እየተዳፈኑ መልሰው ከሚቆሰቆሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እሳቶች መካከል “የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም” አንዱ ነው። “ልዩ ጥቅም” ሲባል ምን ማለት ነው? ለአንድ ክልል “ልዩ ጥቅም” መስጠት ለምን አስፈለገ? ለአንድ ወገን “ልዩ ጥቅም” የመስጠት አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ነው ወይ? የሚሉ እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በየጊዜው የሚፈነዱ ነገር ግን አጥጋቢ ምላሽ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋስኦ ላይ ክፉ ጥላቸውን አጥልተዋል። ከሰሞኑ ማባሪያ የሌለው “የልዩ ጥቅም” ውዝግብ እንደገና ማገርሸት በመንተራስ በፍቃዱ ኃይሉ ርዕሰ ጉዳዩ የሐተታ ዘ ማለዳ መወያያ አድርጎ አቅርቦታል።
ታከለ ዑማ ሐምሌ 10፣ 2010 የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው ሲሾሙ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቅፅበት ማወዛገብ ከጀመሩት ጉዳዮች መካከል ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ አላት የሚባለው “ልዩ ጥቅም” ጉዳይ ቀዳሚው ነው። ታከለ የከተማ መስተዳድሩን ከመቀላቀላቸው በፊት የካቲት ወር 2010 በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረውት ነበር የተባለው “አፋን ኦሮሞን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ለማድረግ፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘውን ሕገ መንግሥታዊ ጥቅም (መብት) እንዲፈፀም፣ የልዩ ዞንና የአዲስ አበባ ወሰንን በዘለቄታው ለማካለል ኦሕዴድ ተግቶ እንደሚሠራ ማዕከላዊ ኮሚቴው በልበ ሙሉነት ወስኗል” የሚል ጽሑፍ ሲሽከረከር መዋሉ አይዘነጋም። የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ በወቅቱ ባለመካሔዱ አንዳንድ ሕጋዊ ሁኔታዎችን በማስተካከል፥ ታከለ ምክትል ከንቲባ ሆነው ሲሾሙ በሥልጣን ደረጃ ግን የከንቲባነቱን ማዕረግ ተቆጣጥረዋል። ይሁንና ከቀድሞ አስተያየታቸው ውስጥ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ – ኦዴፓ (በወቅቱ ኦሕዴድ) ቁርጠኛ መሆኑን ያወጁበት “ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘው ሕገ መንግሥታዊ ጥቅም” የሚለው በአንዳንዶች ዘንድ የተሾሙት ለዚሁ ነው በሚል ጥርጣሬ ውስጥ ጥሏቸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ፣ የኢትዮጲስ ጋዜጣ ሥራ አስኪያጅ እስክንድር ነጋ በጥር ወር 2011 ማገባደጃ ላይ አስተያየት ሲሰጡ በታዩበት የቪዲዮ ቃለ ምልልስ ላይ፥ አዲስ አበባ “ለመብቷ የሚከራከርላት ሰው ወክሏት አያውቅም” ካሉ በኋላ፣ የአዲስ አበባን ጉዳይ ዴሞክራሲ ይፈታዋል ብለዋል። ሌሎች ጥያቄዎች በሙሉ ለጊዜው ተትተው “ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አላት ወይስ የለትም?” የሚለውን ጥያቄ እንደ ዋነኛ ጥያቄ በማነገብ፣ “አላት” ለሚል ድርጅት የአዲስ አበባ ሰው ድምፅ መስጠት አይገባውም ብለዋል። አያይዘውም “አቶ ታከለ ዑማ ወይ ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም የላትም ማለት አለባቸው፣ አሊያም ‘አላት’ የሚሉ ከሆነ ግን በምርጫ እንቀጣቸዋለን” ማለታቸው የውዝግብ መንሥኤ ሆኖ ሰንብቷል።
“ልዩ ጥቅም የሚለው ራሱ የመለስ [ዜናዊ] ሸር ነው፤ ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር የለም፣ የባለቤትነት ጥያቄ ነው” በሚል በኦኤምኤን ቴሌቪዥን ቀርበው ምላሽ የሰጡት የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃዋር መሐመድ ናቸው። “አንድ ክልል በዋና ከተማው ላይ ልዩ ጥቅም ብሎ የሚጠይቅበት ምንም ሕጋዊም ሆነ ‘ሎጂካል’ የሆነ ትንታኔ የለም። የአማራ ክልል ባሕር ዳር ላይ ልዩ ጥቅም ይኑራት፣ ትግራይ በመቀሌ ላይ ልዩ ጥቅም ይኑራት የሚለው አካሔድ አያዋጣም” ብለዋል። ጃዋር አክለውም “ስለ ምርጫ የሚነሳው [ከእንግዲህ] በምርጫም፣ በፍጥጫም፣ በማንኛውም የኦሮሚያን የፊንፊኔ ባለቤትነት ማውረድ አይቻልም” ብለዋል። ጉዳዩ ከንቲባ ማን ይሁን የሚለው አለመሆኑን የተናገሩት ጃዋር፣ “ካስፈለገ ከቻይናም ማስመጣት ይቻላል” በማለት ዋናው ጥያቄ “የባለቤትነት፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ” መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።
“ልዩ ጥቅም” ለምን?
