የቢራ ዋጋ ጭማሪ

Views: 122

ባሳለፍነው ሳምንት የካቲት 05/2012 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ውሳኔ የተለያዩ አዋጆችን ማጽደቁ ይታወሳል። ከአዋጆቹ መካከል በማኅበራዊ ገጾች ላይ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከልም፣ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ጉዳይ አንዱ ቢሆንም፣ እንደ ኤክሳይስ ታክስ ግን ሰፊ መነጋገረያ ሆኖ አልተመለከትነውም።

የኤክሳይስ አዋጅ ተግባራዊ መሆን የሚጀመረው ከየካቲት 6/2012 ጀምሮ ነው ሲል የገቢዎች ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፤ የቢራ አምራቾች፣ አከፋፋዮችና ሻጮችም ይህን ተሸቀዳድመው የዋጋ ጭማሪ አደረጉ። ይህም ጉዳዩን የበለጠ መነገጋገሪያ አደረገው።

የቢራ ዋጋው መጨመር ብዙዎችን ያበሰጨ እና ያመረረ መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሰነዘሩት ሐሳብ መታዘብ ይቻላል። ታድያ እንዲህ ነገሩ ያንገበገባቸው ቢኖሩም፣ በተቃራኒው ‹‹የቢራ ዋጋ ጭማሪ እንዴት ይህን ያህል መነጋገሪያ ሊሆን ይችላል፤ ይህማ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ብዙ የቢራ አድናቂዎች ያፈራች መሆኗን ነው።›› ሲሉ ሐሳባቸውን የሰነዘሩ አልጠፉም።

በዚህ ሳምንት የቢራ ዋጋ ጭማሪ መነጋገሪያ ሆኖ በመቆየቱ፣ ጭማሪ ተደርጎበት ሳምንታት ያስቆጠረውን የጤፍ ዋጋ በጥቂቱም ቢሆን ዳግም ትኩረት እንዲያገኝ ማድረጉንም ታዝበናል።
የዋጋ ጭማሪው ደግሞ እንደተለመደው አለመሆኑ ነገሩን ትኩረት እንዲስብ አስችሏል። ለምሳሌ የአንዱ ቢራ ዋጋ እስከ ከ30 ብር መሆኑ፣ በብዙ ሰዎች ቀልድ መፍጠሪያ ጭምር ሆኗል። አንዱ ሰው ታድያ፤ እንደ ወትሮው ከጓደኞቹ ጋር መጠጥ ቤት ጎራ ብሎ ነው፤ አስተናጋጁን ጠራ። ‹ምን ልታዘዝ› ሲባል፣ ‹አንድ ቢራ እና ሦስት ብርጭቆ›

አንዳንዶች በአንጻሩ ‹‹ምነው የጤፍ ዋጋ በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ሺሕ ብር የዋጋ ጭማሪ ሲያሳይ የት ነበራችሁ? መጀመሪያኮ ሲበላ ነው፣ ሊጠጣ የሚችለው።›› ብለዋል። ሌሎቹ ደግሞ ‹የናቅናትን ጠላ ይቅር በይን ማለት እንጀምራለን። እንደው ከቻልንና ብሎልን ቢራ ከጠጣን፣ እንደበፊቱ በብርጭቆ ሳይሆን በአረቄ መጠጫ መለኪያ እያጣጣምን ነው›› ሲሉ የቀለዱም ነበሩ።

ነገሩን ታዝበው ሐሳባቸውን በማኅበራዊ ድረገጽ ካንሸራሸሩት ውስጥ ‹‹ብዙዎች ለቢራ ጥቂቶች ደግሞ ለእንጀራ እየጮሁ የሚገኝባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ሱዳናውያን እኮ ዳቦ ላይ ጭማሪ ተደርጓል ብለው ነው አደባባይ የወጡት›› በማለት አነጻጽረው ተችተዋል። በተመሳሳይ ‹‹ጤፍ የተወደደ ጊዜ ተጋግዘን ብንጮኽ፣ ዛሬ ቢራ ሲጨምር የት በደረስን›› ያሉም አሉ።

ሳቅ ከፈጠሩ ቀልዶች መካከል ተከታዩ ይገኝበታል፤ ‹‹የቢራ ዋጋ ጭማሪውኮ የኢትዮጵን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው። የእኛን የመንግሥት ሠራተኞችን ደሞዝ ያማከለ አይደለም። ጎበዝ! ድህነታችንና ብስጭታችንን የምንረሳው በቢራ ነበር። በሕግ አምላክ እንጠጣበት።››

ከቢራ ዋጋ ጭማሪ በተጨማሪ የጠርሙስ ለስላሳ መጠጥም፣ አንዱ ከ13 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com