ጀነራል ታደሰ ወረደ እና ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ገ/ተንሳኤን ጨምሮ በቁጥጥር ያልዋሉ 54 ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱ ትዛዝ ሰጠ

0
1105

ዕሮብ ጥር 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ጀነራል ታደሰ ወረደ እና ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ገ/ተንሳኤን ጨምሮ በቁጥጥር ያልዋሉ 54 ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱ ትዛዝ ሰጥቷል።

በነ ጄነራል ታደሰ ወረደ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የህውሐት ወታደራዊ ቡድን አመራርና አባላት ናቸው የተባሉ አጠቃላይ 74 ተከሳሾች ሲሆኑ፣ ከነዚህ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታዩ ያሉት ግን 20 ተከሳሾች ብቻ ናቸው።

ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረቡት ኮነሌል መሐመድ ኑሩ፣ ኮነሬል ባሀሩ ታጀበን ጨምሮ 17 ተከሳሾች ብቻ ሲሆኑ፣ ሦስት ተከሳሾች በህመም ምክንያት ከማረሚያ ቤት አለመቅረባቸውን በተከሳሽ ባልደረቦቻቸው ተገልጿል።

ይሁንና የችሎቱ ዳኞች ከተያዘው የቀጠሮ ሰዓት አርፍደው 4 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ላይ የተሰየሙ ሲሆን ዳኛ በማሟላት ሂደት ምክንያት ማርፈዳቸውን አብራርተው ይቅርታ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ 54 ተከሳሾችን ፖሊስ ከመከላከያ ጋር በመተባበር እንዲያቀርባቸው በሰጠው ተደጋጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ አለመቅረባቸውን ተከትሎ ፖሊስ ያላቀረበበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ታዞ ነበር።

ይህን ትዛዝ ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሾቹ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንደነበሩ በመጥቀስ የትግራይ ልዩ ሀይል አባል በመሆን በጦርነቱ በመሳተፍ
እና በመምራት ላይ ያሉ መሆናቸውን አብራርቷል።

ካለው አገራዊ ሁኔታ አንጻር ተከሳሾቹን ይዞ ለማቅረብ እንደሚቸገር ግንዛቤ እንዲያዝለት በጽሁፍ የማረጋገጫ ምላሹን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ከሳሽ ዓቃቢህግ ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የወንጀል ህግ ድንጋጌ ከ12 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ መሆኑን አብራርቶ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የቀረቡት ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ያልቀረቡት ተከሳሾች በሌሉበት ጉዳያቸው ተነጥሎ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ መርምሮ ትዛዝ ለመስጠት ለዛሬ በይደር በያዘው ቀጠሮ በወንጀለኛ መቅጪያ ሥነ ሥርዓት ህግ ቁ .162/ሀ መሰረት ያልተያዙ 54 ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዛዝ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

የኢትዮጲያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጣ ጥሪ ውጤት ለመጠባበቅ ለየካቲት 8 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱም ታውቋል።

_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here