“ልዩ ጥቅም” የሚለው ቃል የመጣው በ1987 ከፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49/5 ነው። አንቀፁ “የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ኹለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እስክንድር ነጋ እንደሚሉት “ወሳኙ ነገር የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የሚለው ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሲገባ፣ የሕግ አውጪው መነሻ መግፍኤ (‘ሞቲቭ’) ምንድን ነበር የሚለው ነገር ነው” ይላሉ። “ሲጀመር፣ ሕገ መንግሥቱ ከሕዝብ የመነጨ ሳይሆን በኢሕአዴግ ሕዝብ ላይ የተጫነ ነው” ካሉ በኋላ፣ በወቅቱ ኢሕአዴግ በሕወሓት የበላይነት ይመራ ስለነበር “ልዩ ጥቅም” የሚለው ሲገባ የሕወሓት መነሻ መግፍኤ ምንድን ነበር ብለን መጠየቅ ይኖርብናል ይላሉ። “እውነት የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ አስበው ነው?” ብለው ከጠየቁ በኋላ ራሳቸው “አይደለም፤” በማለት የሚመልሱት እስክንድር ነጋ “ልዩ ጥቅም የሚለውን ሕዝብን ለመከፋፈል የጊዜ ቦንብ አድርገው ነው የቀበሩት። በተለይም በአማራና ኦሮሞ መካከል መከፋፈል ለመፍጠር ሳንቃ አድርገው ነው ያስቀመጡት” በማለት መነሻ ዓለማው አሁን የምናየውን ውዝግብ ማስከተል እንደሆነ ይናገራሉ።
ይኼንኑ በማስመልከት ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ይህ አንቀፅ ሲገባ የነበረው መነሻ መግፍኤው ምንድን ነበር በማለት በወቅቱ የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ኮሚሽን አባል ለነበሩት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። “አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል ነው ያለችው” በማለት ዋነኛው ጉዳይ የአቀማመጧ ጉዳይ መሆኑን እና ይህም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መቀመጡን ጠቁመዋል። ነጋሶ “ይቺ አዲስአበባ ከኦሮሚያ የግንባታ ግብኣቶቿን እንደ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ወዘተ. ታስመጣለች። ውሃ ከለገዳዲና ገፈርሳ ነው የምታስመጣው። ኤሌክትሪሲቲም ለብዙ ጊዜ ከቆቃ ነበር የምታገኘው” ካሉ በኋላ “ስለዚህ ኦሮሚያ በሆነ መንገድ መካስ አለባት… ይኼ ነው ዋናው ጥያቄ” ብለዋል። ይሁን እንጂ ጃዋር እንደሚሉት ጥያቄው የባለቤትነት እንዳልሆነ ነጋሶ ይናገራሉ። የታሪክ ጥያቄ ትተናል፤ እሱን ድጋሚ እናንሳ ከተባለ ሕገ መንግሥቱን መከለስ ይኖርብናል፤ አሁን የምናወራው የአስተዳደር ጉዳይ ነው” በማለት።
ይህንን ክርክር ከመሠረቱ የማይቀበሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቻምየለህ ታምሩ ናቸው። “እንደ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ግልገል ግቤ የመሳሰሉት የኃይል ማመንጫዎች ሲገነቡ ገበሬዎችን አፈናቅለዋል። ነገር ግን የሚያመነጩት ኃይል ኦሮሚያን ጨምሮ ለሁሉም ክልሎች እኩል ነው ያለታሪፍ ልዩነት የሚከፋፈለው። ኦሮሚያ ለአዲስ አበባ ውሃ በማቅረቡ ልዩ ጥቅም ላግኝ ካለ፥ ኦሮሚያም ለሚያገኘው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ልዩ ጥቅም መስጠት አለበት ማለት ነው።”
