ዕሮብ ጥር 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሸኔ ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል 163 ትምህርት ቤቶችን ማወደሙ ተገለጸ።
ክልሉ ወንድማማችነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በትምህርት ተደራሽነት ላይ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በጽህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳተናገሩት፣ ሸኔ 163 ትምህርት ቤቶችን በማውድም፣ ከ756 ትምህርት ቤቶች መጻሕፍት በመቃጠል፣ ኮምፒውተሮችን ሌሎች ንብረቶችን በመዝረፍ ትውልዱ እንዳይማር በማድረግ የሕዝብ ጠላት መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።
በሸኔ የሽብር ድርጊት ብቻ 325 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ መሆናቸውን የገለጹት ኃይሉ በዚህም ምክንያት 5 ሺህ 227 መምህራን ከሥራ ገባታ ውጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ የሸኔ የሽብር ድርጊቶችን በመረዳት ከመንግሥት ጋር በመሆን ቡድኑን እየደመሰሰ ነው ያሉት ኃላፊው በስህተት ወደ ሸኔ የተቀላቀሉና ቡድኑ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ሲያቃጥል ያዩ ወጣቶችም የቡድኑን የሽብር ድርጊት በመረዳት እጃቸውን ለመንግሥት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። የቡድኑ አመራርም በቅርቡ እጅ መስጠቱን ጠቁመዋል።
ክልሉ የሸኔ ቡድንን ከመዋጋት ጎን ለጎንም ክልሉ ወንድማማችነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በትምህርት ተደራሽነት ላይ ትኩረት አደርጎ እየሰራ መሆኑን ኃይሉ ተናግረዋል።
አፋን ኦሮሞ ለማሳደግና ትውልዱ እርስ በእራሱ እንዲተዋወቅና ወንድማማችነትን እንዲያጎለብት በማሰብ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአማራ ክልል ኦሮሞ ዞን አስተዳደርና በሌሎች ክልሎች በአፋን ኦሮሞ ትምህርት እንዲሰጥ እየተደረገ ነው።
እንደ ኃይሉ ገለጻ፤ ወንድማማችነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግሥት በ23 ትምህርት ቤቶች በአፋን አሮሞ ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን በጋምቤላ ክልልም ተመሳሳይ ሥራ እየተሰራበት ነው።
ተማሪዎች የሕብረተሰቡን ፍልስፍና፣ ባህላቸውን እሴታቸውን እንዲገነዘቡ ለማድረግ የገዳ ሥርዓት በትምሀርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካቶ ከ1-8ኛ ክፍል እንዲሰጥ ተደርገዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ105 ትምህርት ቤቶች 50ሺህ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርታቸወን እየተከታተሉ ነው። በአማራ ክልል መንግሥት ኦሮሞ ዞን አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶለት ትምህርቱ በአፋን ኦሮሞ እየተሰጠ ነው።
የትምህርት ስታንደርድ ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት በ5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር 100 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመስራት ታቅዶ 93 ትምህርት ቤቶች ተገንብተው የመማር ማስተማር ሥራው ተጀምሯል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ሰባት አዳሪ ትምህርት ቤቶች በ 13 ነጥብ 5 ቦሊዮን ብር በሕዝብ ተሳትፎ ተገንብተው ተማሪዎች የፈለጉትን ቋንቋ የሚማሩበት ዕድል ተፈጥሯል። ፈረንሳይኛ፣ አረብኛና ቻይንኛ ቋንቋዎችም በአማራጭነት እየተሰጡ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
በተጨማሪም ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች ክልሉን የሚያዋስኑት ሱማልኛ፣ አፋርኛ፤ ሲዳሚኛ ቋንቋዎች በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካተው እንዲሰጡ ተደርጓል። በዚህ ፕሮጀክት 3ሺህ መዋዕለ ሕጻናትን ለመገንባት ታቅዶ 2 ሺህ 616 ግንባታው ተጠናቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



