በመዲናዋ የኤሌክትሪክ አውቶቡስን ሥራ ላይ ለማዋል ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

0
392

ሰኞ ጥር 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በመዲናዋ አዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አውቶቡስን ሥራ ላይ ለማዋል ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው በውጭና አገር ውስጥ ከሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ለአውቶቡስ ግዥ የሚውል ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ እየሰራ መሆኑን ነው የገለፀው፡፡

የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ሌሊት ቻርጅ አድርገው ቀኑን በሙሉ ያለምንም የጊዜ ብክነት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋሉም ተብሏል፡፡

አውቶቡሶቹ የሙከራ ትግበራ የሚደረግባቸው በሸገር እና አንበሳ አውቶቡሶች ሲሆን፥ ከሸጎሌ ዴፖ ቅርበት ያላቸው አራት ኮሪደሮች ልየታ መከናወኑም ተነግሯል፡፡

የመጀመሪያው ኮሪደር ከአዲሱ ገበያ – ቄራ ሲሆን፥ ሁለተኛው ኮሪደር መነሻውን ዊንጌት አድርጎ መዳረሻው አየር ጤና ይሆናል፡፡

እንዲሁም ሶስተኛው ኮሪደር ከለገሃር ተነስቶ መዳረሻው ድል በር እንዲሁም አራተኛው ኮሪደር ከአውቶቡስ ተራ – አስኮ ይሆናል፡፡

ከዴፖው ያላቸው ርቀት፣ ከBRT ኮሪደሮች ጋር ያላቸው ትስስር እና ገበያ አካባቢዎች መሆናቸው ለኮሪደሮች የሙከራ ትግበራ መመረጥ እንደመስፈርት መቀመጡም ነው የተገለፀው፡፡

በቀጣይ በከተማዋ ሌሎች ተጨማሪ ኮሪደሮችን በማጥናት የተደራሽነት አድማሱን የማስፋት ስራም ይሰራል መባሉን፣ አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
___
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here