እስካሁን ኦሮሚያ “ልዩ ተጠቃሚ ናት”
አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ መሆኗን በአካባቢ ብክለት፣ በሀብት አጠቃቀም እና ሌሎችም እንደተጎጂነት የሚያቀርቡት ፖለቲከኞች ቢኖሩም እውነታው ግን አዲስ አበባ ኦሮሚያ መሐል መገኘት ለኦሮሚያ ጂኦግራፊያዊ በረከት እንዳዘነበላት የምጣኔ ሀብት ተንታኞች ይናገራሉ።
የአዲስ ማለዳ እና የኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት መራሒ አሰናጅ አማን ይኹን ረዳ ይናገራሉ። “ኦሮሚያ አዲስ አበባን በመክበቧ አሁንም ቢሆን ተጠቃሚ ነች። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው መዋዕለ ንዋይ (‘ኢንቨስትመንት’) ውስጥ 40 በመቶ የተከማቸው በአዲስ አበባ ነው። ሌላው 40 በመቶ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉት ልዩ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ ነው። ቀሪው 20 በመቶ ለሌሎቹ ክልሎች የሚደርሳቸው” በማለት ኦሮሚያን በኢኮኖሚ ተጎጂ የማድረጉ ክርክር ውሃ የማያነሳ መከራከሪያ መሆኑን ያሠምሩበታል። “ይህንን ያህል መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል” በማለት።
አማን ይኹን “የኢትዮጵያ ዓመታዊ ጥቅል ምርት ከ50 በመቶ በላይ አዲስ አበባ ነው ያለው። ከተማዋ ትልቅ ገበያ ነች። ብዙ የሸማቾች አቅም አላት። ይኼ ደግሞ አዲስ አበባን በ100 ኪሎ ሜትር ‘ራዲየስ’ ለከበባት የኦሮሞ ገበሬ መልካም ዕድል ነው። የኦሮሞ ገበሬ ለዚህ ሸማች እና ገበያ ያለውን ተዳራሽነት የሚያክል ተዳራሽነት የጎጃሙም፣ የትግሬውም፣ ሌላውም ገበሬ የለውም” ይላሉ።
ይሁንና የልዩ ጥቅም ጥያቄው ከዚህ የኢኮኖሚያዊ ትንታኔም ባሻገር ይቀጥላል።
የታሪካዊ ባለቤትነት “ልዩ ጥቅም”?
ነጋሶ ጊዳዳ “ስለታሪክ አናወራም” ይበሉ እንጂ “ልዩ ጥቅም” የሚለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የገባው በአንድ በኩል “አዲስ አበባ ከኦሮሞ የተወሰደች በመሆኗ ያንን ታሪክ ለማስታወስ ነው” ይላሉ። በሚያዝያ ወር 2009 ““የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የጥናት ሰነድ” የሚል ባለ 46 ገጽ ሐተታ እና በዚሁ መሠረት የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ በበይነመረብ ተለቀው ነበር። ይህንን ረቂቅ እና መግለጫ መንግሥት አላውቀውም ይበል እንጂ፥ ብዙዎች ‘ትኩሳቱን ለመለካት’ የተለቀቀ ሰነድ አድርገው ወስደውታል። በአዲስ አበባ ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች የአዳራሽ ኪራይ እንኳን ሲፈልጉ “ቅድሚያ ይሰጣቸዋል” ከሚለው ረቂቅ ጋር ተያይዞ የነበረው የመግለጫ ሰነድ በአንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ስላለው “ልዩ ጥቅም” የሚሰጠው ማብራሪያ ጋር ይመሳሰላል።
