በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ካልተሳኩባቸው ምክንያቶች አንዱ በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ የልኂቃን ከፍተኛ ተዋናይነት እና የብዙኃን ዝቅተኛ ተሳታፊነት ነው። በሕግ ደረጃ የመደራጀት መብት ከተረጋገጠ ወዲህ በገዢው ቡድን ውስጥም ይሁን በተቃዋሚዎች ዘንድ ልኂቃን ብዙኃኑን ሳያሳትፉ በራሳቸው የመሰላቸውን እና የወደዱትን ሐሳብ ወይም ርዕዮተ ዓለም “የምንወክለው” ሕዝብ ፍላጎት ነው በማለት መልሰው ሕዝቡ ላይ ይጭኑበታል። ከዚህም በከፋ የዴሞክራሲ ጭላንጭል በታየባቸው ጊዜያት በሙሉ በተለይም በማኅበረሰቡ ውስጥ በተለያየ መንገድ በቂ ውክልና ያላገኙ ዜጎችን ማሳተፍ ፈፅሞ ያልተለመደ ነው።
አሳታፊ ዴሞክራሲ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ዜጎች በሙሉ በፖለቲካ ሒደቶች እና በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ/ተፅዕኖ እንዲያደርጉ ዕድል የሚሰጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው። ምንም እንኳን የዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብ በጥቅሉ ሕዝባዊ ተሳትፎን ማረጋገጥ ቢሆንም በበርካታ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ውስጥ የማይወከሉ በርካታ ድምፆች መኖራቸው “የአሳታፊ ዴሞክራሲ” ፅንሰ ሐሳብ እንዲወለድ አድርጓል። አሳታፊ ዴሞክራሲ ለወትሮው በብዙኃን የሚዋጡ ድምፆችን፣ የተገለሉ፣ በፖለቲካዊ ተፅዕኖ የተዳከሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚወከሉበት እና ድምፃቸው የሚደመጥበት ስርዓት ነው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ የዜጎች ድምፅ የማይወክልባቸው አጋጣሚዎች የተለመዱ ናቸው። ለምሳሌ “ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ የሚኖረው ልዩ ጥቅም” በሚል ሕገ መንግሥት ውስጥ የተካተተው አንቀፅን በተመለከተ የታየው ማስተማሪያ ነው። ይሁን እንጂ ዜጎች ሁሉ በተለይም ደግሞ ይህ የሕገ መንግሥት አንቀፅ ዝርዝር ሕግ ሲወጣለት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚያሳድርባቸው ዜጎች ለማሳተፍ ጥረት ሲደረግ አይታይም። 1ኛ፣ አንቀፁ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሲገባ አስተያየታቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ የተሳትፎ ዕድል አልተሰጣቸውም፤ 2ኛ፣ በአንቀፁ መሠረት ዝርዝሩን የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ሲወጣ የተሳትፎ ዕድል አልተሰጣቸውም፤ 3ኛ፣ ረቂቁ ከወጣ ከ6 ወር በኋላም ምንም ዓይነት የመወያየት ተሳትፎ ዕድል አልተሰጣቸውም። እነዚህ የዚህ አዋጅ እውነታዎች በኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካም ይሁን ዴሞክራሲ ምንም ዓይነት አሳታፊነት እንደሌላቸው ማሳያ ነው።
በዚህ “ልዩ ጥቅም” ጉዳይ አዋጁን ከማርቀቅ ጀምሮ እስከሚፀድቅ ድረስ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ የሚገባቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ቢሆኑም፥ በአሁኑ ወቅት ተሳትፎ የሚያደርጉት ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው የብሔርተኛ ቡድኖች ናቸው። ስለሆነም አዋጁ – አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለመኖሩ ምክንያት – የልኂቃን ፍላጎት ማስፈፀሚያ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011