የፀደይ ባንክ ቦርድ ጥር 9/2014 በባህርዳር ከተማ ባካሄደው ቦርዱየመጀመሪያ ስብሰባ፣ የፀደይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መኮንን የለውምወሰን እንዲሆን መወሰኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ሥራ አስፈፃሚው ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዎችን ለቦርድ አቅርቦ የሚያስወስን ሲሆን፣ ሌሎች የማኔጅመንት አባላትን ይመድባል ተብሏል። መኮንን ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ምስረታ ጀምሮ በምክትልና በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ላለፉት 25 ዓመታት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ተገልጿል።
ቦርዱ በስብሰባው ባንኩን ለማገዝ ሶስት አደረጃጀቶችን የፈጠረ ሲሆን፣ እነሱም የኦዲት፣ የሪስክና ኮምፕሊያንስ እንዲሁም የሰው ኃይል፣ፋይናንስና አይቲ ኮሚቴዎች ናቸው። የሰው ሀይል ምደባ፣ የቢሮ ስታንዳርድ፣ የመመሪያና የስልጠና ስራዎች በፍጥነት እንዲሰሩም አቅጣጫ ተቀምጧል።
እስካሁን ባለው ሂደት ባንኩ ባላክሲዮኖችን በማስፈረም ለሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ያስረከበ ሲሆን፣ ኤጀንሲው ለብሄራዊ ባንክ አቅርቦ እንደሚጸድቅ ተጠቁሟል። በቀጣይ የሚሰሩት የሰው ሀይል ምደባ፣ የስታንዳርድ፣ የመመሪያና የስልጠና ስራዎች እንዳለቁ ብሄራዊ ባንክ የባንክ ፈቃዱን እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ፈቃዱን በአጭር ጊዜ ለማግኘትም የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014