ሰነዱ “በወቅቱ ፊንፊኔ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢና ዙሪያው ከኦሮሞ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የቱለማ ጎሣ ከሦስቱ ዐቢይ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የዳጪ ንዑሳን ጎሳዎች የሆኑት የጉለሌ፣ የኤካ፣ የገላን እና የአቢቹ ጎሳዎች ይኖሩበት እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል” ይልና ከትንሽ ማብራሪያ በኋላ በዐፄ ምኒልክ “ወረራ” መሬቱ ከኦሮሞ ገበሬዎች እንደተቀማ እና የከተማዋ አካባቢዎች የኦሮሞ ሥማቸው እንደተቀየረ ያትታል። በማከልም የኦሮሞ ተወላጆችን በተለይም የቱለማ ጎሳዎችን “ነባር የፊንፊኔ ተወላጆች” በማለት ቀሪዎቹን “መጤ” ያደርጋቸዋል።
የሕግ ባለሙያው ፀጋዬ አራርሳ አዲስ ስታንዳርድ መጽሔት (ድረገጽ) ላይ ጥር 2009 “The Interest that is not So Special” (‘ብዙም የተለየ ነገር የሌለው ልዩ ጥቅም’) በሚል ባተሙት ረዘም ያለ መጣጥፍ ላይ ይህንኑ “የመጤ” እና “ነባር” ተረክ አስተጋብተዋል። በዚህ በርካታ የሐሰት ማጣቀሻዎችን ተጠቅመዋል በሚል በአቻምየለህ ታምሩ የተብጠለጠለባቸው መጣጥፋቸው “ባለቤቱ እንግዳ ሆነ” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንትም ጀምሮ በአሁኑ አሰፋፈሩ የነበረ እና በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ መሬቱን የተቀማ እንደሆነና “ልዩ ተጠቃሚነት” የባለቤትነት ማዕረጉን እንደሚያሳንስበት ተከራክረው ጽፈዋል።
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በመጀመሪያ እትሟ ይኼንን የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ “አዲስ አበባ፤ ፊንፊኔ – ሸገር – በረራ” በሚል ሐተታ የቃኘችው ሲሆን፥ በኦሮሞ ብሔርተኞች “ፊንፊኔ ኬኛ” (ፊንፊኔ የኛ) በሚል ለተጀመረው ትርክት፣ የአማራ ብሔርተኞች “በረራ የኛ” የሚል (ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የጠፋች በአዲስ አበባ ደቡብ ምሥራቅ ትገኝ የነበረች ጥንታዊ ከተማ በመጥቀስ) አፀፋዊ ትርክት ያመጡ መሆኑን አትታ ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ትርክቶች ስንዝር እንደማያራምዱ ተመልክቷል። በወቅቱ አስተያየት ከሰጡ ምሁራንን መካከል የታሪክ ምሁሩ አበባው አያሌው “ከታሪክ አኳያ ይኼንን መሬት ይኼንኛው ሕዝብ ረግጦታልና የዚህ ነው፣ የዛኛው ነው ማለት አይቻልም” በሚል ከታሪክ አንፃር ‘እዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት እነማን ናቸው?’ ከተባለ ማለቂያ ወደ ሌለው ሌላ አጨቃጫቂ ጉዳይ እንደሚገባ አመላክተዋል። አበባው ምሳሌ የሚጠቅሱትም “በ14ኛው እና 15ኛው ክፍለ ዘመን እዚህ አካባቢ የነበሩት ወርጂ የተባሉ ሕዝቦች ነበሩ” በማለት ነው። ሸዋ ከዚያ በፊት እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የኢፋት ሡልጣኔቶች ይገዟት እንደነበርም ተጽፏል።
ረቂቁ ምን ይላል?
