በሳዑዲ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎችን በተመለከተ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ከታዋቂ ሰዎች የተውጣጡ ተውካዮች ወደ ሳዑዲ ለማቅናት ቪዛ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
ማክሰኞ ጥር 17 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሻከረውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማስተካከል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ፡፡
አምባሳደር ዲና በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት ታሪካዊ ነው፤ የሕዝቦች ወዳጅነት የቆየ ከመሆኑም በላይ እጥፍ ድርብ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በኩል አሁን የተፈጠረውን የሁለቱ አገራት አለመግባባት መፍታት አለብን የሚል አቋም አለ።
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት የምክትል ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን መጎብኘታውም በሁለቱ አገሮች መካከል የሻከረውን ግንኙነት ለማስተካከል አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ የሁለቱ አገር ሕዝቦች ጥልቅ የሆነ ግኙነት አላቸው በችግር ጊዜ የሚፈላለጉና የሚረዳዱ ናቸው፡፡
የሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ግንኙነቱን ወደ መልካም ለመለወጥ ያግዛል፡፡
የሁሉቱን አገሮች ግንኙነትም አሁን ካለበት የተበላሽ ግንኙነት ለማውጣት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብሎ መገመት ያችላል ብለዋል፡፡ ግንኙነት አንዴ ከተጀመረ የሚቀጥልና እያደገ የሚሄድ እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ችግሮች ከአገር ለሚወጡ ኢትዮጵያውያኖች ሱዳን ማረፊያ ስትሆን እንደነበር ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ ሕዝቡም ደግሞ ደግና ጨዋ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ አመራር የሚሠራውን ሥራ የሱዳን ሕዝብን አይወክልም ስንል የነበረው ሕዝቡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መልካም ግንኙነት ስላለው ነው፤ በኢትዮጵያ በኩልም ግንኙነቱን ለማሻሻል ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ የሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎችን ጉባዔ ለማስተናገድ ጥሩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ፤ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከኢሚግሬሽን ፣ ከጸጥታ ጉዳይና ከመስተንግዶ ጋር በተገናኘ የተሳካና ሰላማዊ ቆይታ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በሳዑዲ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎችን በተመለከተ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ከታዋቂ ሰዎች የተውጣጡ ተውካዮች ወደ ሳዑዲ ለማቅናት ቪዛ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ጥረቶችን እያደረገ ነው፤ ተወካዮች ወደ ሳዑዲ አምርተው የተቸገሩ ዜጎችን ወደ አገር እንዲመለሱ ያደርጋሉም ብለዋል፡፡
በሳዑዲ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ተጽዕኖዎችን በመቀነስ ረገድ ተወካዮች አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



