ለአዲሱ ብሔራዊ ስቴድየም ግንባታ 2.4 ቢሊየን ብር ወጥቷል ተባለ

0
679

አዲሱ ብሔራዊ ስቴድየም የምዕራፍ አንድ ግንባታ ሐምሌ 2010 ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም እስካሁን 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር አስወጥቶ አለመጠናቀቁ ታወቀ።

የስቴድየሙ ግንባታ በኹለት ምዕራፎች ይከናወናል ተብሎ ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በፌደራል መንግሥት በጀት ተመድቦለት የሚያሠራው ብቸኛው ስቴድየም ነው። ሆኖም የዓለም ዐቀፍ ውድድሮችን ያካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀው ስቴድየም ምዕራፍ አንዱ በተመደበለት በጀት አለመጠናቀቁን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናስር ለገሠ ገልፀዋል።

ብሔራዊ ስቴድየሙ 2008 የተጀመረ ሲሆን ዓለም ዐቀፍ ውደድሮችን ያካሔዳል ተብሎ የሚጠበቅና በተለየ ሁኔታ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንደሚሆን ታቅዶ እየተገነባ መሆኑ ታውቋል።

በተያያዘም ዜና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ያሉት ስቴድየሞች በታቀደላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው የታወቀ ሲሆን የግንባታው የአፈጻጸም ደረጃቸውም የመቀሌ ሰቴድየም 86 በመቶ፣ የባሕርዳር ስቴድየም 89 በመቶ፣ ነቀምት ስቴድየም 95 በመቶ እና ሀዋሳ 90 በመቶ መሆናቸው ታውቋል። ለአፈጻጸም ድክምቱ እንደምክንያት የቀረቡት ችግሮች የበጀት እጥረት እና ሰላም መታጣት መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግራዋል።

የጋምቤላ ስቴድየምን በተመለከተ ግንባታው በ2007 የተጀመረ ቢሆነም በሰው ኃይል እጥረት እና ከክልሉ በጀት አመዳደብ ጋር በተያያዘ ስቴድየሙ እንዳይጠናቀቅ አድርጎታል የተባለ ሲሆን የድሬዳዋ እና ጅጅጋ ስቴድየሞች በፊት የነበረውን የማሻሻል ሥራ እየሠሩ መሆኑም ይታወቃል።

በአጠቃላይ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ በጀት በመሸፈን ስቴድየሞችን በተለያዩ ክልሎች መገንባት አለባቸው በሚል እየተሰራ መሆኑን ቢታወቅም በአጠቃላይ የስቴድየም ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም አነስተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here