መንግሥት አላውቀውም ያለው “ረቂቅ” በበይነመረብ ላይ መዘዋወር ከጀመረ ከአንድ ወር በኋላ ሰኔ 20 ቀን 2009፥ መንግሥት ሌላ እና አዲስ ረቂቅ በማስተዋወቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ከአፀደቀው በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል። ረቂቁ ቀደም ሲል በበይነመረብ ተለቅቆ ባለቤት ካጣው “ረቂቅ” ጋር ያለው ልዩነት በተለይም “ማንነትን መሠረት ያደረገ አድልዖን ያበረታታሉ” በሚል ከፍተኛ ውግዘት የደረሰባቸው አንቀፆች ከማስወገዱ በቀር እምብዛም ነው።
ረቂቅ አዋጁ ከሁሉም በላይ ትኩረት የሰጠው የቋንቋ ጉዳይ መሆኑ ይስተዋላል። አንቀፅ 4 ላይ በከተማው መስተዳድር ወጪ በአፋን ኦሮሞ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ይደራጃሉ ይልና፣ አንቀፅ 6/1 ላይ ደግሞ አፋን ኦሮሞ በከተማ መስተዳድሩ የሥራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል ይላል። በተጨማሪም አመቺ የሆኑ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሰፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች እንደ አስፈላጊነታቸው በቀድሞ የኦሮምኛ ሥማቸው እንዲጠሩ ይደረጋል (አንቀፅ 6/2) ይላል።
ከዚህ በተለየ ኦሮሚያ ክልል ለመንግሥት ሥራ ከሊዝ ነጻ ያገኛል (አንቀፅ 7) ይላል፣ የውሃ ጉድጓድ እና የመሳሰሉትን የሚቆፍርባቸው የክልሉ አካባቢዎችን እና ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል (አንቀፅ 8) ከማለቱም ባሻገር “የባቡር መሠረተ ልማት ዝርጋታና አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉትን የክልል ከተሞች ያማከለ እንዲሆን ይደረጋል” (አንቀፅ 9) ይላል። በመሠረቱ በተለይም በአንቀፅ 9 የተቀመጠው የአዲስ አበባን ከተማን በአዲስ አበባ ዙሪያ ወዳሉት “የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች” መስፋፋት የሚያበረታታ ነው ማለት ይቻላል።
አንቀፅ 12 ደግሞ በመንግሥት ወጪ የሚገነቡ ኮንዶሚኒየሞች የኦሮሚያ የመንግሥት ሠራተኞችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኮታ እንደሚመደብላቸው ይደነግጋል። ይኼም “የኦሕዴድ (ኦዴፓ) ልዩ ተጠቃሚነት” በሚል ከትችት አልዳነም።
ረቂቁ ከእነዚህ አንቀፆች ውጪ የተለየ ነገር ይዟል ከተባለ በክፍል ሦስት “ስለ ጋራ ምክር ቤት” መቋቋም የተጠቀሰው ዋነኛው ነው። በዚሁ ክፍል አንቀፅ 18 እንደተጠቀሰው የጋራ ምክር ቤቱ ዓላማ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49/5ን በተመለከተ በረቂቁ “የተዘረዘሩት ልዩ ጥቅሞች በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆኑ መከታተል፣ መገምገምና ለአፈፃፀሙ ቅልጥፍና ድጋፍ ማድረግ ነው”። የምክር ቤቱ አባላት ከአስተዳደሩ ምክር ቤት እና ከኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በእኩል ቁጥር የተውጣጡ እንደሚሆኑም ረቂቅ አዋጁ ይጠቅሳል።
የታሪክ ምሁሩ አበባው አያሌው “ከታሪክ አኳያ ይኼንን መሬት ይኼንኛው ሕዝብ
ረግጦታልና የዚህ ነው፣ የዛኛው ነው ማለት አይቻልም” በሚል ከታሪክ አንፃር ‘እዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት እነማን ናቸው?’
