ብሎ አስወርቶ ለሕክምና ወደ ውጭ ወጡ ለማለት የታሰበ ነገር ካለ፣ ከወዲሁ መንገዱን ጨርቅም ሆነ እሾህ ያድርግላቸው ብሎ ሕዝቡ ከመመኘት ውጭ ምንም እንደማያደርግ ታውቆ ከሥር ከሥር ሒደቱ ይፋ ቢደረግ መልካም ነው። ጓድ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማሪምን ከአገር ካስወጡዋቸው በኋላ እንዳደረጉት፣ የተዋጊው ቡድን አመራሮች በቀጣይ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ እጃቸውን እንዳያስገቡ ለማድረግ ታስቦም ከሆነ፣ ውጤት አመጣም አላመጣ አስቀድሞ ሒደቱ ምስጢር ነው ከማለት ይፋ ቢደረግ ሊመጣ ከሚችል ጉዳት ይታደጋል።
ሕዝብ በስሙ የሚደረግ ነገር ከተፈጸመ በኋላ መቃወም ብቻ ሳይሆን ምን ሊደረግ ነው? ለምንስ ወዲያው አልተነገረም? እንዲህስ ለምን አይደረግም? እያለ እራሱን እንደአገር ባለቤት አድርጎ ሊጠይቅ ይገባል። ለምን ብሎ መጠየቅ የሕዝብ ግዴታ ብቻ ሳይሆን መንግሥት ጭምር፣ ሐሳቦች ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሲቀርቡለት ምክንያቱን ለማወቅና ለማሳወቅ ለምን ብሎ በተገቢው ወቅት መጠየቅ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።
“አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” እንደሚባለው ሠበብ አስባብ እየፈጠሩ፣ በቃላትም እያሳመሩ ጊዜ ለመፍጀት መሞከር አያዛልቅም። ትውልዱ የነቃበት፣ ዘመናዊነትም የተንሠራፋበት ወቅት እንደመሆኑ የተነገረው ኹሉ እውነትነቱ እያደር ይገለፃል። “ሽል ከሆነ ይገፋል ዱባም ከሆነ ይጠፋል” እንዲሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014



