በጦርነቱ ምክንያት ለወራት መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ሠላም ወደሠፈነበት አካባቢ ተፈናቅለው የነበሩ የወልዲያና አካባቢዋ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው ቢመለሱም፣ ቤት ንብረታቸው መውደሙን ተከትሎ ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ነዋሪዎቹ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከሐምሌ ወር 2013 ጀምሮ ቤታቸውን ለቀው ሠላም ወደነበረባቸው ቦታዎች ተጠግተው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ከወራት ቆይታ በኋላ ቀድሞ ወደነበሩበት ቦታቸው የተመለሱት ነዋሪዎች፣ ቤት ንብረታቸው በታጣቂ ቡድኑ በመዘረፉ የመሠረታዊ ፍላጎት ዕጥረት እንደተጋረጠባቸው ነው መረዳት የተቻለው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው የህውሓት ቡድን ዘረፋና ጥቃት ከፈጸመባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች መካከል የተሻለ የመንግሥትና የግለሰብ ንብረት የሚገኝባት ወልዲያ ከተማ ላይ በርካታ ንብረቶች መዘረፋቸው ሲነገር መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ይበልጣል አበበ የተባሉት ግለሰብ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ደሴ ተፈናቅለው እንደቆዩ ገልጸው፣ “ተፈናቅለን ብንመለስም ሌላ ሥቃይ ነው የጠበቀን። ንብረታችን የጎረቤት ኹሉ ሳይቀር ተዘርፏል፤ ድጋፍም እየተደረገልን አይደለም” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይበልጣል፣ ከመፈናቀላቸው በፊት የህወሓት ታጣቂዎች ባደረሱባቸው ድብደባ ምክንያት በእንጨት ቃሬዛ እንኳን መንቀሳቀስ ሳይችሉ እንደቆዩ ገልጸው፣ ገንዘብና ልብስ ሳይቀር ስለተዘረፈባቸው ከነሙሉ ቤተሰባቸው ጋር ችግር ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አዲስ ማለዳ የድጋፍ ዕርዳታ ከሌለ የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዴት ነው የሚኖረው ስትል ጥያቄ ያቀረበችላቸው አስተያየት ሠጭው፣ “ማኅበረሰቡ እየኖረ ያለው ከወፍጮ ቤት ደጃፍ ታፔላ ተተክሎ ለማስፈጨት የሚመጡ ሰዎች ትንሽ ትንሽ ዱቄት እየሰጡ፣ ያለው ለሌለው እያካፈለ ነው”፤ እናም በመንግሥት በኩል ጥሪ የተደረገለት ዳያስፖራው እንኳ አካባቢውን ቢጎበኘው መልካም ነው ብለዋል።
ዘሀራ መሐመድ የተባሉት የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው “በጦርነቱ ወቅት ሦስት ወር ሙሉ በችግር ውስጥ ነበርኩ፤ በመጨረሻም ወደ ሐይቅ ሔጄ ቤተሰብ ጋር ተጠጋሁ። እስካሁን ግን እንደኔ የተቸገሩ ጎረቤቶቸም ሆኑ እኔ ምንም ድጋፍ አላገኘንም” በማለት ይናገራሉ።
ወልዲያ ከተማ ከሳምንታት በፊት ከህወሓት ቁጥጥጥር ነጻ ብትወጣም፣ እስከአሁን ድረስ የመብራትና የውኃ አገልግሎት አለማገኘቷን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የንጹህ ወኃ ችግርን ሦስት ወር ሙሉ እየተጋፈጡ በቦታው የቆዩት ዘሀራ መሐመድ፣ ማኅበረሰቡ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው “ሰይጣን ባህር” ከተሰኘው ቦታ ወኃ እየቀዳ እየተጠቀመ እንደሚገኝ እና ችግሩ እስካሁን እንዳልተቀረፈ አንስተዋል።
አዲስ ማለዳ፣ የጥቅምት ወር 2014 ዕትሟ ባስነበበችው ዘገባ፣ በከተማው የውኃ አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ የቆሸሸ ወራጅ ውኃን ከወንዝ ቀድተው በመጠቀማቸው ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ ሰለባ መሆናቸውን ማሳወቋ ይታወሳል።
የውኃ ችግር አለ የሚሉት ኤፍሬም አዲስ የተባሉት ግለሰብ በበኩላቸው፣ በወልዲያ ከተማ አልፎ አልፎ ድጋፍ የሚደረግበት ኹኔታ ነበረ። ነገር ግን፣ ድጋፍና ክፍፍሉ ፍትሐዊ ስላልሆነ ብዙዎች ንጹህ ውኃ እንዳላገኙና በችግር ላይ እንደሆኑ ተመልክቻለሁ ነው ያሉት።
አያይዘውም፣ ተፈናቃዮች ከተመለሱ በኋላም ቢሆን ዕርዳታ አለ ተብሎ ምዝገባ እየተካሄደ ነበር። ግን ውስጥ ለውስጥ እንጅ ኹሉም ሊሠማ ባለመቻሉ ሰው የሌለው አካል የዕርዳታው ተጠቃሚ አልሆነም ሲሉ የተመለከቱትን አብራርተዋል።
ይበልጣል አበበ በበኩላቸው፣ “ሚዲያዎች ሰሞኑን በወልዲያ ከተማ 400 ኩንታል ዱቄት ዕርዳታ ተደርጓል ብለው እየዘገቡ ነበር፤ እውነታው ግን አሁንም ቢሆን ማኅበረሰቡ ችግር ላይ ነው” ሲሉ ነው የታዘቡትን ያብራሩት።
በጉዳዩ ዙሪያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወልዲያ ከተማ 06 ቀበሌ የተፈናቃዮች አስተባባሪ ቸኮለ አማረ በበኩላቸው፣ ባሳለፍነው ጥር ሦስት 2014 ለከተማዋ 06 ቀበሌ ነዋሪዎች የ15ኪሎ ስንዴና ግምሽ ሊትር ዘይት ዕርዳታ ማከፋፈል ተጀምሯል ሲሉ ተናግረዋል።
አያይዘውም፣ ለ05 ቀበሌ ነዋሪዎችም ድጋፍ ለማድረግ ቀጠሮ ተይዟል፤ ለቀሪዎቹም ሠሞኑን ድጋፍ ለማዳረስ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።
አዲስ ማለዳ የነዋሪዎቹን ቅሬታ ይዛ ለወልዲያ ከተማ ከንቲባ ሐብታሙ አሊጋዝ ስልክ የደወለች ሲሆን፣ ስልካቸውን አንስተው “ስብሰባ ላይ ነን” ብለው ከቆይታ በኋላ በድጋሚ ቢደወልላቸውም፣ ስልክ ለማንሳት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።
ተመሳሳይ ርዕሶ
ችግራቸው እንደብዛታቸው የጨመረ ተፈናቃዮች – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014