ከተባለ ማለቂያ ወደ ሌለው ሌላ አጨቃጫቂ ጉዳይ እንደሚገባ አመላክተዋል
በጥቅሉ ረቂቅ አዋጁ አራት ክፍሎች እና 24 አንቀፆች አሉት። ክፍል አንድ ጠቅላላ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፣ ክፍል ኹለት “ክልሉ በከተማው አስተዳደር ስለሚኖረው አገልግሎቶች አቅርቦት” የሚያወራ ነው። ክፍል ሦስት “ክልሉ በከተማው አስተዳደር ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ልዩ ጥቅም” ሲያወራ፣ ክፍል አራት “ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን” ይዟል።
ከረቂቁ ጋር አብሮ የተለቀቀው መግለጫ ላይ በረቂቁ አዘገጃጀት ወቅት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እንደተሳተፉበት የተገለጸ ከመሆኑም ባሻገር ሰፊ ሕዝባዊ ውይይት ይካሔድበታል ቢልም፥ ረቂቁ እስካሁን ለምክር ቤት ካለመቅረቡም በላይ “የገባበት አይታወቅም” እስከሚባል ደርሷል። ብዙዎች “ኦሕዴድ/ኦዴፓ የፌዴራሉን ማዕከላዊ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ አዋጁን አይፈልገውም” የሚል አስተያየት እየሰጡ ቢሆንም፣ “ለብዙ ውዝግቦች የሚዳርገው የአዋጁ አለመውጣት ነው” የሚሉም አልታጡም። ነጋሶ ጊዳዳ “ኢሕአዴግ ለምንድን ነው ዝርዝር ሕጉን እስካሁን ያላወጣው?” በማለት ይጠይቃሉ። “አሁንም ቶሎ ማውጣት አለበት። ይህንን ሁሉ ዓመት ሙሉ ሳይወጣ መዘግየቱ ነው ዋናው ችግር” ብለዋል።
የሆነ ሆኖ “ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር አያስፈልግም” የሚሉት ረቂቁ ከተቀመጠበት መሳቢያ አንድ ቀን ተመዝዞ መውጣቱ እንደማይቀር አሁን መጣ ሔደት የሚሉት ውዝግቦች ያመላክታሉ ባዮች ናቸው። በሌላ በኩል ረቂቁ “ምንም የተለየ ጥቅም አይሰጥም፤ ትርፉ ሥሙ ነው” የሚሉ ደግሞ በሌላ ወገን አሉ። በዚህም የተለያየ አማራጮችን እየጠቆሙ ነው።
“ፌደራሉ መንግሥት ከተማውን ይቀይር”
ፀጋዬ አራርሳ ከላይ በጠቀስነው “ምንም የተለየ ነገር የሌለው ልዩ ጥቅም” በሚለው መጣጥፋቸው ላይ ስድስት አማራጭ “የመፍትሔ ሐሳቦችን” ጠቁመዋል። አንደኛ፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ሁሉም ክልሎች የሚሥማሙበት ግዛት መከለል፤ ኹለተኛ፣ በሌላ ክልል ወይም በኦሮሚያ ሌላ ከተማ አዲስ ዋና ከተማ በመቆርቆር ተጠሪነቱን ለክልሉ ማድረግ፤ ሦስተኛ፣ ለፌዴራል መንግሥቱ የተለያዩ ክፍሎች መቀመጫ ካንድ በላይ ከተማዎችን መምረጥ፤ አራተኛ፣ በየዐሥር ዓመቱ ገደማ የሚለዋወጥ ተንቀሳቃሽ የፌዴራል ዋና ከተማ ማድረግ፤ አምስተኛ፣ አዲስ አበባን ተጠሪነቷ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሆነች ራስ ገዝ የኦሮሞ ከተማ አድርጎ ፌዴራል መንግሥቱን ልዩ ተጠቃሚ ማድረግ፤ እና ስድስተኛ፣ አዲስ አበባን ለኹለቱም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነች ከተማ ማድረግ ናቸው።
ይሁንና በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተሳትፎ ለተገነባችው አዲስ አበባ በተለይም “የፌደራሉ ዋና ከተማ መቀየር” ጉዳይ አሥማሚ አይሆንም። በተለይም ደግሞ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ከተማ ይልቅ ብዙ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባትን ከተማ ለቅቆ ወደ ሌላ መዞር ለፌደራል መንግሥቱ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ አጠያያቂ ይሆናል።
“ኦሮሚያ ከተማውን ይቀይር”
ከፀጋዬ አራርሳ በተቃራኒ ኦሮሚያ ዋና ከተማዋን ብትቀይር ይሻላል የሚሉት ኦላና አባጢቆ የተባሉ ጸሐፊ ናቸው። ጸሐፊው ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ኢንሳይት በተባለ ድረገጽ ላይ “Let’s end Finfinne saga, and shoot for the stars” (የፊንፊኔን ነገር ትተን አዲስ ነገር እንሞክር) በሚል ርዕስ ባሰፈሩት መጣጥፋቸው ላይ ስለ “ልዩ ጥቅም” የተጻፈውን “መጀመሪያ ልዩ ጥቅም ከሚለው ሐረግ ጋር እንግባባ” በማለት ሐረጉ አዲስ አበባን የኦሮሚያ እንደማያረጋት ይጠቁማሉ። ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ከተማ አድርጎ ቢመለከታት ኖሮ “ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ያለው ጥቅም” ብሎ አይጽፍም ነበር” በማለት መግቢያችን ላይ የጠቀስነውን የጃዋር መሐመድን ንግግር የሚያጠናክር ነገር ግን ተቃራኒ መንፈስ ያለው ጽሑፍ አስፍረዋል። ከተማዋ ማንነትን አቅላጭ እና ዋጭ ናት የሚሉት ኦላና አባጢቆ በይዘቷ አዲስ አበባ የብዙ ብሔሮች መኖሪያ ብትሆንም ነዋሪዎቿን በባሕል አማራ ታደርጋቸዋለች ብለው ተከራክረዋል።
ኦላና በመቀጠልም፣ የኦሮሞ ትግል ረዥም ጊዜ የፈጀው ኦሮሞነት ዋና ባሕል የሆነበት ከተማ መገንባት ባለመቻሉ ነው በማለት በባሕል ኦሮሞ የሆነ ከተማ መገንባት አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተው ጽፈዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፣ “ባጭሩ፣ ፊንፊኔ የአገሪቷ ተቃርኖዎች ሁሉ መጠራቀሚያ ነች። አዲስ አበባ በጂኦግራፊ ኦሮሚያ መሐል ያለች፣ በባሕል እና ቋንቋ ኦሮሞ ያልሆነች፣ በሕግ ተጠሪነቷ ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠች፣ ነገር ግን ነዋሪዎቿ የራሳቸው የተለየ አስተያየት ያላቸው የኦሮሚያም ዋና ከተማ ነች።” ይህ ካሉ በኋላ ምንም እንኳን ቀላል እና የአጭር ጊዜ ጉዳይ ባይሆንም “የኦሮሞ ባሕልን እና ማንነትን የምታንፀባርቅ አዲስ ከተማ እንገንባ” በማለት የመፍትሔ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ሌላ መፍትሔ
ብዙዎቹ ጥያቄዎች የኢኮኖሚ ናቸው። “የኦሮሞ ገበሬዎች መሬት ያለ አግባብ እየተወረረ ነው” የሚለው ክርክር ዋነኛው ነው። ይሁን እንጂ መሬት የመንግሥት በመሆኑ መንግሥት መሬቱን በሊዝ ሸጦ ገበሬዎቹን ከይዞታቸው ሲያስነሳ የካሣ ማነስ ችግር እንዳለ ብዙዎች ይስማማሉ። ይኼንን እውነት መሆኑን ያስታወሱት አማን ይኹን፥ ግለሰቦች መሬት መግዛት በሚፈልጉበት ጊዜ ግን እውነታው የተለየ መሆኑን ይናገራሉ። “ለምሳሌ ያክል፣ ባለሀብቶች ከገበሬዎች ጋር ተደራድረው ሲገዙ ኹለት መቶ ካሬ ሜትር የሚገመት መሬት እስከ 600 ሺሕ ብር ነው የሚገዙት። ተመሳሳይ ስፋት ያለውን መሬት የጎጃም እና የትግሬ ገበሬዎች በ60 ሺሕ ብር የሚገዛቸው የለም” በማለት በአንድ በኩል ይህም ተጠቃሚነት መሆኑን ሲያመላክቱ፣ በሌላ በኩል የኦሮሚያ አዲስ አበባ ችግር ሌላ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ርዕስ “የትኛውም ኢትዮጵያዊ የትኛውም አካባቢ ሲኖር የተለየ ጥቅም ሊያገኝ አይገባውም” የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቻምየለህ ታምሩ “ልዩ ጥቅም የሚባለው ስለተከበረ የከተማዋ መሥፋፋት፣ የገበሬውም መፈናቀል አይቆምም” ይላሉ፤ ይልቁንም መፍትሔው “ገበሬውን የመሬቱ ባለቤት ማድረግ ነው” ሲሉ በማለት በአጭሩ ይገልጹታል። አቻምየለህ ገበሬው የገዛ መሬቱ ባለቤት ሆኖ የመደራደር አቅሙ ካላደገ እና ለባለሀብት ለሚለቀው መሬት የሚበቃውን ካሣ መጠየቅ ካልጀመረ በስተቀር የማይቀረው የከተማ መሥፋፋት ሲከሰት “ከተማ መጣብኝ እንጂ ከተማ መጣልኝ” አይልም ይላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011